በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታይ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ያደገና በሕግ መስክ ጥሩ ሥራ የነበረው አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር የሆነው ለምንድን ነው? አሸባሪ የነበረ አንድ ሰው የዓመፅ እንቅስቃሴውን ትቶ ወንጌላዊ ለመሆን ያነሳሳው ምንድን ነው? እስቲ እነዚህ ሰዎች የሚሉትን እንስማ።

“ትክክል ወይም ስህተት ስለሆነው ነገር ጥልቅ የሆነ ግንዛቤ አገኘሁ።”​—ሴባስቲያዎ አልቪስ ዡንኬራ

የትውልድ ዘመን፦ 1946

የትውልድ አገር፦ ብራዚል

የኋላ ታሪክ፦ አጥባቂ ካቶሊክ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ቤተሰቦቼ የሚኖሩት ከፒኬቲ ከተማ 6 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኝ ገጠራማ አካባቢ ነበር። ወላጆቼ አነስተኛ እርሻ የነበራቸው ሲሆን መሠረታዊ ፍላጎቶቻችንን የምናሟላው ከዚህ እርሻ በምናገኘው ገቢ ነበር። የምማረው ፒኬቲ በሚገኝ ትምህርት ቤት ስለነበረ ከጊዜ በኋላ አንድ ያረጀ ብስክሌት ገዛሁ፤ ይህም ወደ ከተማ መጓዝ ቀላል እንዲሆንልኝ አድርጓል። በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ድሆች ቢሆኑም ከተማዋ ንጹሕ ከመሆኗም ሌላ በአንጻራዊ ሁኔታ ብዙም ወንጀል አይታይባትም ነበር። አብዛኞቹ የከተማዋ ወንዶች የጦር መሣሪያ በሚያመርት ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው ይሠሩ ነበር።

በትጋት አጠና ስለነበር በአቅራቢያችን ባለ ከተማ በሚገኝ የወታደራዊ አውሮፕላን ምሕንድስና ትምህርት ቤት መግባት ቻልኩ፤ በ1966 ከዚህ ትምህርት ቤት ተመረቅሁ። ቀጥሎም የሕግ ትምህርት ቤት ገብቼ በሕግ ዲግሪ አገኘሁ። ከጊዜ በኋላ የፖሊስ አዛዥ ለመሆን አመለከትሁ። በ1976 መንግሥት ያዘጋጀውን ፈተና ስላለፍኩ ይህን ቦታ አገኘሁ። ሥራዬ አንዳንድ ጊዜ የወኅኒ ቤት አስተዳዳሪ መሆንንም ያካትት ነበር። በዚህ ሥራ ላይ እያለሁ የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ ወደ ወኅኒ ቤቱ እየመጡ በዚያ ላሉት እስረኞች ለመስበክ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ይጠይቁ ነበር። በዚህ ወቅት ለእኔም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ይነግሩኛል። ለአምላክ ከፍተኛ አክብሮት ነበረኝ። አምላክ፣ ይሖዋ የሚባል ስም እንዳለውና ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት እንደምንችል ስገነዘብ በጣም ተገረምኩ።

ቀስ በቀስ በተሰማራሁበት የሕግ መስክ እድገት እያገኘሁ ሄድኩ። በ1981 መንግሥት ያዘጋጀውን ሌላ ፈተና አልፌ ዳኛ ሆንኩ። ከዚያም በ2005 በሳኦ ፓውሎ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆኜ ተሾምኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ከሕግ ትምህርት ቤት ከተመረቅሁ ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመርኩ፤ ይህም በአመለካከቴ ላይ ትልቅ ለውጥ አመጣ። አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነበርኩ። ቀሳውስት የሆኑ ዘመዶች ነበሩኝ፤ እንዲያውም አንደኛው ጳጳስ ነበር። እንዲሁም በሥርዓተ ቁርባን ወቅት ቄሱን አግዘው ነበር። ከቄሱ ስብከት በፊት ከጸሎት መጽሐፉ ላይ የተወሰኑ ክፍሎችን አነብ ነበር። የካቶሊክ እምነት ተከታዮች በሆኑ ቤተሰቦች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የተለመደ ነገር አልነበረም። በመሆኑም እናቴ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንደጀመርኩ ስታውቅ በጣም ተበሳጨች። አእምሮዬን እንድስት ሊያደርገኝ እንደሚችል በመናገር ተስፋ ልታስቆርጠኝ ሞከረች። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ምንም ጉዳት እንደሌለው ስለተሰማኝ በንባቤ ገፋሁበት።

መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ያነሳሳኝ ለማወቅ የነበረኝ ጉጉት ይመስለኛል። ስለ ቀሳውስትና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላላቸው ቦታ የበለጠ ማወቅ ፈልጌ ነበር። የካቶሊክ ሃይማኖት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆናን ለማስወገድ መታገል እንዳለባት ስለሚገልጸው ሊበሬሽን የሚባል ንቅናቄም ማንበብ ጀመርኩ፤ ሆኖም የዚህ ንቅናቄ አራማጆች የሚያቀርቧቸው ነጥቦች የተሳሳቱ ስለነበሩ ሐሳባቸው ምንም ሊገባኝ አልቻለም።

በዚሁ ጊዜ አካባቢ፣ ቡድሂስት የነበረው የጥርስ ሐኪሜ ከሌሎች የተቀበለውን አንድ መጽሐፍ ሰጠኝ። የመጽሐፉ ርዕስ ሰው የተገኘው በፍጥረት ነው ወይስ በዝግመተ ለውጥ? * (እንግሊዝኛ) የሚል ነበር። ይህን መጽሐፍ ዚ ኦሪጅን ኦቭ ስፒሺስ (ሕይወት ያላቸው ነገሮች አመጣጥ) ከተባለው የቻርልስ ዳርዊን መጽሐፍ ጋር እያወዳደርኩ ማንበብ ስለፈለግሁ መጽሐፉን ተቀበልኩት። ሰው የተገኘው በፍጥረት ነው ወይስ በዝግመተ ለውጥ? በተባለው መጽሐፍ ላይ የቀረቡት ነጥቦች በማስረጃ የተደገፉ፣ ምክንያታዊና አሳማኝ ነበሩ። በመሆኑም የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ መሠረት የሌለው እንደሆነ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሆንኩ።

መጽሐፉ ስለ ፍጥረት የሚናገረውን ሐሳብ ማንበቤ የማወቅ ጉጉቴን ስለቀሰቀሰው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ተጨማሪ መጻሕፍትን ለማግኘት ፈለግሁ። በዚህ መሃል፣ የይሖዋ ምሥክር ስለሆነ አንድ መካኒክ ሰማሁ። ይህን ሰው ሄጄ ሳናግረው አንዳንድ መጻሕፍት ሰጠኝ። በወቅቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና የቀረበልኝን ግብዣ ለመቀበል ግን ፈቃደኛ አልነበርኩም። መጽሐፍ ቅዱስን በራሴ ላጠናው እንደምችል ተሰምቶኝ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ስጀምር ትዳር መሥርቼ ስለነበር ከቤተሰቤ ጋር ማንበቡ ጥሩ እንደሆነ ተሰማኝ። በየሳምንቱ የቤተሰብ ጥናት የምናደርግ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን አብረን እናነብብ ነበር። ካቶሊኮች እንደመሆናችን መጠን ቀሳውስትና ጳጳሳት በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበራቸው። በመሆኑም በ⁠ዮሐንስ 14:6 ላይ የሚገኘው የሚከተለው ሐሳብ ትኩረቴን ሳበው፦ “ኢየሱስም [ለደቀ መዝሙሩ ቶማስ] እንዲህ አለው፦ ‘እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።’” በዚህ ጉዳይ ላይ ጥልቀት ያለው ምርምር ካደረግሁ በኋላ መዳን የምናገኘው በኢየሱስ በኩል ከይሖዋ እንደሆነ ተገነዘብኩ። ከዚህ ቀደም ግን መዳን ማግኘት የምንችለው በቀሳውስት በኩል እንደሆነ ተምረን ነበር።

ስለ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና ስለምታስተምረው ትምህርት ያለኝን አመለካከት እንድቀይር ያደረጉኝ ሌሎች ሁለት ጥቅሶችም ነበሩ። አንደኛው ጥቅስ ምሳሌ 1:7 ሲሆን “እግዚአብሔርን መፍራት የዕውቀት መጀመሪያ ነው፤ ተላሎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ” ይላል። ሌላው ደግሞ በ⁠ያዕቆብ 1:5 ላይ የሚገኘው የሚከተለው ጥቅስ ነው፦ “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ ምክንያቱም አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣል፤ ለእሱም ይሰጠዋል።” እውቀትና ጥበብ የማግኘት ከፍተኛ ጥማት ነበረኝ፤ ይሁንና ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ይህን ጥማቴን ማርካት አልቻልኩም። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን መሄድ አቆምኩ።

