በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት​—ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት​—ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት​—ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ያስደስታቸዋል። አንተስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተያያዘ ግራ የሚያጋባህ ጥያቄ አለ? የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ወይም ስለ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስትገናኝ ጥያቄህን ከማቅረብ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከአንተ ጋር መወያየት ያስደስታቸዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ምን ዓይነት ውይይት እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ምሳሌ ከዚህ በታች ቀርቧል። ማርቆስ የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት እየሄደ ሲሰብክ ሮቤል የሚባል ሰው እንዳገኘ አድርገን እናስብ።

ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች እዚያ ሄደው ምን ያከናውናሉ?

ማርቆስ፦ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ስታስብ ሁኔታዎች የሚሻሻሉ ይመስልሃል? ወይስ እንደሚባባሱ አለዚያም በዚሁ እንደሚቀጥሉ ይሰማሃል?

ሮቤል፦ ሁኔታዎች እንደሚሻሻሉ ይሰማኛል። ከጌታ ጋር ለመሆን ወደ ሰማይ የምሄድበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቅሁ ነው።

ማርቆስ፦ ይህ ግሩም ተስፋ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ ስላለው ሕይወት እንዲሁም ወደዚያ የመሄድ መብት ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ይናገራል። ይሁንና ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች እዚያ ምን እንደሚሠሩ አስበህበት ታውቃለህ?

ሮቤል፦ ከአምላክ ጋር እንሆናለን፤ እንዲሁም እሱን ለዘላለም እናወድሰዋለን።

ማርቆስ፦ ይህ በእርግጥም የሚያስደስት ተስፋ ነው። የሚገርምህ ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ስለሚያገኙት መብት ብቻ ሳይሆን ስለሚኖራቸው ትልቅ ኃላፊነትም ጭምር ይናገራል።

ሮቤል፦ ምን ዓይነት ኃላፊነት?

ማርቆስ፦ ራእይ 5:10 ስለዚህ ኃላፊነት ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “[ኢየሱስ] ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት እንዲሆኑ [አድርጓቸዋል]፤ በምድርም ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ።” ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ምን ዓይነት ኃላፊነት እንደሚኖራቸው አስተዋልክ ሮቤል?

ሮቤል፦ ጥቅሱ በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው እንደሚገዙ ይናገራል።

ማርቆስ፦ ይሄ ራሱ ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ነው፤ አይደል?

የሚገዙት እነማንን ነው?

ማርቆስ፦ ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ነገሥታት ሆነው የሚገዙ ከሆነ ተገዢዎች መኖር ያለባቸው አይመስልህም? ደግሞስ ተገዢዎች የሌሉት መንግሥት ሊኖር ይችላል?

ሮቤል፦ አሃ፣ እውነትህን ነው፤ ተገዢ ያስፈልጋል።

ማርቆስ፦ ታዲያ ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች የሚገዙት እነማንን ይመስልሃል?

ሮቤል፦ ገና ሞተው ወደ ሰማይ ያልሄዱትን በምድር ላይ ያሉ ሰዎች ይመስለኛል።

ማርቆስ፦ ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ የሚሄዱ ከሆነ አሁን ያልከው ነገር ምክንያታዊ ይመስላል። እስቲ ጉዳዩን ከሌላም አቅጣጫ እንመልከተው። ወደ ሰማይ የማይሄዱ ጥሩ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉስ አስበህ ታውቃለህ?

ሮቤል፦ እንዲህ ብሎ የሚያምን ክርስቲያን አለ እንዴ?

ማርቆስ፦ ጥያቄውን እንዳነሳ ያደረገኝ በመዝሙር 37:29 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ነው። እባክህ ይህን ጥቅስ አንብበው።

ሮቤል፦ እሺ፤ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል።

ማርቆስ፦ አመሰግናለሁ። በዚህ ጥቅስ መሠረት፣ አብዛኞቹ ጥሩ ሰዎች የት የሚኖሩ ይመስልሃል?

ሮቤል፦ ጥቅሱ በምድር ላይ እንደሚኖሩ ይናገራል።

ማርቆስ፦ ልክ ነህ፤ ደግሞም በምድር ላይ የሚኖሩት ለአጭር ጊዜ ብቻ አይደለም። ጥቅሱ “በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” እንደሚል ልብ በል።

ሮቤል፦ ግን እኮ ይህ ጥቅስ በምድር ላይ ምንጊዜም ጥሩ ሰዎች እንደሚኖሩ የሚያመለክት ሊሆን አይችልም? እኛ ሞተን ወደ ሰማይ ስንሄድ ሌሎች ጥሩ ሰዎች መወለዳቸው አይቀርም።

ማርቆስ፦ ብዙ ሰዎች ጥቅሱን በዚህ መንገድ ይረዱት ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ጥቅስ እየተናገረ ያለው ስለ ሌላ ሐሳብ ሊሆን አይችልም? ጥሩ ሰዎች ወደ ሰማይ ሲሄዱ በሌሎች እንደሚተኩ ሳይሆን እነሱ ራሳቸው ለዘላለም በምድር ላይ እንደሚኖሩ የሚያመለክት ይሆን?

