በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የእውነት ጠበቆች

የእውነት ጠበቆች

132ኛው የጊልያድ ምረቃ

የእውነት ጠበቆች

መጋቢት 10, 2012 በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የትምህርት ማዕከል ለተሰበሰቡት ሁሉ ልዩ ቀን ነበር። ከተለያዩ አገሮች የመጡትን ጨምሮ ጥሩ አለባበስ ያላቸው በሺህ የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 132ኛው ክፍል የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል። ብዙዎቹ የተሰበሰቡት በፓተርሰን በሚገኘው አዳራሽ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች ሆነው ፕሮግራሙን በቴሌቪዥን ተከታትለዋል። የተሰብሳቢዎቹ አጠቃላይ ቁጥር 9,042 ነበር።

ሁሉም ፕሮግራሙን በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። ከዚህ ቀደም በትምህርት ቤቱ ከተካፈሉ ክርስቲያኖች በተለየ ሁኔታ ሁሉም ተመራቂዎች በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሰማርተው የነበሩ ናቸው፤ በሌላ አባባል ቤቴላውያን፣ ልዩ አቅኚዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ወይም ሚስዮናውያን ናቸው። ሆኖም አንዳቸውም ቢሆን ከዚያ በፊት በጊልያድ ትምህርት ቤት አልሠለጠኑም። ታዲያ ለእነዚህ ልምድ ያካበቱ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ንግግር ሊቀርብላቸው ይችላል?

ተሰብሳቢዎቹ መልሱን ለማግኘት ብዙም መጠበቅ አላስፈለጋቸውም። የመጀመሪያውን ንግግር ያቀረበው የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የነበረውና የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጌሪት ሎሽ ነው። “ጥብቅና ትቆማላችሁ?” የሚል ጉጉት የሚቀሰቅስ ጥያቄ አቀረበ። ወንድም ሎሽ፣ ክርስቲያኖች ለእውነት ይኸውም ለክርስትና ትምህርቶች በሙሉ ጥብቅና እንደሚቆሙ ተናገረ። ለእውነት ጥብቅና መቆም ሲባል ለሰዎች እውነትን ማስተማርን ብቻ ሳይሆን እንዲወዱት መርዳትንም ይጨምራል።

ወንድም ሎሽ “እውነትን እንደያዝን እንዴት እናውቃለን?” በማለት ጠየቀ። ይህን የሚያሳውቀን እውነትን የተቀበሉ ሰዎች ቁጥር መብዛት አይደለም። በዛሬው ጊዜ ንጹሑን አምልኮ የተቀበሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቢኖሩም በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ግን ይህን ያደረጉት ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። ወንድም ሎሽ እውነትን እንደያዝን የምናውቅባቸውን አምስት ነገሮች ዘረዘረ፤ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦ (1) የኢየሱስን ትምህርቶች እንከተላለን፣ (2) እርስ በርስ እንዋደዳለን፣ (3) የአምላክን የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በጥብቅ እንከተላለን፣ (4) በዚህ ዓለም ፖለቲካ ውስጥ አንገባም እንዲሁም (5) የአምላክን ስም ተሸክመናል።

“ከይሖዋ የምትቀበሏቸውን መመሪያዎች መታዘዛችሁን ቀጥሉ”

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን ሻንጣ ይዞ ወደ መድረኩ መውጣቱ ተሰብሳቢዎቹ የሚናገረውን ለማዳመጥ እንዲጓጉ አደረጋቸው። በ⁠ኢሳይያስ 50:5 ላይ የተመሠረተው የንግግሩ ጭብጥ “ከይሖዋ የምትቀበሏቸውን መመሪያዎች መታዘዛችሁን ቀጥሉ” የሚል ነበር። “እኔም ዐመፀኛ አይደለሁም፤ ወደ ኋላም አላፈገፈግሁም” የሚለው ይህ ጥቅስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረ ትንቢት ነው።

ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠውን አመራር ለመታዘዝ ንቁ እንዲሆኑ ወንድም ጃክሰን ተማሪዎቹን አሳሰባቸው። በ⁠ማቴዎስ 25:14-30 በሚገኘው ስለ ታላንት የሚናገር ምሳሌ ላይ እያንዳንዱ ባሪያ የተሰጠው እንደ አቅሙ ስለነበር ሁሉም የተሰጣቸው ተመሳሳይ መጠን ያለው ታላንት ነው ሊባል ይችላል። እነዚህ ባሪያዎች አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸው ነበር። ሁለቱ ባሪያዎች የተመሰገኑ ሲሆን “ጥሩና ታማኝ ባሪያ!” ተብለውም ተጠርተዋል። ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ታማኝ የሚያስብለን የምናገኘው ውጤት ሳይሆን ከይሖዋ የምንቀበላቸውን መመሪያዎች መታዘዛችንን መቀጠላችን ነው።

ሦስተኛው ባሪያ “ክፉና ሰነፍ” እንዲሁም “የማይረባ” ተብሏል። የዚህ ባሪያ ድክመት ምን ነበር? የተሰጠውን ታላንት ቀብሮት ነበር። ታላንት ሳንቲም አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የክብደት መለኪያ ነው። አንድ ታላንት 6,000 ዲናር የሚያህል ዋጋ ያለው ሲሆን 20 ኪሎ ግራም ክብደት አለው። ይህ ደግሞ አንድ ሰው በአውሮፕላን ወደ ሌላ አገር ሲጓዝ ለመያዝ የሚፈቀድለት የጭነት መጠን ነው። አንድ ሻንጣ የሚያህልን ዕቃ መቅበር ቀላል ሥራ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህ ባሪያው አንድ ሥራ አከናውኗል፤ ይኸውም ታላንቱን ቀብሯል። ሆኖም የታዘዘው ይህን እንዲያደርግ አልነበረም። በተመሳሳይም አንድ ሚስዮናዊ በሥራ ሊጠመድ ይችላል፤ ሆኖም በየትኞቹ ሥራዎች? ምናልባትም ለወዳጅ ዘመዶቹ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ኢንተርኔት በመቃኘት፣ በማኅበራዊ ሕይወት ወይም ሰብዓዊ ሥራ በመሥራት ተጠምዶ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው ሰው እነዚህን ነገሮች ሲያከናውን በመዋሉ በጣም ሊደክመው ይችላል፤ ሆኖም የታዘዘውን ነገር አላከናወነም። ወንድም ጃክሰን ንግግሩን ሲደመድም “ምንጊዜም መመሪያ ተከተሉ!” ብሏል።

“ጥርጣሬ እንዳያድርባችሁ ተጠንቀቁ”

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም አንቶኒ ሞሪስ በዚህ ጭብጥ ላይ ተመሥርቶ ንግግር አቀረበ። ወንድም ሞሪስ “መጽሐፍ ቅዱስ፣ እምነትን ከጥርጣሬ ጋር ፈጽሞ አያያይዘውም” ብሏል። አክሎም “እምነት፣ ጥርጣሬን ያስወግዳል” አለ። ሰይጣን፣ ፍጹም በሆነችው በሔዋን አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬ መዝራት ከቻለ በእኛም አእምሮ ውስጥ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይችላል። ወንድም ሞሪስ “በመንፈሳዊ በመመገብ እምነታችሁን ከገነባችሁት ጥርጣሬ በረሃብ ይሞታል” አለ። አክሎም የጴጥሮስን ምሳሌ ጠቀሰ፤ ጴጥሮስ ‘በውኃ ላይ መራመድ’ ቢችልም “ማዕበሉን ሲያይ” ስለፈራ መስጠም ጀመረ። ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ከያዘው በኋላ “ለምን ተጠራጠርክ?” ብሎታል። (ማቴዎስ 14:29-31) “እናንት ሚስዮናውያን፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመጠመዳችሁ የምታከናውኗቸው ነገሮች ብዛት በውኃ ላይ የመራመድን ያህል ሌሎችን ያስገርም ይሆናል፤ ይሁንና ማዕበል ሲመጣባችሁ መጠራጠር እንዳትጀምሩ ተጠንቀቁ” በማለት ወንድሞ ሞሪስ መከራቸው።