በ1980 ባለቤቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ቤት በምሆንበት ጊዜ በጥናቱ ላይ እገኝ ነበር። ውሎ አድሮ እኔም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማሁ። ያም ቢሆን ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክሮች ለመሆን ረጅም ጊዜ ፈጅቶብናል። በመጨረሻም ባለቤቴ በ1994 እኔ ደግሞ በ1998 ተጠመቅን።

ያገኘሁት ጥቅም፦ አራቱን ልጆቻችንን ያሳደግናቸው ይሖዋ ባወጣቸው መመሪያዎች ኮትኩተን ሲሆን ይህም ጠቅሟቸዋል። (ኤፌሶን 6:4) ሁለቱ ወንዶች ልጆቻችን በየጉባኤዎቻቸው ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ተግተው ይሠራሉ። ሁለቱ ሴቶች ልጆቻችን ደግሞ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት እየተካፈሉ ነው። ባለቤቴ፣ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያውቁ በመርዳት በየወሩ በርካታ ሰዓታት ታሳልፋለች፤ እኔም በአካባቢዬ በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ አገለግላለሁ።

የይሖዋ ምሥክር ስሆን፣ ትክክል ወይም ስህተት ስለሆነው ነገር ጥልቅ የሆነ ግንዛቤ አገኘሁ። በዳኝነት ሥራዬ ላይ ከአንድ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን በሙሉ ከግምት ለማስገባት፣ ምክንያታዊ ለመሆን እንዲሁም የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች በሚኖሩበት ጊዜ ርኅራኄ ለማሳየት ጥረት አደርጋለሁ፤ በዚህ መንገድ ይሖዋ የተለያዩ ጉዳዮችን የሚይዝበትን መንገድ ለመከተል እሞክራለሁ።

ከዓመፅ፣ ከወንጀል፣ ልጆችን ከመበደልና ከሌሎች ከባድ የወንጀል ድርጊቶች ጋር የተያያዙ የፍርድ ጉዳዮችን ተመልክቻለሁ። ሆኖም እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን በተደጋጋሚ መስማቴ ልቤ እንዲደነድን አላደረገም። ዜና በምመለከትበት ወቅት በዓለም ላይ የሚታየው የሥነ ምግባር ብልሹነትና ዝቅጠት ይዘገንነኛል። ወንጀል የተስፋፋበትን ምክንያት ማወቅ ስላስቻለኝና የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጽ ተስፋ ስለሰጠን ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።

‘ወኅኒ ቤት መግባቴ ጠባዬ እንዲታረም አላደረገም።’​—ኪት ዉድዝ

የትውልድ ዘመን፦ 1961

የትውልድ አገር፦ ሰሜን አየርላንድ

የኋላ ታሪክ፦ አሸባሪ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ በ1961 በሰሜን አየርላንድ በምትገኘው ፖርትዳውን የተባለች ሞቅ ያለች ከተማ ውስጥ ተወለድኩ። ቤተሰቦቼ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ሲሆኑ ያደግሁት ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች በኅብረት የሚኖሩባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሚገኙበት አካባቢ ነው። አብዛኞቹ ቤተሰቦች በአንጻራዊ ሁኔታ ድሆች ነበሩ። ከአካባቢያችን ነዋሪዎች ጋር በጣም ስለምንቀራረብ የጎረቤቶቻችን ቤት እንደ ራሳችን ቤት ነበር።

የነበረኝ አኗኗር አሁን ሳስበው የምኮራበት ዓይነት አይደለም። በ1974 በሰሜን አየርላንድ በነበረው “ትራብልስ” ተብሎ በሚታወቀው ፖለቲካዊና የእርስ በርስ ግጭት መካፈል ጀመርኩ። በዚሁ ጊዜ በአካባቢያችን ሁኔታዎች አስከፊ እየሆኑ መጡ። ለምሳሌ ያህል፣ የኧልስተር * ምንጣፍ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ የነበረው አባቴ አንድ ምሽት ላይ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑ ሁለት የጎረቤታችንን ልጆች በሥራ ቦታው እያሠለጠናቸው ነበር። በዚህ መሃል አንድ ሰው እነዚህ ወጣቶች ወደሚኖሩበት ቤት ቦምብ በመወርወሩ አባታቸው፣ እናታቸውና ወንድማቸው ተገደሉ።