ሮቤል፦ እኔ እንጃ፣ ምን ለማለት እንደፈለግህ አልገባኝም።

ወደፊት ምድር ገነት ትሆናለች

ማርቆስ፦ ወደፊት በምድር ላይ ስለሚኖረው ሕይወት መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማየት እስቲ ሌላ ጥቅስ እንመልከት። ራእይ 21:4 በዚያ ዘመን ስለሚኖረው ሕይወት ሲናገር “እሱም [አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል” ይላል። ይህ ተስፋ አስደሳች አይደለም?

ሮቤል፦ አዎ፣ በጣም ደስ ይላል። ይሁን እንጂ ይህ ጥቅስ የሚናገረው በሰማይ ስለሚኖረው ሕይወት አይደለም እንዴ?

ማርቆስ፦ በእርግጥ ወደ ሰማይ የሚሄዱትም ተመሳሳይ በረከቶችን ያገኛሉ። ሆኖም ጥቅሱን እስቲ እንደገና ተመልከተው። ሞትን በተመለከተ ምን እንደሚል አስተውለሃል?

ሮቤል፦ ጥቅሱ “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም” ይላል።

ማርቆስ፦ ልክ ነህ። አንድ ነገር ‘ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም’ ሊባል የሚችለው ቀድሞ የነበረ ከሆነ ብቻ ነው አይደል?

ሮቤል፦ እውነት ነው።

ማርቆስ፦ ታዲያ በሰማይ ላይ ሞት ኖሮ ያውቃል? ሰዎች የሚሞቱት እዚህ ምድር ላይ ብቻ አይደል?

ሮቤል፦ እምም፤ ልክ ነህ።

ማርቆስ፦ ስለዚህ ሮቤል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጥሩ ሰዎች ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ቢናገርም ሌሎች ብዙዎች እዚሁ ምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ ያስተምራል። እንዲያውም “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” የሚለውን የታወቀ ጥቅስ ሳትሰማው አትቀርም።—ማቴዎስ 5:5 አ.መ.ት

ሮቤል፦ አዎን፣ ይህ ጥቅስ በቤተ ክርስቲያን ብዙ ጊዜ ሲነበብ ሰምቻለሁ።

ማርቆስ፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የዋሆች ምድርን እንደሚወርሱ መናገሩ ሰዎች በምድር ላይ እንደሚኖሩ አያመለክትም? በምድር ላይ የሚኖሩት ሰዎች ደግሞ በራእይ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሱትን በረከቶች ያገኛሉ። አምላክ ሞትን ጨምሮ መጥፎ ነገሮችን በሙሉ ስለሚያስወግድ በምድር ላይ የሚኖሩት ሰዎች ዓለማችን ሙሉ በሙሉ ስትለወጥ ያያሉ።

ሮቤል፦ አሁን ሐሳብህ እየገባኝ ነው፤ ነገር ግን አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶች ብቻ ላነሳኸው ነጥብ ማስረጃ ይሆናሉ ብዬ አላስብም።

ማርቆስ፦ እውነትህን ነው። ወደፊት በዚህች ምድር ላይ የሚኖረው ሕይወት ምን እንደሚመስል የሚናገሩ በርካታ ጥቅሶች አሉ። እንዲያውም ጥቂት ጊዜ ካለህ አንድ የምወደውን ጥቅስ ላሳይህ እችላለሁ።

ሮቤል፦ እሺ፣ ትንሽ መወያየት እንችላለን።

“ክፉ ሰው አይዘልቅም”

ማርቆስ፦ ቅድም መዝሙር 37 ቁጥር 29⁠ን አንብበን ነበር። እስቲ አሁንም ወደዚያው መዝሙር እንመለስና ቁጥር 10 እና 11⁠ን እናንብብ። እነዚህን ቁጥሮች ልታነባቸው ትችላለህ?

ሮቤል፦ እሺ፤ “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ። በታላቅ ሰላምም ሐሴት ያደርጋሉ።”

ማርቆስ፦ አመሰግናለሁ። ቁጥር 11 ላይ “ገሮች” ወይም ጥሩ ሰዎች የት ይኖራሉ ይላል?

