በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቅርቡ የሚፈጸሙ ተአምራት

በቅርቡ የሚፈጸሙ ተአምራት

በቅርቡ የሚፈጸሙ ተአምራት

አንድ ሐኪም ከባድ ቀዶ ሕክምና ሊያደርግልህ ቀጠሮ ይዘሃል እንበል፤ ይህ ሐኪም ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ቀዶ ሕክምና አድርጎ እንደማያውቅ ብትገነዘብ ምን ይሰማሃል? ሁኔታው እንደሚያሳስብህ ጥያቄ የለውም። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሐኪም በሙያው አንቱ የተባለ ሰው እንደሆነና ለአንተ ከሚያደርግልህ ጋር የሚመሳሰሉ በርካታ ቀዶ ጥገናዎችን በተሳካ ሁኔታ እንዳከናወነ ብታውቅ ምን ይሰማሃል? ይህ ሐኪም ሊረዳህ እንደሚችል ይበልጥ አትተማመንም?

የምንኖርበት ዓለም እንደታመመ ሰው ስለሆነ ከባድ “ቀዶ ጥገና” ያስፈልገዋል። በመሆኑም ይሖዋ አምላክ፣ ምድርን እንደገና ገነት እንደሚያደርጋት በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተስፋ ሰጥቷል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይህ እንዲሆን ግን ክፋት ሙሉ በሙሉ መወገድ አለበት። (መዝሙር 37:9-11፤ ምሳሌ 2:21, 22) ምድር እንደገና ገነት ከመሆኗ በፊት በዙሪያችን የምናያቸው መጥፎ ነገሮች በሙሉ መጥፋት ይኖርባቸዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ቃል በቃል ተአምር ያስፈልጋል ማለት ይቻላል!​—ራእይ 21:4, 5

የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለው መጠነ ሰፊ ለውጥ በቅርቡ እንደሚከናወን ያምናሉ። እንዲህ ያለ እምነት ሊኖራቸው የቻለው ለምንድን ነው? ይሖዋ አምላክ ከዚህ በፊት የፈጸማቸው ተአምራት ስለ ወደፊቱ ጊዜ የገባውን ቃል ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል እንዳለው ስለሚያረጋግጡ ነው። እስቲ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተመዘገቡት ተአምራት መካከል ስድስቱን ወደፊት እንደሚፈጸሙ ከተነገሩ ተስፋዎች ጋር እናወዳድር።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊት ሕይወታችን የሚሰጣቸውን ተስፋዎች መማርህን እንድትቀጥል እናበረታታሃለን። እምነትህ እያደገ በሄደ መጠን ይሖዋ ከሚፈጽማቸው ተአምራት በግለሰብ ደረጃ ጥቅም የምታገኝበት ጊዜ እንደሚመጣ ያለህ ተስፋም ይጠናከራል።

[በገጽ 9 እና 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ተአምር፦

ኢየሱስ በጥቂት ዳቦና ዓሣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግቧል።​ማቴዎስ 14:13-21፤ ማርቆስ 8:1-9፤ ዮሐንስ 6:1-14

ተስፋ፦

“ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል።”​መዝሙር 67:6

ለእኛ ያለው ትርጉም፦

ማንም ሰው በረሃብ አይጠቃም።

ተአምር፦

ኢየሱስ ዓይነ ስውራንን ፈውሷል።​ማቴዎስ 9:27-31፤ ማርቆስ 8:22-26

ተስፋ፦

“የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ።”​ኢሳይያስ 35:5

ለእኛ ያለው ትርጉም፦

ዓይነ ስውራን ሁሉ ማየት ይችላሉ።

ተአምር፦

ኢየሱስ የአካል ጉዳተኞችን ፈውሷል።​ማቴዎስ 11:5, 6፤ ዮሐንስ 5:3-9

ተስፋ፦

“አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል።”​ኢሳይያስ 35:6

ለእኛ ያለው ትርጉም፦

የአካል ጉዳተኞች በሙሉ ይፈወሳሉ።

ተአምር፦

ኢየሱስ የተለያየ በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ፈውሷል።​ማርቆስ 1:32-34፤ ሉቃስ 4:40

ተስፋ፦

“‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።”​ኢሳይያስ 33:24

ለእኛ ያለው ትርጉም፦

ማንኛውም ዓይነት በሽታ ይወገዳል። ፍጹም ጤንነት ይኖረናል።

ተአምር፦

ኢየሱስ የተፈጥሮ ኃይሎችን ተቆጣጥሯል።​ማቴዎስ 8:23-27፤ ሉቃስ 8:22-25

ተስፋ፦

“ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ድካማቸው በከንቱ አይቀርም።”​ኢሳይያስ 65:21, 23

“ሕዝቤ ሰላማዊ በሆነ መኖሪያ፣ በሚያስተማምን ቤት፣ ጸጥ ባለም ስፍራ ዐርፎ ይኖራል።”​ኢሳይያስ 32:18

ለእኛ ያለው ትርጉም፦

የተፈጥሮ አደጋዎች አይኖሩም።

ተአምር፦

ኢየሱስ ሙታንን አስነስቷል።​ማቴዎስ 9:18-26፤ ሉቃስ 7:11-17

ተስፋ፦

“በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ . . . ይወጣሉ።”​ዮሐንስ 5:28, 29

“ባሕርም በውስጡ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሔዲስም በውስጣቸው ያሉትን ሙታን ሰጡ።”​ራእይ 20:13

ለእኛ ያለው ትርጉም፦

በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ይነሳሉ።