ጸሎት ሰሚ ወደሆነው አምላክ ቅረብ
ጸሎት ሰሚ ወደሆነው አምላክ ቅረብ
በአምላክ እንደሚያምኑ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች ለሚያምኑበት ነገር አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም። ሃይማኖት ብዙውን ጊዜ ለመጥፎ ነገሮች ምክንያት የሚሆነው ወይም አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ማብራራትም አይችሉም። የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ማንነቱን ወደማያውቁት አምላክ መጸለይ ብቻ ነው።
አንተ ግን ከዚህ ባለፈ ወደ አምላክ መቅረብ ትችላለህ። ስለ አምላክ በማወቅ እምነትህን መገንባት ትችላለህ፤ ስለ አምላክ ማወቅህ እሱን እንድትወደውና እንድታከብረው ያደርግሃል። እውነተኛ እምነት በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ነው። (ዕብራውያን 11:1) ስለ አምላክ እውነቱን ከተማርህ እሱን ልታውቀውና ልክ እንደ ወዳጅህ ልታነጋግረው ትችላለህ። ከዚህ ቀጥሎ፣ አምላክ ስለ መኖሩ ጥርጣሬ ቢኖራቸውም ወደ እሱ ይጸልዩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎችን ተሞክሮዎች እንመለከታለን።
▪ በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ፓትሪሻ። “አንድ ቀን አሥር ከሚሆኑ ጓደኞቼ ጋር እያለሁ ስለ ሃይማኖት ውይይት ተጀመረ። ከዚያ በፊት፣ በአምላክ መኖር የማያምነው አባቴና ቤታችን የመጣች አንዲት የይሖዋ ምሥክር ሲወያዩ ቤቱን ጥዬ እንደወጣሁ ለጓደኞቼ ነግሬያቸው ነበር። ከጓደኞቼ አንዱ ‘የይሖዋ ምሥክሮች ትክክል ሳይሆኑ አይቀሩም’ አለ።
“ሌላዋ ጓደኛዬ ደግሞ ‘ታዲያ ለምን ወደ ስብሰባቸው ሄደን ምን እንደሚሉ አንሰማም?’ አለች። ስለዚህ እንደተባባልነው አደረግን። በዚያ ስለሰማነው ነገር ጥርጣሬ የነበረን ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ስለተቀበሉን አንዳንዶቻችን በስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘታችንን ቀጠልን።
“አንድ እሁድ ቀን የሰማሁት ነገር አመለካከቴን ለወጠው። ተናጋሪው፣ ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው ለምን እንደሆነ አብራራ። ሰው መጀመሪያ ሲፈጠር ፍጹም እንደነበረ እንዲሁም ኃጢአትና ሞት የመጣው በአንድ ሰው የተነሳ እንደሆነና ከዚያም ወደ ሰው ሁሉ እንደተዳረሰ ከዚያ በፊት ፈጽሞ ሰምቼ አላውቅም ነበር። በተጨማሪም ተናጋሪው፣ የመጀመሪያው ሰው ያጣውን ነገር የሰው ዘር መልሶ እንዲያገኝ የኢየሱስ ሞት አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት አብራራ። * (ሮም 5:12, 18, 19) በድንገት ሁሉም ነገር ግልጽ ሆነልኝ። ‘ለካስ ከልብ የሚያስብልን አምላክ አለ’ ብዬ አሰብኩ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን ቀጠልኩ፤ ብዙም ሳይቆይ፣ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እውን ወደሆነ አካል መጸለይ እንደምችል ተገነዘብኩ።”
▪ በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው አለን። “አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን ሲመጡ ባለቤቴ እንዲገቡ ጋበዘቻቸው፤ በምድር ላይ ለዘላለም ስለመኖር የተናገሩት
ነገር ትኩረቷን ስቦት ነበር። እኔ ግን ተበሳጨሁ። ስለዚህ እነሱን በተቀመጡበት ትቻቸው ባለቤቴን ወደ ኩሽና ወሰድኳትና ‘አትሞኚ፤ እንዲህ ዓይነቱን ነገር ማመን የለብሽም!’ አልኳት።“‘ታዲያ እንዲህ ካልክ ስህተት መሆናቸውን ለምን ሄደህ አታሳያቸውም?’ ብላ መለሰችልኝ።
