በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡትን ተአምራት እምነት ልትጥልባቸው ትችላለህ?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡትን ተአምራት እምነት ልትጥልባቸው ትችላለህ?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡትን ተአምራት እምነት ልትጥልባቸው ትችላለህ?

አንድ ሰው አስደናቂ የሆነ ታሪክ ቢነግርህ ግለሰቡ እምነት የሚጣልበት መሆን አለመሆኑ ታሪኩን በማመንህ ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም? ግለሰቡ፣ ታሪኩን የተረከበት መንገድ ብቻ ሳይሆን ከዚያ ቀደም እውነት በመናገር ረገድ ያተረፈው ስምም እሱን እንድታምነው ወይም እንዳታምነው ሊያደርግህ ይችላል። ይህ ግለሰብ እስከ ዛሬ እውነት ብቻ ይነግርህ ከነበረና ሆን ብሎ የተሳሳተ መረጃ ሰጥቶህ የማያውቅ ከሆነ አሁን የነገረህን ታሪክ ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አለህ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡትን ተአምራት በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እነዚህ ተአምራት በተፈጸሙበት ወቅት ማናችንም በሕይወት አልነበርንም። ያም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እምነት የሚጣልባቸውና እውነተኛ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንችላለን። እንዴት? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ስለ ተአምራት የሚናገሩ ዘገባዎች እምነት እንድንጥልባቸው የሚያደርጉ አንዳንድ ነጥቦችን እንመልከት።

ብዙዎቹ ተአምራት የተፈጸሙት በርካታ እማኞች ባሉበት ነው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ተአምራት ሲፈጸሙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተመልክተዋል። (ዘፀአት 14:21-31፤ 19:16-19) እነዚህ ተአምራት የተፈጸሙት ከሕዝብ እይታ ተሰውረው ወይም በድብቅ አልነበረም።

ተአምራቱ የተፈጸሙት በማያደናግርና ግልጽ በሆነ መንገድ ነበር። ተአምራቱን ለመፈጸም ለየት ያሉ ቁሳቁሶችን ወይም ማታለያዎችን መጠቀም አላስፈለገም፤ አሊያም ትኩረት ለመሳብ የሚደረጉ የተጋነኑ ነገሮች አልነበሩም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት አብዛኞቹ ተአምራት የተፈጸሙት ግለሰቦቹ ተአምሩን ከፈጸመው ሰው ጋር በአጋጣሚ በመገናኘታቸውና እርዳታ እንዲደረግላቸው በመጠየቃቸው ነው። (ማርቆስ 5:25-29፤ ሉቃስ 7:11-16) በእነዚህ ወቅቶች ተአምራቱን የፈጸመው ሰው አስቀድሞ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ሊሆን አይችልም።

ተአምራቱን የፈጸሙት ግለሰቦች ዓላማቸው ዝና፣ ክብር እንዲሁም ሀብት ማግኘት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይህን ያደረጉት ለአምላክ ክብር ለማምጣት ነበር። (ዮሐንስ 11:1-4, 15, 40) እንዲያውም በተአምራዊ ክንውኖች አሳብበው ለራሳቸው ሀብት ለማካበት የሞከሩ ግለሰቦች ተወግዘዋል።​—2 ነገሥት 5:15, 16, 20, 25-27፤ የሐዋርያት ሥራ 8:18-23

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት ተአምራት ዓይነታቸው ብዙ መሆኑ በሰው ኃይል ብቻ ሊከናወኑ እንደማይችሉ ይጠቁማል። ለምሳሌ ያህል፣ በማዕበል የሚናወጥ ባሕር ጸጥ ብሏል፤ ውኃ ወደ ወይን ተቀይሯል፤ ዝናብ እንዲጠፋና መዝነብ እንዲጀምር ተደርጓል፤ በሽተኞች ተፈውሰዋል እንዲሁም ዓይነ ስውር የሆኑ ሰዎች ማየት ችለዋል።​—1 ነገሥት 17:1-7፤ 18:41-45፤ ማቴዎስ 8:24-27፤ ሉቃስ 17:11-19፤ ዮሐንስ 2:1-11፤ 9:1-7

ተአምራቱ በተፈጸሙበት ወቅት የነበሩ ተቃዋሚዎች እንኳ ተአምራቱን አልካዱም። ኢየሱስ ወዳጁን አልዓዛርን ከሞት ባስነሳበት ወቅት ተቃዋሚዎቹ የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች አልዓዛር ሞቶ የነበረ መሆኑን አላስተባበሉም። ደግሞስ እንዴት ይህን ማድረግ ይችላሉ? አልዓዛር አራት ቀናት በመቃብር ውስጥ ቆይቷል። (ዮሐንስ 11:45-48፤ 12:9-11) ኢየሱስ ከሞተ ከበርካታ ዘመናት በኋላ እንኳ የአይሁድ ታልሙድ ጸሐፊዎች ኢየሱስ ተአምር የመፈጸም ችሎታ እንደነበረው ያምኑ ነበር። የእነሱ ጥያቄ ‘ይህን ችሎታ ያገኘው ከየት ነው?’ የሚል ነበር። በተመሳሳይም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በአይሁድ ሸንጎ ፊት በቀረቡበት ወቅት “ተአምር ፈጽማችኋል?” የሚል ጥያቄ አልቀረበላቸውም። ከዚህ ይልቅ የተጠየቁት “ይህን ያደረጋችሁት በምን ሥልጣን ወይም በማን ስም ነው?” ተብለው ነው።​—የሐዋርያት ሥራ 4:1-13

ታዲያ ስለ ተአምራት በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ? እስካሁን ከተመለከትነው አንጻር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት ስለ ተአምራት የሚገልጹ ዘገባዎች እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ ግልጽ ነው። እነዚህን ዘገባዎች እንድናምንባቸው የሚያደርጉን ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ተአምር እንደተፈጸመ ሲናገር ጊዜውን፣ ቦታውንና የግለሰቦቹን ስም መጥቀሱ የተለመደ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች እንኳ በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት ዝርዝር የሆኑ ታሪካዊ መረጃዎች ትክክለኝነት ያስደንቃቸዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አንድም ሳይቀር በትክክል ተፈጽመዋል። ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከሰዎች ጋር አስደሳች ግንኙነት ለመመሥረት የሚያስችሉን በርካታ ምክሮችን የያዘ ሲሆን ይህም በየትኛውም የዕድሜ ክልልና በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ጠቅሟቸዋል። ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ተወዳዳሪ የለውም።

አሁንም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሙሉ እምነት መጣል እንደማትችል ከተሰማህ ይህን መጽሐፍ ይበልጥ ለመመርመር ለምን ጊዜ አትመድብም? ይበልጥ ባወቅኸው መጠን ይበልጥ እምነት እየጣልክበት ትሄዳለህ። (ዮሐንስ 17:17) ባለፉት ዘመናት ስለተፈጸሙት ተአምራት በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ እምነት ልትጥል እንደምትችልም ትገነዘባለህ። በእነዚህ ዘገባዎች ላይ እምነት ስታዳብር ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ እንደሚፈጸሙ በሚናገራቸው ተስፋዎች ላይ እምነት ለመጣል የሚያስችል በቂ ምክንያት ይኖርሃል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ ተቃዋሚዎች አልዓዛር ሞቶ የነበረ መሆኑን አላስተባበሉም