ሮቤል፦ “ምድርን ይወርሳሉ” ይላል። ይሁን እንጂ ይህ ጥቅስ የሚያመለክተው የወደፊቱን ጊዜ ሳይሆን አሁን ያለውን ሁኔታ ይመስለኛል፤ ጥሩ ሰዎች ደግሞ በዛሬው ጊዜም በምድር ላይ አሉ።

ማርቆስ፦ እውነትህን ነው። ይሁን እንጂ ጥቅሱ፣ ጥሩ ሰዎች “በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” እንደሚልም ልብ በል። በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ሙሉ በሙሉ ሰላም ሰፍኗል ማለት እንችላለን?

ሮቤል፦ አይ፣ አንችልም።

ማርቆስ፦ ታዲያ ይህ ተስፋ የሚፈጸመው እንዴት ነው? እስቲ ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር፦ የምታከራየው ሕንፃ አለህ እንበል። አንዳንዶቹ ተከራዮች ጥሩ ሰዎች ናቸው፤ የተከራዩትን ቤት በአግባቡ ይይዛሉ፤ እንዲሁም ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላም ለመኖር ይጥራሉ። ሕንፃውን እንደነዚህ ላሉት ሰዎች በማከራየትህ ደስተኛ ነህ። ሌሎቹ ተከራዮች ግን መጥፎ ሰዎች ናቸው፤ ንብረትህን የሚያበላሹ ከመሆኑም ሌላ ጎረቤቶቻቸውን ሰላም ነስተዋቸዋል። እነዚህ መጥፎ ተከራዮች ባሕርያቸውን ለማሻሻል እምቢተኞች ከሆኑ ምን ታደርጋለህ?

ሮቤል፦ ከቤቴ አስወጣቸዋለሁ።

ማርቆስ፦ አምላክም በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ባሉት መጥፎ ሰዎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳል። እስቲ ቁጥር 10⁠ን እንደገና እንመልከተው። “ክፉ ሰው አይዘልቅም” ይላል። አምላክ በሌሎች ላይ ችግር የሚፈጥሩትን ሰዎች “ያስወጣቸዋል” ማለትም ያጠፋቸዋል። ከዚያም ጥሩ ሰዎች በምድር ላይ በሰላም መኖር ይችላሉ። ጥሩ ሰዎች ለዘላለም በምድር ላይ እንደሚኖሩ የሚገልጸው ይህ ሐሳብ አንተ ቀደም ሲል ከተማርከው የተለየ ሊሆን እንደሚችል ይገባኛል።

ሮቤል፦ አዎን፣ ቤተ ክርስቲያን ስሄድ እንዲህ ዓይነት ነገር ሰምቼ አላውቅም።

ማርቆስ፦ ደግሞም ቅድም እንዳልከው አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶች ብቻ ላቀረብኩት ሐሳብ በቂ ማስረጃ ሊሆኑ አይችሉም። በእርግጥም ጥሩ ሰዎች ወደፊት ስለሚኖራቸው ሕይወት ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል መመርመር ያስፈልገናል። ይሁን እንጂ እስከ አሁን ካነበብናቸው ጥቅሶች አንጻር አንዳንድ ጥሩ ሰዎች ወደ ሰማይ ቢሄዱም በርካታ ጥሩ ሰዎች እዚሁ ምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩ አይመስልህም?

ሮቤል፦ እሱን እርግጠኛ አይደለሁም። ይሁን እንጂ ያነበብናቸው ጥቅሶች ይህን የሚደግፉ ይመስላሉ። ጉዳዩን በደንብ ባስብበት ደስ ይለኛል።

ማርቆስ፦ ይህን ጉዳይ በጥልቀት ስትመረምር ሌሎች ጥያቄዎችም ወደ አእምሮህ ይመጡ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ቀደም ባሉት ዘመናት የኖሩ ጥሩ ሰዎችስ ምን ይሆናሉ? ሁሉም ወደ ሰማይ ሄደዋል? ካልሆነ ደግሞ የት ናቸው?

ሮቤል፦ ስለዚህ ጉዳይ ማወቅ እፈልጋለሁ።

ማርቆስ፦ ታዲያ ለምን እንዲህ አናደርግም፦ በመጀመሪያ፣ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገሩ አንዳንድ ጥቅሶችን ጽፌ ልስጥህ። * ከዚያም እነዚህን ጥቅሶች አንብበህ ካሰብክባቸው በኋላ ሌላ ጊዜ መጥቼ ልንወያይባቸው እንችላለን። ምን ይመስልሃል?

ሮቤል፦ ጥሩ ሐሳብ ነው፤ አመሰግናለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]