ወንድም ሞሪስ፣ ማዕበል መሰል በሆኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ ከባድ ቢሆንም ውሎ አድሮ ነፋሱ ማቆሙ እንደማይቀር ተማሪዎቹን አስታውሷቸዋል። ተማሪዎቹ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ ታስረው በነበረበት ጊዜ ያደረጉትን ነገር እንዲያስታውሱ አበረታታቸው። የሐዋርያት ሥራ 16:25 “እኩለ ሌሊት ገደማ ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩና አምላክን በመዝሙር እያወደሱ ነበር፤ ሌሎቹ እስረኞችም ይሰሟቸው ነበር” ይላል። ጳውሎስና ሲላስ ከመጸለይም አልፈው ይዘምሩ እንደነበር አስተውሉ። የሚዘምሩትም ሌሎች እስረኞች እስኪሰሟቸው ድረስ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ነበር። አብዛኞቻችን ጥሩ አድርገን የመዘመር ችሎታ ባይኖረንም በተለይ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ወቅት ከመዘመር ወደኋላ ማለት አይኖርብንም። ወንድም ሞሪስ ለይሖዋ ዘምሩ በተባለው መዝሙር መጽሐፍ ላይ የሚገኘውንና “እስከ መጨረሻው መጽናት” የሚለውን መዝሙር ቁጥር 135⁠ን በማንበብ ንግግሩን ደመደመ።

ሌሎች የሚያበረታቱ ንግግሮች

“በጎ ዘመን ለማየት ትወዳላችሁ?” በሚል ርዕስ በዕቃ ግዢ ክፍል ውስጥ የሚሠራው ወንድም ሮበርት ሉሲዮኒ ንግግር አቀረበ። የንግግሩ ጭብጥ የተወሰደው በ⁠መዝሙር 34:12 [የ1954 ትርጉም] ላይ ከሚገኘው የንጉሥ ዳዊት ሐሳብ ነው። የወንድም ሉሲዮኒ ንግግር ከይሖዋ ጋር ያለንን ጥሩ ግንኙነት ሳናጣ አስቸጋሪ ወቅቶችን እንዴት ማለፍ እንደምንችል የሚያብራራ ነበር። በ⁠1 ሳሙኤል ምዕራፍ 30 ላይ ከሚገኘው ዘገባ ብዙ ትምህርቶችን ማግኘት ይቻላል። ዳዊት፣ አብረውት ያሉት ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው ከንጉሥ ሳኦል ይሸሹ በነበረበት ወቅት በጺቅላግ በስደት ይኖሩ ነበር። አማሌቃውያን ወራሪዎች ቤተሰቦቻቸውን ማርከው በወሰዱባቸው ጊዜ ሰዎቹ፣ ጥፋተኛው ዳዊት እንደሆነ ስለተሰማቸው ሊወግሩት ተነሱ። ታዲያ ዳዊት ምን አደረገ? ተስፋ አልቆረጠም፤ ከዚህ ይልቅ “በአምላኩ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ልቡን አበረታ።” (1 ሳሙኤል 30:6) ዳዊት መመሪያ እንዲሰጠው ይሖዋን ጠየቀ፤ ከዚያም ከአምላክ መመሪያ ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ ምርኮኞቹን አስመለሰ። ተማሪዎቹ ልክ እንደ ዳዊት በይሖዋ ላይ የሚታመኑና መመሪያውን የሚከተሉ ከሆነ በጎ ዘመን ለማየት መውደዳቸውን እንደሚያሳዩ ተናጋሪው ገልጿል። በተሰጣቸው ውድ የሆነ አገልግሎት ሲካፈሉ አስደሳች ሕይወት ይመራሉ።

“ከጨለማው በኋላ በሚፈነጥቀው ብርሃን ላይ አተኩሩ” በሚል ጭብጥ የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ወንድም ማይክል በርኔት ንግግር አቀረበ። እስራኤላውያን ፀሐይ ከጠለቀች ጀምሮ ጎህ እስከሚቀድበት ድረስ ያለውን ጊዜ በሦስት የሚከፋፍሉት ሲሆን እያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ አራት አራት ሰዓት ይሸፍን ነበር። ከሌሊቱ 8:00 እስከ 12:00 ያለውን ጊዜ የሚሸፍነው የመጨረሻው ክፍለ ጊዜ ድቅድቅ ጨለማ ከመሆኑም ሌላ በጣም ስለሚቀዘቅዝ ነቅቶ ለመጠበቅ አስቸጋሪ ነው። መዝሙራዊው በዚህ ክፍለ ጊዜ እንቅልፍ እንዳያሸልበው ሲል በይሖዋ ቃል ላይ ያሰላስል ነበር። (መዝሙር 119:148) ወንድም በርኔት ለተማሪዎቹ “ንቁ መሆን አለባችሁ” አላቸው። “አንዳንድ ጊዜ ሁሉ ነገር ሊጨልምባችሁና በተስፋ መቁረጥ ልትዋጡ እንዲሁም በዓለም ላይ የሚታየው የፍቅር መቀዝቀዝ ተጽዕኖ ሊያሳድርባችሁ ይችላል። በዚህ ጊዜ ምን እንደምታደርጉ አስቀድማችሁ ማሰብ ይኖርባችኋል።” በመንፈሳዊ ንቁ መሆን እንዲችሉ ጥልቀት ያላቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሶች ማጥናት እንደሚያስፈልጋቸው አስታወሳቸው። ወንድም በርኔት ነጥቡን ግልጽ ለማድረግ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ ወዳጃችሁ እንዲሆን ስለምትፈልጉ በየዕለቱ ወደ እሱ ትጸልያላችሁ። ወዳጃችሁ ይሖዋም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት በየዕለቱ ሲያናግራችሁ አዳምጡት። ሌሊቱ እየተገባደደ ነው፤ ስለዚህ ከፊታችሁ ያሉትን ቀናት እንዴት እንደምትጠቀሙባቸው እቅድ አውጡ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ ከጨለማው በኋላ በሚፈነጥቀው ብርሃን ላይ ማተኮር ትችላላችሁ።”