“ሆኖም መሳሳታቸውን ማሳየት አልቻልኩም። እነሱ ግን በደግነት ያነጋገሩኝ ሲሆን ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ይሁን በዝግመተ ለውጥ የሚያብራራ መጽሐፍ ትተውልኝ ሄዱ። መጽሐፉ ላይ የቀረበው ሐሳብ በጣም ግልጽና በማስረጃ የተደገፈ ስለነበረ ስለ አምላክ ይበልጥ ለማወቅ አነሳሳኝ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ፤ ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር ቀደም ሲል ስለ ሃይማኖት ከነበረኝ አመለካከት ፍጹም የተለየ እንደሆነ አስተዋልኩ። ስለ ይሖዋ እየተማርኩ ስሄድ የምፈልገውን ነገር ለይቼ በመጥቀስ ወደ እሱ መጸለይ ጀመርኩ። ስለ አንዳንድ ነገሮች የነበረኝ አመለካከት ትክክል ስላልነበረ አምላክ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። ይሖዋም ጸሎቴን ሰምቶ ምላሽ እንደሰጠኝ ይሰማኛል።”
▪ በእንግሊዝ የሚኖረው አንድሩ። “በሌሎች ጉዳዮች ረገድ የራሴ አቋም ያለኝና ስለ ሳይንስ የማወቅ ጉጉት የነበረኝ ሰው ነኝ፤ ያም ሆኖ የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ የተቀበልኩት ሰዎች ትክክል እንደሆነ ስለነገሩኝ ብቻ ነበር።
የማያቸው በርካታ መጥፎ ነገሮች በአምላክ ማመኔን እንድተው አድርገውኝ ነበር።“ሆኖም አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ብዬ አስብ ነበር፦ ‘በእርግጥ አምላክ ካለ የሕይወት ትርጉም ምንድን ነው? ወንጀልና ጦርነት ይህን ያህል የበዛው ለምንድን ነው?’ እርግጥ ነው፣ ችግር ሲገጥመኝ እርዳታ ለማግኘት አንዳንድ ጊዜ እጸልይ ነበር፤ ሆኖም ጸሎቴን የማቀርበው ለማን እንደሆነ አላውቅም።
“በዚህ መሃል አንድ ሰው፣ ይህ ዓለም ከጥፋት ይተርፍ ይሆን? የሚል ርዕስ ያለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ትራክት ለባለቤቴ ሰጣት። የትራክቱ ርዕስ ብዙ ጊዜ የሚያሳስበኝን ጥያቄ የያዘ ነበር። ትራክቱ ‘መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸውን መልሶች መመርመር ይኖርብኝ ይሆን?’ ብዬ እንዳስብ አደረገኝ። በሌላ ጊዜ ደግሞ እረፍት ላይ ሳለሁ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? * የሚለውን መጽሐፍ ሰጠኝ። መጽሐፍ ቅዱስ ከእውነተኛ ሳይንስ ጋር እንደሚስማማ ስገነዘብ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ እንደሚያስፈልገኝ ተሰማኝ። ስለዚህ አንድ የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስን ከእሱ ጋር እንዳጠና ሲጋብዘኝ ተስማማሁ። የይሖዋን ዓላማ እየተረዳሁ ስመጣ አምላክን እንደ አንድ እውን አካል አድርጌ እመለከተው ጀመር፤ በጸሎት ሐሳቤን በነፃነት ልገልጽለት እንደምችል ተሰማኝ።”
▪ በለንደን የምትኖረውና ከልጅነቷ ጀምሮ ፕሮቴስታንት የነበረችው ጃን። “በሃይማኖት ውስጥ ያለው ግብዝነትና በዓለም ላይ መከራና ሥቃይ መብዛቱ ሃይማኖትን እርግፍ አድርጌ እንድተው አደረገኝ። የኮሌጅ ትምህርቴንም ያቋረጥኩ ሲሆን ገንዘብ ለማግኘት መዝፈንና ጊታር መጫወት ጀመርኩ። ከፓት ጋር የተገናኘሁት በዚህ ጊዜ ነበር። ፓት በካቶሊክ ሃይማኖት ውስጥ ያደገ ሲሆን እንደ እኔው ሃይማኖት የለሽ ሆኖ ነበር።
“እኔና ፓት፣ እንደ እኛው ትምህርታቸውን ካቋረጡና ስለ ምሥራቃውያን ሃይማኖቶች የማወቅ ጉጉት ከነበራቸው ሌሎች ብዙዎች ጋር ሆነን ወና በተተዉ ቤቶች ውስጥ መኖር ጀመርን። ማታ ማታ ስለ ሕይወት ትርጉም የጦፈ ውይይት ስናደርግ እናመሽ ነበር። እኔና ፓት በአምላክ ባናምንም ሕይወትን የፈጠረ የሆነ ‘ኃይል’ እንዳለ እናስብ ነበር።
