በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጸሎትን የሚሰማው አካል ማን ነው?

ጸሎትን የሚሰማው አካል ማን ነው?

ጸሎትን የሚሰማው አካል ማን ነው?

ጸሎትን የሚሰማ አካል ካለ፣ ይህ አካል ፈጣሪ መሆን አለበት ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። ደግሞስ የሰውን አንጎል ንድፍ ካወጣው ፈጣሪ ሌላ የምናስበውን ነገር ማን ሊያውቅ ይችላል? የሰው ልጆች የሚያቀርቡትን ጸሎት ሰምቶ የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ መስጠት የሚችል ከፈጣሪ በቀር ማን አለ? በሌላ በኩል ግን ‘በፈጣሪ ማመን ምክንያታዊ ነው?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስብህ ይሆናል።

ብዙ ሰዎች፣ በፈጣሪ ማመን የሚቻለው ዘመናዊ ሳይንስ የደረሰባቸውን ማስረጃዎች ችላ ካልን ብቻ ነው ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ በአምላክ ማመን ከሳይንስ ጋር አብሮ የማይሄድ ነገር ነው ብሎ ማሰብ ከእውነታው የራቀ ነው። እስቲ ቀጥሎ የቀረበውን ሐሳብ ተመልከት፦

▪ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በ21 እውቅ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሚሠሩ 1,646 የሳይንስ ፕሮፌሰሮች ላይ በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው በአምላክ እንደማያምኑ የገለጹት አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።

ሐቁ እንደሚያሳየው በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት በአምላክ መኖር ያምናሉ።

ፈጣሪ መኖሩን የሚያሳይ ማስረጃ

ታዲያ ጸሎትን የሚሰማ አካል መኖሩን ያለ ምንም ማስረጃ መቀበል አለብን ማለት ነው? በጭራሽ። እምነት፣ አንድን ነገር ያለ ምንም ማስረጃ ማመን እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ስህተት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው እምነት ማለት “እውነተኛዎቹ ነገሮች ባይታዩም እንኳ መኖራቸውን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።” (ዕብራውያን 11:1) አንድ ሌላ ትርጉም ደግሞ እምነት “የማናያቸው ነገሮች እውን መሆናቸውን እርግጠኛ እንድንሆን” እንደሚያደርገን ይናገራል። (ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ለምሳሌ ያህል፣ የሬዲዮ ሞገዶችን ማየት አትችልም፤ ይሁን እንጂ በሞባይል ስልክ መነጋገር መቻልህ ድምጽ የሚያስተላልፉ የማይታዩ የሬዲዮ ሞገዶች እንዳሉ ስለሚያረጋግጥ እንዲህ ዓይነት ሞገዶች መኖራቸውን አምነህ ትቀበላለህ። በተመሳሳይም ጸሎት ሰሚ የሆነውን አካል ልናየው ባንችልም በዙሪያችን ያሉትን ማስረጃዎች በመመርመር እንዲህ ያለ አካል መኖሩን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ታዲያ አምላክ መኖሩን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከየት ማግኘት እንችላለን? በዙሪያችን ያሉትን ነገሮች መመልከቱ ብቻ በቂ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በእርግጥ እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው” ይላል። (ዕብራውያን 3:4) በዚህ ሐሳብ ትስማማለህ? በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ስላለው ሥርዓት፣ ስለ ሕይወት አመጣጥ ወይም በምድር ላይ ካሉት ነገሮች ሁሉ እጅግ ውስብስብ ስለሆነው የሰው አንጎል ስታስብ ከሰው የበለጠ አንድ አካል መኖር እንዳለበት ይሰማህ ይሆናል። *

ይሁን እንጂ ተፈጥሮ ስለ አምላክ ሊያስተምረን የሚችለው ነገር ውስን ነው። አምላክ መኖሩን የሚያሳየውን በተፈጥሮ ውስጥ የሚታይ ማስረጃ መመርመር ቤት ውስጥ ሆነህ ከደጅ የሚመጣን ሰው ኮቴ ከመስማት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አንድ ሰው እየመጣ እንደሆነ ብትገነዘብም ማንነቱን ግን አታውቅም። የግለሰቡን ማንነት ለማወቅ በሩን መክፈት ያስፈልግሃል። እኛም ከተፈጥሮ በስተጀርባ ያለውን አካል ለይተን ለማወቅ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ያስፈልገናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ እውቀት ለማግኘት እንደሚያስችል በር ነው። ይህንን በር ከፍተህ በውስጡ የሰፈሩትን ዝርዝር ሐሳብ የያዙ ትንቢቶችና ፍጻሜያቸውን ስትመረምር አምላክ እንዳለ የሚጠቁም ማስረጃ ታገኛለህ። * አምላክ ከሰዎች ጋር ስለነበረው ግንኙነት የሚገልጸው ዘገባ ደግሞ ጸሎት ሰሚ የሆነው አካል ስላሉት ባሕርያት ይበልጥ ለማወቅ ያስችልሃል።

ጸሎትን የሚሰማው አካል ምን ዓይነት አምላክ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጸሎትን የሚሰማው አምላክ የራሱ ማንነት እንዳለውና ስለ እሱ ማወቅ እንደምትችል ይናገራል። በእርግጥም የምናቀርበውን ጸሎት ማዳመጥና መረዳት የሚችለው የራሱ ማንነት ያለው አካል ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ጸሎትን የምትሰማ ሆይ፤ የሰው ልጆች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ” የሚል የሚያበረታታ ሐሳብ ይዟል። (መዝሙር 65:2) አምላክ በእምነት ወደ እሱ የሚጸልዩትን ሰዎች ይሰማል። ደግሞም ስም አለው። መጽሐፍ ቅዱስ “[“ይሖዋ፣” NW] ከክፉዎች ሩቅ ነው፤ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል” ይላል።​—ምሳሌ 15:29

ይሖዋ፣ ስሜት ያለው አምላክ ነው። ‘የፍቅር አምላክ’ ሲሆን “ደስተኛ [የሆነ] አምላክ” ተብሎም ተጠርቷል። (2 ቆሮንቶስ 13:11፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:11) ክፋት እጅግ ተስፋፍቶ በነበረበት ወቅት አምላክ ምን እንደተሰማው መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ “ልቡም እጅግ አዘነ” ይላል። (ዘፍጥረት 6:5, 6) አምላክ ሰዎችን ለመፈተን ብሎ መከራና ሥቃይ እንደሚያመጣ የሚገልጸው ትምህርት ሐሰት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር ዘንድ፣ . . . ይራቅ” ይላል። (ኢዮብ 34:10) ይሁንና ‘አምላክ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ ከሆነ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስብህ ይሆናል።

ይሖዋ፣ ለሰው ልጆች በመምረጥ ነፃነታቸው የመጠቀም ችሎታ ሰጥቷቸዋል፤ ይህም ስለ አምላክ ባሕርይ የሚነግረን ነገር አለ። ሕይወታችንን የምንመራበትን መንገድ የመምረጥ ነፃነታችን ከፍ አድርገን የምንመለከተው ነገር አይደለም? የሚያሳዝነው ግን ብዙ ሰዎች የመምረጥ ነፃነታቸውን አላግባብ የሚጠቀሙበት ሲሆን ይህ ደግሞ በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ መከራና ሥቃይ ያስከትላል። ከዚህ አንጻር ‘አምላክ የሰው ልጆችን ነፃነት ሳይጋፋ መከራና ሥቃይን ማስወገድ የሚችለው እንዴት ነው?’ የሚለው ጥያቄ በአንክሮ ሊታሰብበት ይገባል። የዚህን ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 አምላክ መኖሩን የሚያረጋግጡ ተጨማሪ ማስረጃዎች ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን የሕይወት አመጣጥ​መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተሰኘውን ብሮሹርና ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተሰኘውን መጽሐፍ ተመልከት።

^ አን.10 የይሖዋ ምሥክሮች፣ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ለማቅረብ ሲሉ ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተሰኘውን ብሮሹርና መጽሐፍ ቅዱስ​የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተሰኘውን መጽሐፍ አዘጋጅተዋል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጥርጣሬ እንዲያድርብህ ያደረገው ሃይማኖት ነው?

የሚያሳዝነው ነገር ብዙዎች ርኅሩኅ የሆነና ጸሎትን የሚሰማ አምላክ መኖሩን እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸው ሃይማኖት ነው። ሃይማኖት እንደ ጦርነትና ሽብርተኝነት ባሉት ድርጊቶች መካፈሉ እንዲሁም በልጆች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በቸልታ መመልከቱ ጸሎተኛ የሆኑ ሰዎችም እንኳ “በአምላክ አላምንም” እንዲሉ አድርጓቸዋል።

ሃይማኖት አብዛኛውን ጊዜ ለመጥፎ ነገሮች መንስኤ የሚሆነው ለምንድን ነው? በአጭሩ፣ መጥፎ ሰዎች በሃይማኖት ስም መጥፎ ነገሮችን ስለሚሠሩ ነው። ክርስትናን መጥፎ ድርጊቶችን ለመፈጸም የሚጠቀሙበት አካላት እንደሚነሱ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ተናግሯል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ከእናንተ ከራሳችሁ መካከል እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ።”​—የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30

አምላክ የሐሰት ሃይማኖትን ይጸየፋል። እንዲያውም የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ‘በምድር ላይ ለታረዱ ሰዎች ሁሉ ደም’ ተጠያቂው የሐሰት ሃይማኖት እንደሆነ ይገልጻል። (ራእይ 18:24) የሐሰት ሃይማኖቶች፣ ፍቅር ስለሆነው እውነተኛ አምላክ ሰዎችን ሳያስተምሩ በመቅረታቸው በአምላክ ፊት በደም ዕዳ ተጠያቂ ናቸው።​—1 ዮሐንስ 4:8

ጸሎትን የሚሰማው አምላክ ጨቋኝ በሆኑ ሃይማኖቶች ግፍ ለደረሰባቸው ሰዎች ያዝናል። አምላክ ለሰው ዘር ያለው ፍቅር፣ ግብዝ በሆኑ ሃይማኖቶች ሁሉ ላይ በኢየሱስ አማካኝነት በቅርቡ የፍርድ እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳዋል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያ ቀን ብዙዎች እንዲህ ይሉኛል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? . . .’ እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ!’ እላቸዋለሁ።”​—ማቴዎስ 7:22, 23