በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው ሕይወት​—ዓሣ አጥማጁ

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው ሕይወት​—ዓሣ አጥማጁ

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው ሕይወት​—ዓሣ አጥማጁ

“[ኢየሱስ] በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲሄድ ሁለት ወንድማማቾች ማለትም ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለነበሩ መረባቸውን ወደ ባሕሩ ሲጥሉ አየ። እሱም ‘ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ’ አላቸው።”​—ማቴዎስ 4:18, 19

በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ዓሣ፣ ዓሣ ማጥመድና ዓሣ አጥማጆች ብዙ ጊዜ ተጠቅሰዋል። ኢየሱስ ዓሣ ስለ ማጥመድ የሚጠቅሱ በርካታ ምሳሌዎችን ተናግሯል። ኢየሱስ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው በገሊላ ባሕር ዳርቻ ወይም በአቅራቢያው በማስተማር ስለነበር እንዲህ ማድረጉ ምንም አያስገርምም! (ማቴዎስ 4:13፤ 13:1, 2፤ ማርቆስ 3:7, 8) ውበት የተላበሰው ይህ ጨው አልባ ባሕር 21 ኪሎ ሜትር ገደማ ርዝመትና 11 ኪሎ ሜትር ገደማ ስፋት አለው። ከኢየሱስ ሐዋርያት መካከል ሰባቱ ማለትም ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣ ቶማስና ናትናኤል ዓሣ አጥማጆች ሳይሆኑ አይቀሩም።​—ዮሐንስ 21:2, 3

በኢየሱስ ዘመን የኖሩ ዓሣ አጥማጆች ሕይወት ምን ይመስል ነበር? ስለ እነዚህ ሰዎችና ስለ ሙያቸው ጊዜ ወስደህ እንድታነብብ እንጋብዝሃለን። እንዲህ ማድረግህ ስለ ሐዋርያቱ ያለህን ግንዛቤ ለማስፋት እንዲሁም ኢየሱስ ስላከናወናቸው ነገሮችና ስለተጠቀመባቸው ምሳሌዎች ይበልጥ ለመረዳት ያስችልሃል። እስቲ መጀመሪያ በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ይከናወን የነበረው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

‘በባሕሩ ላይ ኃይለኛ ማዕበል ተነሳ’

የገሊላ ባሕር ያለው በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ሲሆን ከባሕር ጠለል በታች 210 ሜትር ገደማ ላይ ይገኛል። የባሕሩ ዳርቻ ዐለታማ ሲሆን ግርማ ሞገስ የተላበሰው የሄርሞን ተራራ በስተሰሜን በኩል ጉብ ብሎ ይታያል። በቅዝቃዜው ወቅት እንደ አለንጋ የሚጋረፈው ነፋስ አንዳንድ ጊዜ ባሕሩን ያናውጠዋል። አየሩ ሞቃት በሚሆንበት ወቅት ደግሞ ውኃው ይሞቃል። አልፎ አልፎ በአካባቢው ካሉት ተራሮች የሚነሳው ኃይለኛ ወጀብ ከየት መጣ ሳይባል በድንገት ባሕረኞቹ ላይ ዶፉን ያወርደዋል። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ ባለው አየር ሳቢያ ኃይለኛ ማዕበል አጋጥሟቸው ያውቃል።​—ማቴዎስ 8:23-27

ዓሣ አጥማጆቹ 8 ሜትር ገደማ ርዝመትና ከ2 ሜትር በላይ ስፋት ያለው የእንጨት ጀልባ ይጠቀሙ ነበር። በአብዛኞቹ ጀልባዎች ላይ ሸራው የሚወጠርበት ምሰሶ ይኖራል፤ እንዲሁም ከኋላ በኩል ማረፊያ የሚሆን ቦታ አለ። (ማርቆስ 4:35-41) እንዲህ ያለው ጀልባ ፈጣን ባይሆንም ምሰሶው ላይ የተወጠረውን ሸራ የሚገፋውን ነፋስ እንዲሁም ጀልባው ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲያዘነብል የሚያደርገውን የመረቡን ክብደት ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ነበረው።

ዓሣ አጥማጆቹ ጀልባውን የሚያንቀሳቅሱት በጀልባው ጎኖች ላይ ያሉትን መቅዘፊያዎች በመጠቀም ነው። በአንድ ጀልባ ላይ ስድስት ወይም ከዚያ በላይ ዓሣ አጥማጆች ሊኖሩ ይችላሉ። (ማርቆስ 1:20) በተጨማሪም ዓሣ አጥማጆቹ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በጀልባቸው ላይ መያዛቸው አይቀርም፤ ከእነዚህም መካከል ከበፍታ የተሠራ ሸራ (1)፣ ገመድ (2)፣ መቅዘፊያዎች (3)፣ የድንጋይ መልሕቅ (4)፣ ሙቀት የሚሰጡ ደረቅ ልብሶች (5)፣ ምግብ (ማርቆስ 8:14) (6)፣ ቅርጫቶች (7)፣ ትራስ (ማርቆስ 4:38) (8) እንዲሁም መረብ (9) ይገኙበታል። ከዚህም ሌላ ትርፍ ማንሳፈፊያዎች (10)፣ ማስመጫዎች (11)፣ የጥገና ቁሳቁሶች (12) እንዲሁም ችቦ (13) ይይዙ ይሆናል።

“እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ”

በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም በገሊላ ባሕር ላይ ብዙ ዓሦች የሚገኙት የባሕሩ ገባር የሆኑት በርካታ ምንጮችና ወንዞች ወደ ባሕሩ በሚገቡበት ቦታ አካባቢ ነው። እዚህ አካባቢ ዕፅዋት ወደ ባሕሩ ስለሚገቡ ዓሦቹ እነሱን ፍለጋ ይመጣሉ። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ዓሣ አጥማጆች ዓሦች ለማግኘት ብዙውን ጊዜ ችቦ ይዘው በሌሊት ይሠሩ ነበር። በአንድ ወቅት ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶቹ ሌሊቱን ሙሉ ለማጥመድ ሲሞክሩ ቢያድሩም ዓሣ መያዝ አልቻሉም ነበር። በቀጣዩ ቀን ግን ኢየሱስ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት መረባቸውን ሲጥሉ እጅግ ብዙ ዓሣ ከመያዛቸው የተነሳ ጀልባዎቻቸው ሊሰምጡ ደረሱ።​—ሉቃስ 5:6, 7

አንዳንድ ጊዜ ዓሣ አጥማጆቹ ጥልቅ ወደሆነው የባሕሩ ክፍል ይሄዱ ነበር። በሚያጠምዱበት ቦታ ላይ ሁለት ጀልባዎች ተባብረው ይሠራሉ። ዓሣ አጥማጆቹ መረባቸውን በሁለቱ ጀልባዎች መካከል ይጥሉታል፤ ከዚያም በአንዱ ጀልባ ላይ ያሉት ባሕረኞች የመረቡን አንድ ጫፍ ይዘው ወደ ግራ፣ በሌላኛው ጀልባ ላይ ያሉት ደግሞ የመረቡን ሌላ ጫፍ ይዘው ወደ ቀኝ አቅጣጫ በኃይል በመቅዘፍ መረቡን እየወጠሩት ይሄዳሉ፤ በዚህ ወቅት መረቡ በመሃል ያሉትን ዓሦች እንዳይወጡ ያግዳቸዋል። ጀልባዎቹ ክብ ሠርተው እንደገና ሲገናኙ መረቡ ዓሦቹን አንድ ላይ ሰብስቦ ይይዛቸዋል። ከዚያም ዓሣ አጥማጆቹ በመረቡ ጫፎች ላይ የታሠሩትን ገመዶች ወደ ላይ ከጎተቱ በኋላ ዓሦቹን ወደ ጀልባዎቹ ያስገባሉ። መረቡ ከ30 ሜትር በላይ ርዝመትና ከ2 ሜትር በላይ ስፋት ሊኖረው የሚችል ሲሆን በቡድን የሚዋኙ በርካታ ዓሦችን በሙሉ መያዝ ይችላል። ከባሕሩ በላይ በሚውለው የመረቡ ጠርዝ ላይ ማንሳፈፊያዎች፣ ባሕሩ ውስጥ በሚገባው የመረቡ ጠርዝ ላይ ደግሞ ማስመጫዎች ይደረጉበታል። ዓሣ አጥማጆቹ መረባቸውን በተደጋጋሚ እየጣሉ ለሰዓታት ያጠምዳሉ።