“በሙዚቀኝነት መስክ ሥራ ለማግኘት ወደ ሰሜናዊ እንግሊዝ ከሄድን በኋላ ልጃችን ተወለደ። አንድ ምሽት ልጃችን በመታመሙ፣ በአምላክ ባላምንም እንኳ ወደ እሱ ጸለይኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እኔና ፓት ግንኙነታችን እየሻከረ ስለሄደ ልጃችንን ይዤ ከቤት ወጣሁ። በዚህ ጊዜም ምናልባት የሚሰማኝ አካል ሊኖር ይችላል ብዬ በማሰብ እርዳታ ለማግኘት እንደገና ጸለይኩ። በወቅቱ እኔ ባላውቀውም ፓትም ጸልዮ ነበር።
“በዚያኑ ዕለት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ፓት ቤት የመጡ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከያዛቸው ጠቃሚ ምክሮች አንዳንዶቹን አሳዩት። ፓት ስልክ ደወለልኝና መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አብሬው ለማጥናት ፈቃደኛ መሆኔን ጠየቀኝ። ብዙም ሳይቆይ፣ አምላክን ለማስደሰት ከፈለግን ጋብቻችንን ሕጋዊ ማድረግ እንዳለብን ተማርን። ግንኙነታችን ቋፍ ላይ ደርሶ ስለነበር ጋብቻችንን ሕጋዊ ማድረግ በጣም ከባድ እንደሆነ ተሰምቶን ነበር።
“ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ፣ መከራና ሥቃይ ስለመጣበት ምክንያት እንዲሁም ስለ አምላክ መንግሥት ምንነት ይበልጥ ለማወቅ ፈለግን። ቀስ በቀስ አምላክ ለሰዎች እንደሚያስብ የተገነዘብን ሲሆን ይህም እሱ የሚለውን እንድናደርግ አነሳሳን። በዚህም ምክንያት ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተጋባን። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ሦስቱን ልጆቻችንን በማሳደግ ረገድ ረድቶናል። በእርግጥም ይሖዋ ጸሎታችንን እንደመለሰልን ይሰማናል።”
ማስረጃውን ራስህ መርምር
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች እንዳደረጉት ሁሉ በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎችም የሐሰት ሃይማኖት አታላይ መሆኑን የተገነዘቡ ሲሆን አምላክ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነም መርምረው አውቀዋል። እነዚህ ግለሰቦች በሙሉ ይሖዋ የሚቀርቡለትን ጸሎቶች በእርግጥ እንደሚመልስ ያሳመናቸው መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል መረዳት መቻላቸው እንደሆነ ልብ ብለሃል?
አንተስ አምላክ መኖሩን የሚያረጋግጠውን ማስረጃ መመርመር ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ይሖዋ እንዲሁም ‘ጸሎት ሰሚ’ ወደሆነው ወደዚህ አምላክ መቅረብ ስለምትችልበት መንገድ እውነቱን እንድትማር ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።—መዝሙር 65:2
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.6 የኢየሱስ ሞት፣ ቤዛ የሚሆነው እንዴት እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ተመልከት።
^ አን.12 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“የይሖዋን ዓላማ እየተረዳሁ ስመጣ አምላክን እንደ አንድ እውን አካል አድርጌ እመለከተው ጀመር፤ በጸሎት ሐሳቤን በነፃነት ልገልጽለት እንደምችል ተሰማኝ”
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ እምነት ለማዳበር ማስረጃውን ልንመረምርና ስለ አምላክ እውነቱን የማወቅ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል