በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በእስራኤል ሊቀ ካህን የደረት ኪስ ላይ የነበሩት የከበሩ ድንጋዮች የተገኙት ከየት ነው?

እስራኤላውያን ከግብፅ ወጥተው በምድረ በዳ በነበሩበት ወቅት አምላክ በሊቀ ካህኑ ልብስ ላይ የደረት ኪስ እንዲሠሩ አዝዟቸው ነበር። (ዘፀአት 28:15-21) በደረት ኪሱ ላይ የነበሩት የከበሩ ድንጋዮች ሰርዲዮን፣ ቶጳዝዮን፣ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፣ በሉር፣ ሰንፔር፣ አልማዝ፣ ያክንት፣ ኬልቄዶን፣ አሜቴስጢኖስ፣ ቢረሌ፣ መረግድና ኢያስጴድ ናቸው። * ይሁንና እስራኤላውያን እነዚህን የከበሩ ድንጋዮች ማግኘት የሚችሉበት አጋጣሚ ነበራቸው?

በጥንት ዘመን የነበሩ ሰዎች የከበሩ ድንጋዮችን እንደ ውድ ሀብት ይቆጥሯቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ለመገበያያነት ይጠቀሙባቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የጥንቶቹ ግብፃውያን በጣም ሩቅ ወደሆኑ አካባቢዎች ማለትም በዛሬው ጊዜ ኢራንና አፍጋኒስታን ተብለው ወደሚጠሩት ቦታዎች ምናልባትም እስከ ሕንድ ድረስ በመሄድ የከበሩ ድንጋዮችን ለማግኘት ጥረት ያደርጉ ነበር። እንዲሁም በግብፅ ካሉ የማዕድን ማውጫ ቦታዎች የተለያየ ዓይነት ያላቸው በርካታ የከበሩ ድንጋዮችን ያወጡ ነበር። የግብፅ ነገሥታት ድል አድርገው በያዟቸው አካባቢዎች ያሉ የማዕድን ማውጫ ቦታዎችን በበላይነት ይቆጣጠሩ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ኢዮብ፣ በእሱ ዘመን የነበሩ ሰዎች ውድ የሆኑ ማዕድናትን ለማግኘት ጉድጓድ ይቆፍሩና ከመሬት በታች መተላለፊያ ያበጁ የነበረው እንዴት እንደሆነ ገልጿል። ኢዮብ፣ ከመሬት ተቆፍረው ከሚወጡት ማዕድናት መካከል ሰንፔርንና ቶጳዝዮንን ለይቶ ጠቅሷል።​—ኢዮብ 28:1-11, 19

በዘፀአት መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ዘገባ፣ እስራኤላውያን ግብፅን ለቅቀው ሲወጡ የግብፃውያንን ውድ ንብረቶች ‘በዝብዘው እንደወሰዱ’ ይናገራል። (ዘፀአት 12:35, 36) በመሆኑም እስራኤላውያን በሊቀ ካህኑ የደረት ኪስ ላይ የተደረጉትን የከበሩ ድንጋዮች ያገኙት ከግብፅ ሊሆን ይችላል።

በጥንት ዘመን የነበሩ ሰዎች ወይንን ለመድኃኒትነት ይጠቀሙበት የነበረው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች አንዱ በዘራፊዎች ስለተደበደበ ሰው ይገልጻል። ኢየሱስ፣ በምሳሌው ላይ አንድ ሳምራዊ ቁስሎቹ ላይ “ዘይትና የወይን ጠጅ” ካፈሰሰ በኋላ በጨርቅ በማሰር ይህን ሰው እንደረዳው ተናግሯል። (ሉቃስ 10:30-34) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ለወዳጁ ለጢሞቴዎስ ደብዳቤ ሲጽፍለት “ከእንግዲህ ውኃ አትጠጣ፤ ከዚህ ይልቅ ለሆድህና በተደጋጋሚ ለሚነሳብህ ሕመም ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ” በማለት መክሮታል። (1 ጢሞቴዎስ 5:23) ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ሐሳብና ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ምክር በሕክምናው ዓለም ተቀባይነት አላቸው?

ኤንሸንት ዋይን የተባለው መጽሐፍ፣ ወይን “ሕመምን የሚያስታግስ፣ በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን የሚገድል እንዲሁም ሁለገብ ጥቅም ያለው መድኃኒት” እንደሆነ ገልጿል። በጥንት ዘመን በግብፅ፣ በሜሶጶጣሚያና በሶርያ የነበሩ ሰዎች በሚጠቀሙበት የሕክምና ዘዴ ውስጥ ወይን ወሳኝ ቦታ ነበረው። ዚ ኦክስፎርድ ከምፓኒየን ቱ ዋይን የተሰኘው መጽሐፍ ወይን “በጽሑፍ ሰፍረው ከሚገኙት መድኃኒቶች ሁሉ ጥንታዊው” እንደሆነ ገልጿል። ዚ ኦሪጅንስ ኤንድ ኤንሸንት ሂስትሪ ኦቭ ዋይን የተባለው መጽሐፍ ደግሞ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠውን ምክር አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦ “የታይፎይድ በሽታ አምጪ ተሕዋስያንና ሌሎች አደገኛ የሆኑ በዓይን የማይታዩ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ወይን ከነካቸው ወዲያውኑ እንደሚሞቱ በቤተ ሙከራ ማረጋገጥ ተችሏል።” በዘመናችን የተደረገ አንድ ምርምር እንዳረጋገጠው በወይን ውስጥ ከሚገኙት ከ500 በላይ የሚሆኑ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ከሕክምና ጋር የተያያዙ በርካታ ጥቅሞች አሏቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 እዚህ ጥቅስ ላይ የተዘረዘሩት የከበሩ ድንጋዮች በሙሉ ዛሬ ምን ተብለው እንደሚጠሩ ለይቶ ለማወቅ ያስቸግራል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቴብስ፣ ግብፅ የናክት መቃብር ላይ የሚገኝ ገበሬዎች ወይን ሲረግጡ የሚያሳይ ምስል

[የሥዕሉ ምንጭ]

Gianni Dagli Orti/​The Art Archive at Art Resource, NY