በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ትንባሆ ማጨስ ከአምላክ ጋር ያለኝን ግንኙነት ይነካብኛል?

ትንባሆ ማጨስ ከአምላክ ጋር ያለኝን ግንኙነት ይነካብኛል?

▪ የትንባሆ ውጤቶችን እንዳንጠቀም የሚከለክል ቀጥተኛ ሕግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሌለ ቅን የሆኑ ሰዎች እንዲህ ያለ ጥያቄ ሊፈጠርባቸው ይችላል። ታዲያ እንዲህ ያለ ሕግ ስላልተሰጠ አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ያለውን አመለካከት ማወቅ አይቻልም ማለት ነው? በፍጹም።

“ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት” እንደተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ደግሞ አምላክ ጤንነታችንን እንድንንከባከብ እንደሚፈልግና ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ግልጽ መመሪያዎችና ሐሳቦች ሰፍረው እናገኛለን። እስቲ በመጀመሪያ፣ ትንባሆ በጤንነታችን ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት ተመራማሪዎች ምን እንዳገኙ እንመልከት። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን ከእነዚህ የምርምር ውጤቶች አንጻር ለማየት እንሞክራለን።

ትንባሆ፣ የሚያጨሰውን ግለሰብ ጤንነት የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ ሰዎች ያለ ዕድሜያቸው እንዲሞቱ ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች ዋነኛው ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚሞቱት አምስት ሰዎች መካከል አንዱ ለሞት የሚዳረገው በትንባሆ ምክንያት ነው። በአሜሪካ በትንባሆ ምክንያት ለሞት የሚዳረጉት ሰዎች ቁጥር “የአልኮል መጠጦችንና ዕፆችን በመውሰድ፣ በነፍስ ግድያ፣ ራስን በማጥፋት፣ በመኪና አደጋ እንዲሁም በኤድስ በሽታ” ከሚሞቱት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር እንደሚበልጥ ብሔራዊ የአደገኛ ዕፆች መቆጣጠሪያ ተቋም ያወጣው ሪፖርት ይገልጻል።

ትንባሆ የሚያጨሱ ሰዎች ሌሎችንም ይጎዳሉ። አንድ ሰው በመጠኑም ቢሆን ለሲጋራ ጭስ ከተጋለጠ በጤንነቱ ላይ ጉዳት መድረሱ አይቀርም። ለሲጋራ ጭስ የተጋለጡ የማያጨሱ ሰዎች በሳንባ ካንሰርና በልብ በሽታ የመጠቃት አጋጣሚያቸው እስከ 30 በመቶ ያህል ከፍ ያለ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሐኪሞች፣ ሲጋራ በሚጨስበት ወቅት በቦታው ያልነበሩ ሰዎችም እንኳ ለጉዳት እንደሚዳረጉ ደርሰውበታል። ይህም የሆነው የሲጋራው ጭስ ከጠፋ ከረጅም ጊዜ በኋላም በሲጋራ ውስጥ ያሉት ኬሚካሎች ከልብስ፣ ከምንጣፍ ወይም ከሌሎች ቁሳቁሶች ላይ በቀላሉ ስለማይለቁ ነው። እነዚህ መርዛማ ኬሚካሎች በተለይ የልጆችን ጤንነት የሚጎዱ ከመሆናቸውም ሌላ ትምህርት የመቅሰም ችሎታቸው አዝጋሚ እንዲሆን ሊያደርጉ ይችላሉ።

ትንባሆ ሱስ ያስይዛል። የትንባሆ ተጠቃሚዎች ጎጂ ለሆነ ልማድ ባሪያ ይሆናሉ። እንዲያውም ተመራማሪዎች በትንባሆ ውስጥ ከሚገኘው ዋነኛ ኬሚካል ማለትም ከኒኮቲን ሱስ መላቀቅ በጣም ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ።

ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ከእነዚህ እውነታዎች አንጻር ስንመለከታቸው ምን መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን? የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በል፦

አምላክ ለሕይወት አክብሮት እንዲኖረን ይፈልጋል። አምላክ እሱን ማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ ለሰው ሕይወት አክብሮት ሊኖራቸው እንደሚገባ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ላይ ጠቁሟል። (ዘዳግም 5:17) እስራኤላውያን ቤት ሲገነቡ በጣሪያው ዙሪያ መከታ ወይም ከለላ ማበጀት ነበረባቸው። ይህን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? እስራኤላውያን የሚገነቡት ቤት ጣሪያው ጠፍጣፋ የነበረ ሲሆን አንዳንድ ሥራዎችን ጣሪያው ላይ ያከናውኑ ነበር። በመሆኑም መከታው የቤተሰቡ አባላትም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ከጣሪያው ላይ ወድቀው ጉዳት እንዳይደርስባቸው ወይም እንዳይሞቱ ይከላከላል። (ዘዳግም 22:8) ከዚህም ሌላ፣ አንድ እስራኤላዊ የእሱ ንብረት የሆነ እንስሳ በሌሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረበት። (ዘፀአት 21:28, 29) ትንባሆ የሚያጨስ ሰው እነዚህ ሕግጋት የተመሠረቱባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይጥሳል። እንዲህ ያለው ሰው በገዛ እጁ የራሱን ጤንነት ያቃውሳል። አልፎ ተርፎም በአካባቢው ያሉ ሌሎች ሰዎችን ጤንነት አደጋ ላይ ይጥላል።

አምላክ፣ እሱንም ሆነ ባልንጀራችንን እንድንወድ ይጠብቅብናል። ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ተከታዮቹ ሁለቱን ታላላቅ ትእዛዛት መጠበቅ እንዳለባቸው ተናግሯል። ክርስቲያኖች በሙሉ ልባቸው፣ ነፍሳቸው፣ አእምሯቸውና ኃይላቸው አምላክን መውደድ እንዲሁም ባልንጀራቸውን እንደ ራሳቸው መውደድ አለባቸው። (ማርቆስ 12:28-31) ሕይወት ከአምላክ የተገኘ ስጦታ በመሆኑ አንድ ሰው ትንባሆ የሚያጨስ ከሆነ ለዚህ ስጦታ ምንም ዓይነት አድናቆት እንደሌለው እንዲሁም አምላክን እንደማይወድ እያሳየ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 17:26-28) ይህ ግለሰብ ባልንጀራውን እንደሚወድ ቢናገርም ልማዱ በሌሎች ላይ ከባድ ጉዳት ስለሚያስከትል ባልንጀራውን ይወዳል ማለት አይቻልም።

አምላክ ርኩስ ከሆኑ ልማዶች እንድንርቅ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖች “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ” ራሳቸውን እንዲያነጹ ያዝዛል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ትንባሆ ደግሞ አንድን ሰው እንደሚያረክሰው የታወቀ ነው። አምላክን ለማስደሰት ሲሉ ከትንባሆ ሱስ ለመላቀቅ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች ከባድ ትግል ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ በአምላክ እርዳታ ከዚህ ርኩስ ልማድ መላቀቅ ይችላሉ።