“ለሚጠብቃችሁ ሥራ ሥልጠና አግኝታችኋል” በሚል ርዕስ ቀጣዩን ንግግር ያቀረበው ማርክ ኑሜር የተባለ ሌላ የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ ሲሆን ንግግሩ የተመሠረተው በ⁠1 ጴጥሮስ 5:10 ላይ ነው። ወንድም ኑሜር፣ ተማሪዎቹን “ተሞክሮ ያላችሁ ሰባኪዎች ሆናችሁ ሳለ፣ ወደ መጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ለምን ተጠራችሁ?” በማለት ከጠየቃቸው በኋላ መልሱን ሲናገር እንዲህ አለ፦ “በተሰማራችሁበት መስክ ባለሙያ ስለሆናችሁ ነው። ብዙ ባለሙያዎች ችሎታቸውን ይበልጥ ለማዳበር ሲሉ ከሥራቸው ፈቃድ ወስደው ተጨማሪ ሥልጠና ያገኛሉ። ባለፉት አምስት ወራት ይሖዋ፣ ስለ ቃሉና ስለ ድርጅቱ ጥልቀት ያለው ጥናት እንድታደርጉ አጋጣሚ በመስጠት “ጽኑ” እና “ጠንካሮች” እንድትሆኑ አድርጓችኋል፤ ይህም የሚጠብቋችሁን ከባድ ኃላፊነቶች ለመወጣት ያስችላችኋል። ጠንካራ የሆኑ የምሰሶ እንጨቶች ጭነት ሲበዛባቸው አይጎብጡም፣ አይጣመሙም ወይም አይሰበሩም። እናንተም ከሥልጠናው ያገኛችሁት ጥቅም ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር አብራችሁ ስትሠሩ በግልጽ ይታያል። የሚያጋጥማችሁ ጫና ከአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድታፈነግጡ ያደርጋችኋል? ወይስ ጠንካራ በመሆን ከአምላክ ቃል ከተማራችሁት ነገር ጋር በሚስማማ መልኩ ቀጥ ብላችሁ ትመላለሳላችሁ? ጠንካራ የሆነ ነገር ከባድ ጭነትን መሸከም ይችላል። ምሰሶው ጠንካራ እንዲሆን የሚያደርጉት በእንጨቱ ውስጥ ያሉት ንጥረ ነገሮች ናቸው። የእናንተም ጥንካሬ የሚመካው በውስጣዊ ማንነታችሁ ነው። ይሖዋ እዚህ ያመጣችሁ የሚጠብቃችሁን ሥራ ለመወጣት ጠንካሮችና እምነት የሚጣልባችሁ ሰዎች እንድትሆኑ ለማሠልጠን ነው። አምላክ እናንተን ለመርዳት የበኩሉን አድርጓል፤ እናንተም ‘ታላቁ አስተማሪያችሁ’ ሥልጠናችሁን እንዲፈጽም የበኩላችሁን እንድታደርጉ እንጸልያለን።”

ተሞክሮዎችና ቃለ ምልልሶች

በጊልያድ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተማሪዎቹን ተሞክሮ ከራሳቸው አንደበት መስማት የሚያስደስት ነው፤ በዚህ ዓመትም ቢሆን እንዲህ ያለ ክፍል ቀርቦ ነበር። ተማሪዎቹ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ያጋጠሟቸውን ነገሮች በሠርቶ ማሳያ መልክ አቅርበዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ፈረንሳዊ የሆኑ አንድ ባልና ሚስት ወደ ጊልያድ ትምህርት ቤት ሲመጡ በአንድ አውሮፕላን ማረፊያ ለስድስት ሰዓት ያህል መቆየት ነበረባቸው። እነዚህ ባልና ሚስት፣ በአውሮፕላን ማረፊያው ምግብ ቤት ውስጥ ሆነው በረራቸውን ከሚጠብቁ ሁለት ሰዎች ጋር ውይይት ከፈቱ። አንደኛው ሰውዬ ከማላዊ እንደመጣ ሲነግራቸው በቺቼዋ ቋንቋ አነጋገሩት። በጣም ስለተደነቀ ቋንቋውን እንዴት እንዳወቁት ጠየቃቸው። እነሱም በማላዊ ሚስዮናዊ ሆነው ያገለግሉ እንደነበር ነገሩት። ሌላኛው ሰውዬ ደግሞ ከካሜሩን እንደመጣ ሲገልጽላቸው በፈረንሳይኛ አነጋገሩት። ሁለቱም ሰዎች ለይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት የነበራቸው ሲሆን እነዚህ ሚስዮናውያንም ምሥራቹን ነገሯቸው።

በትርጉም አገልግሎት ክፍል የሚሠራው ወንድም ኒኮላስ አላዲስ ደግሞ ለሁለት ባልና ሚስት ተማሪዎች ቃለ መጠይቅ አደረገላቸው። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በጦርነት ትታመስ በነበረችው በምሥራቅ ቲሞር በሚስዮናዊነት ለማገልገል ከአውስትራሊያ ሄደው ነበር። ሌሎቹ ባልና ሚስት ደግሞ በሆንግ ኮንግ ለማገልገል ከኮሪያ የሄዱ ናቸው። ሁለቱም ባልና ሚስቶች ወደ ምድባቸው ተመልሰው በጊልያድ የተማሩትን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ጓጉተዋል።