ሁኔታዎች እየተጋጋሉ በመምጣታቸው በመጨረሻ ጦርነት ተነሳ። የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ባሉበት አካባቢ የሚኖሩ ፕሮቴስታንቶች ቤታቸው በመቃጠሉ አካባቢውን ትተው ለመሄድ ተገደዱ፤ ፕሮቴስታንቶች በሚኖሩበት አካባቢ ያሉ ካቶሊኮችም ጥቃት ይሰነዘርባቸው ነበር። እኛ የምንኖርበት አካባቢ የፕሮቴስታንቶች ሰፈር ሆነ። እኔም ቦምብ ከሚያፈነዱት ሰዎች ጋር በመተባበሬ ብዙም ሳይቆይ ተያዝኩና የሦስት ዓመት እስራት ተፈረደብኝ።

በወኅኒ ቤት ሳለሁ ከአንድ እስረኛ ጋር ወዳጅነት መሠረትኩ፤ ይህ ሰው ሰሜን አየርላንድ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር አንድነት እንዲኖራት በሚፈልግ ሎያሊስት የሚባል ፖለቲካዊ ንቅናቄ ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። ከዚህ ሰው ጋር የወንድም ያህል እንቀራረብ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላም በሠርጉ ላይ ሚዜው ነበርኩ። እኔም ሆንኩ እሱ ወኅኒ ቤት መግባታችን ጠባያችን እንዲታረም አላደረገም። ከእስር ቤት ስንፈታ ሁለታችንም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴያችንን ይበልጥ አጠናክረን ቀጠልንበት። በዚህም ምክንያት ጓደኛዬ እንደገና ታሰረ። እዚያም እያለ ሕይወቱ በሰው እጅ ጠፋ።

እኔም የጥቃት ዒላማ ሆንኩ፤ እንዲያውም በአንድ ወቅት መኪናዬን በእሳት አጋዩአት። ይሁንና እነዚህ ክስተቶች በማደርገው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ይበልጥ እንድገፋበት አነሳሱኝ።

በዚሁ ጊዜ ላይ በሰሜን አየርላንድ የነበረውን “ትራብልስ” የተባለ ንቅናቄ በተመለከተ በብሪታንያ ቴሌቪዥን የተላለፈ አንድ ጥናታዊ ፊልም ሲዘጋጅ በሥራው ተካፈልኩ። ይህ ፊልም ሌላ ችግር አስከተለብኝ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ምሽት ወደ ቤቴ ስገባ ባለቤቴ ጥላኝ እንደሄደች ተገነዘብኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በዚሁ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ምክንያት ልጄ ተወሰደብኝ። በእነዚህ ሁኔታዎች የተነሳ በአንድ ወቅት ራሴን በመስተዋት እየተመለከትኩ “አምላክ በእርግጥ ካለህ እርዳኝ” ብዬ እንደተናገርኩ አስታውሳለሁ።

በቀጣዩ ቅዳሜ ፖል ከሚባል የማውቀው ሰው ጋር ተገናኘሁ፤ ፖል የይሖዋ ምሥክር ሆኖ ነበር። ለእኔም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረኝ ጀመር። ከሁለት ቀናት በኋላ ፖል መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላከልኝ። በመጽሔቱ ላይ ያለ አንድ ርዕስ ኢየሱስ በ⁠ዮሐንስ 18:36 ላይ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ይጠቅሳል፦ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም። መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል ቢሆን ኖሮ በአይሁዳውያን እጅ እንዳልወድቅ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር። አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም።” ይህ ጥቅስ በጥልቅ ነካኝ። ሕይወቴ መለወጥ የጀመረው ያን ጊዜ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ከፖል ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። በኋላ ላይ ደግሞ ጥናቴን ቢል ከሚባል የይሖዋ ምሥክር ጋር ቀጠልኩ። በጥናቱ ወቅት አስቸግረው እንደነበር ይሰማኛል፤ የጥያቄ ውርጅብኝ አዥጎደጉድበት ነበር። ከዚህም ሌላ ቢል መሳሳቱን ለማረጋገጥ ስል በርካታ ሃይማኖታዊ አገልጋዮች በጥናቱ ላይ እንዲገኙ አደርግ ነበር። ውሎ አድሮ ግን በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውነት በግልጽ ማስተዋል ጀመርኩ።