ጥልቀት በሌለው ውኃ ውስጥ ደግሞ ዓሣ አስጋሪዎቹ የተለየ ዘዴ ይጠቀማሉ። ጀልባው የመረቡን አንድ ጫፍ እየጎተተ ወደ ባሕሩ ከሄደ በኋላ በክብ ቅርጽ ዞሮ ወደ ዳርቻው ይመለሳል፤ በዚህ ጊዜ መረቡ ዓሦቹን ይሰበስባቸዋል። ከዚያም በባሕሩ ዳርቻ ላይ ያሉት ሰዎች መረቡን በመጎተት ዓሦቹን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ካወጧቸው በኋላ እዚያው ይለዩአቸዋል። የሚፈልጓቸውን ዓሦች በዕቃ ውስጥ ያስቀምጧቸዋል። አንዳንዶቹ ዓሦች ወዲያውኑ በአካባቢ ባለ ገበያ ላይ ይሸጣሉ። አብዛኞቹ ዓሦች ግን ከደረቁና በጨው ከታሹ ወይም በኮምጣጤ ከተዘፈዘፉ በኋላ በማሰሮ ተደርገው ወደ ኢየሩሳሌም ወይም ወደ ሌሎች አገሮች ይላካሉ። ቅርፊት ወይም ክንፍ የሌላቸው የባሕር ፍጥረታት ርኩስ እንደሆኑ ይቆጠሩ ስለነበር ይጣላሉ። (ዘሌዋውያን 11:9-12) ኢየሱስ ‘መንግሥተ ሰማያትን’ ከመረብ፣ የተለያየ ዓይነት ያላቸውን ዓሦች ደግሞ ከጥሩና ከመጥፎ ሰዎች ጋር ባመሳሰለበት ወቅት እንዲህ ስላለው ዓሣ የማጥመድ ዘዴ እየተናገረ ነበር።​—ማቴዎስ 13:47-50

ብቻውን ሆኖ የሚያጠምድ ሰው ደግሞ ከነሐስ በተሠራ መንጠቆ ላይ ዓሦችን የሚማርክ ምግብ የተንጠለጠለበት ማጥመጃ አሊያም አነስተኛ መረብ ይጠቀም ይሆናል። ዓሣ አጥማጁ በእግሩ ወደ ውኃው ይገባና መረቡን በእጁ አስተካክሎ ከያዘ በኋላ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ይወረውረዋል። በዚህ ጊዜ ክብ ቅርጽ ያለው መረብ ዝርግት ብሎ ውኃው ላይ ያርፍና ወደ ውስጥ ይገባል። ከዚያም ዓሣ አጥማጁ መረቡን በገመዱ ጎትቶ ያወጣዋል፤ ከቀናው መረቡ የተወሰኑ ዓሦች ይዞለት ይወጣል።

መረቦች ዋጋቸው ውድ ከመሆኑም ሌላ እነሱን መጠገን ከባድ ሥራ ስለሚጠይቅ ዓሣ አጥማጆቹ መረቦቻቸውን የሚጠቀሙባቸው በጥንቃቄ ነበር። አንድ ዓሣ አጥማጅ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው መረቦቹን በመጠገንና በማጠብ ሲሆን ከዚያም ያሰጣቸዋል፤ ዓሣ አጥምዶ በተመለሰ ቁጥር እነዚህን ሥራዎች ማከናወን ነበረበት። (ሉቃስ 5:2) ኢየሱስ፣ ከጊዜ በኋላ ሐዋርያቱ የሆኑትን ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን እንዲከተሉት በጋበዛቸው ወቅት በጀልባቸው ላይ ሆነው መረባቸውን እየጠገኑ ነበር።​—ማርቆስ 1:19

በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት ዓሣ አጥማጆች ዘንድ ተፈላጊ ከሆኑት ዓሦች መካከል ተላፒያ የሚባለው በብዛት የሚገኝ ዓሣ ይጠቀሳል። በገሊላ አካባቢ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች አዘውትረው የሚመገቡት ይህን የዓሣ ዝርያ ነበር፤ ኢየሱስም ጣፋጭ የሆነውን ይህን ዓሣ ሳይመገብ አልቀረም። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር የመገበው በደረቁና በጨው በታሹ ሁለት ተላፒያ ዓሦች ሊሆን ይችላል። (ማቴዎስ 14:16, 17፤ ሉቃስ 24:41-43) ይህ የዓሣ ዝርያ ብዙውን ጊዜ የሚዋኘው ልጆቹን አፉ ውስጥ ይዞ ነው። ልጆቹን በማይዝበት ጊዜ ደግሞ ጠጠር፣ ሌላው ቀርቶ የባሕሩ ወለል ላይ የሚያገኛቸውን የሚያንጸባርቁ ሳንቲሞች አፉ ውስጥ ሊይዝ ይችላል።​—ማቴዎስ 17:27

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ዓሣ አጥማጆች ውጤታማ ለመሆንና የልፋታቸውን ፍሬ ለማግኘት ትዕግሥተኛ፣ ታታሪ እንዲሁም ችግሮችን ለመጋፈጥ ፈቃደኞች መሆን ነበረባቸው። በተመሳሳይም ኢየሱስ፣ ከእሱ ጋር ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንዲካፈሉ ያቀረበላቸውን ግብዣ የተቀበሉ ሁሉ “ሰዎችን አጥማጆች” ሆነው ሲሠሩ ውጤታማ መሆን እንዲችሉ እነዚህን ባሕርያት ማዳበር ያስፈልጋቸዋል።​—ማቴዎስ 28:19, 20

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(ጽሑፉን ተመልከት)