ተመራቂዎቹ ዲፕሎማቸውን ከተቀበሉ በኋላ ከመካከላቸው አንዱ ለተሰጣቸው ሥልጠና ያላቸውን አድናቆት የሚገልጽ ደብዳቤ አነበበ። ከዚያም ወንድም ሎሽ አንዳንድ ደስ የሚሉ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን በመጠቀም ፕሮግራሙን ደመደመ። ከእነዚህም መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፦ “እውነት እንደ ቀስተ ደመና ውብ ነው፤ በበረሃ መካከል እንዳለ ገነት እንዲሁም በሚናወጥ ባሕር ላይ እንደ መልሕቅ ነው።” አክሎም “እውነትን ማወቅ እንዴት ያለ በረከት ነው። እናንተም ለእውነት ጥብቅና ቁሙ፤ ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ እርዷቸው” በማለት ተናገረ።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/​ሥዕል]

ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ

12 የተውጣጡባቸው አገሮች

36 አማካይ ዕድሜ

20 ከተጠመቁ በኋላ ያሳለፏቸው ዓመታት በአማካይ

15 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ

[ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ተመራቂዎቹ በካርታው ላይ ወደሚታዩት አገሮች ተመድበዋል

ሚስዮናውያን የተመደቡባቸው አገሮች

ቤሊዝ

ቤኒን

ካምቦዲያ

ካሜሩን

ኬፕ ቨርድ

ኮት ዲቩዋር

ዶሚኒካ ሪፑብሊክ

ምሥራቅ ቲሞር

ኢኳዶር

ጋቦን

ጆርጂያ

ጊኒ

ሆንግ ኮንግ

ላይቤሪያ

ማዳጋስካር

ማላዊ

ፔሩ

ሳሞአ

ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ

ዩናይትድ ስቴትስ

ዚምባብዌ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ132ኛው ክፍል ተመራቂዎች

ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።

(1) ሮቤርቶ ያፕ፣ ጁሊ ያፕ፣ ቲንግ ዋ ንግ፣ ፓትሪሻ ንግ፣ ፍራንክ ሎሪኖ፣ ብላንዲን ሎሪኖ፣ ስቴፋኒ ዎን፣ ሳንግ ዎን

(2) ናታን ሞራሌስ፣ ሚርያም ሞራሌስ፣ ሆናታ ዛኑቱ፣ ማኑዌላ ዛኑቱ፣ ኢንጋ ረምፍ፣ ጄከብ ረምፍ፣ ዴልፊን ዤርሜን፣ ኒኮላ ዤርሜን

(3) ኢቭ አትቻዴ፣ ኢቮን አትቻዴ፣ ክሪስ ቶማስ፣ ኤማ ቶማስ፣ ካትሪን ኤስቲዤን፣ ፖለትሳር ኤስቲዤን

(4) ዴቪድ ኤርማን፣ አና ኤርማን፣ ጆሹዋ ብሬ፣ አማንዳ ብሬ፣ ማርታ አሞሪን፣ ዴቪድ አሞሪን፣ የንግ ሶ፣ የንግ ጊ ሶ

(5) ዣን ሲሞን፣ ክሪስቴል ሲሞን፣ ክሪስቶፈር ሲል፣ ዲአኔዝ ሲል፣ ጄኔፈር ኤሪክሰን፣ ራየን ኤሪክሰን

(6) ዳንዬል መክለስኪ፣ ታንጂ መክለስኪ፣ አዳም ብራውን፣ ቫለሪ ብራውን፣ ዱኣኒ ማሪአኑ፣ ሲልያ ማሪአኑ፣ ዮላንዳ ሎዮላ፣ ካሌብ ሎዮላ

(7) ፊሊፕ ረትገርዝ፣ ኔኦሚ ረትገርዝ፣ ፊሊፕ ፉኮ፣ ሻርሎት ፉኮ፣ ጆኒ ዉንጃ፣ ኤዚኬል ዉንጃ