በአንድ ወቅት ለቢል ስልክ ደውዬ በምኖርበት አካባቢ መንገዱ እንደተዘጋ እንዲሁም ወደዚያ አካባቢ በመኪና ከመጣ መኪናው መወረሱና መቃጠሉ እንደማይቀር ነገርኩት። ቢል ግን እንደተለመደው ለጥናታችን መጣ። የመጣው መኪናውን ቤት ትቶ በብስክሌት ነበር። ብስክሌቱን ደግሞ ማንም እንደማይወስድበት ግልጽ ነው። በሌላ ጊዜ ደግሞ ከቢል ጋር ቤቴ ውስጥ እያጠናን ሳለ ፖሊሶችና ወታደሮች እኔን ለመያዝ መጡ። ፖሊሶቹ ይዘውኝ ሲሄዱ ቢል ጮክ ብሎ በይሖዋ እንድታመን ነገረኝ። በእነዚህ ወቅቶች ያየሁት ነገር በጥልቅ ነክቶኛል።

በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘሁበት ወቅት አንዳንዶች ሳይደነግጡ አልቀሩም። ፀጉሬን ከማሳደጌና ጉትቻ ከማድረጌም ሌላ የየትኛው ፖለቲካዊ ቡድን አባል እንደሆንኩ የሚጠቁም የቆዳ ጃኬት ለብሼ ነበር። ያም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አቀባበል አደረጉልኝ። ያሳዩኝ ደግነት በጣም አስደነቀኝ።

መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናሁም ቢሆን ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር ያለኝን ግንኙነት አላቋረጥኩም ነበር። ውሎ አድሮ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኳቸው እውነቶች በልቤ ውስጥ ሥር መስደድ ጀመሩ። ይሖዋን ማገልገል ከፈለግሁ ስለ ፖለቲካ ያለኝን አመለካከት መቀየርና የቀድሞ ጓደኞቼን መተው እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ይህን ማድረግ ቀላል አልነበረም። ሆኖም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቄና ከይሖዋ ብርታት ማግኘቴ እነዚህን ለውጦች ለማድረግ አስቻለኝ። ፀጉሬን ተቆረጥኩ፤ ጉትቻ ማድረጌን አቆምኩ እንዲሁም ሙሉ ልብስ ገዛሁ። የምማረው ነገር ለሌሎች የነበረኝን አመለካከትም እንድቀይር ረዳኝ።

ያገኘሁት ጥቅም፦ ከዚህ ቀደም በወንጀልና በሽብርተኝነት ድርጊቶች ተጠላልፌ ነበር። በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉት ሕግ አስከባሪዎች በሚገባ ያውቁኝ ነበር። አሁን ግን ሁኔታዎች ተለውጠዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በናቫን ከተማ በተካሄደው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስገኝ ሕግ አስከባሪ አካላት ችግር እንዳልፈጥር ስለፈሩ ከሰሜን አየርላንድ ወደ አየርላንድ ስሄድም ሆነ ስመለስ አጅበውኝ ነበር። አሁን ግን ወደ አውራጃ ስብሰባዎች ስሄድ ሕግ አስከባሪዎች አይከተሉኝም። ከዚህም ሌላ አሁን፣ የእምነት ባልንጀሮቼ ከሆኑት ከፖልና ከቢል እንዲሁም ከሌሎች የጉባኤው አባላት ጋር በስብከቱ ሥራ ላይ በነፃነት መካፈል ችያለሁ።

ሕይወቴ እየተሻሻለ ሲሄድ የጉባኤው አባል መሆን ቻልኩ። ከዚያም ሉዊዝ የተባለች የይሖዋ ምሥክር አገባሁ። በተጨማሪም ከልጄ ጋር እንደገና ተገናኘሁ።

ሕይወቴን መለስ ብዬ ሳስበው ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ማድረጌ ይቆጨኛል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ በተሳሳተ ዓላማ ተነሳስተው መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ እንደ እኔ ያሉ ሰዎች እንዲለወጡ ብሎም ዓላማና ተስፋ ያለው ሕይወት እንዲመሩ እንደሚረዳቸው በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.12 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።

^ አን.25 ኧልስተር የሰሜን አየርላንድ ሌላ ስም ነው።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እናቴ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንደጀመርኩ ስታውቅ በጣም ተበሳጨች