በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ አምላክ ቅረብ

ይሖዋ የፍትሕ መጓደልን ይጠላል

ይሖዋ የፍትሕ መጓደልን ይጠላል

“ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ።” (መክብብ 8:9) ይህ ሐሳብ የተጻፈው 3,000 ከሚያህሉ ዓመታት በፊት ቢሆንም የምንኖርበት ዓለም ያለበትን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው። የሚኖሩት የትም ይሁን የት፣ ሁሉም ሰዎች ሥልጣናቸውን አላግባብ የመጠቀም ዝንባሌ አላቸው። ሥልጣናቸውን አላግባብ የሚጠቀሙ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የጥቃታቸው ሰለባ የሚያደርጉት ምንም አቅም የሌላቸውንና ምስኪኖችን ነው። ታዲያ ይሖዋ እንዲህ ስላለው የፍትሕ መጓደል ምን ይሰማዋል? ሕዝቅኤል 22:6, 7, 31 ላይ ያለውን ሐሳብ በመመርመር የዚህን ጥያቄ መልስ ማግኘት እንችላለን።​—ጥቅሱን አንብብ።

ይሖዋ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ላይ፣ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች ሥልጣናቸውን ፈጽሞ አላግባብ መጠቀም እንደሌለባቸው በግልጽ ተናግሯል። ይሖዋ ብሔሩን የሚባርከው መሪዎቹ የተጨቆኑትንና ድሆችን በደግነት ብሎም በአሳቢነት የሚይዙ ከሆነ ብቻ ነው። (ዘዳግም 27:19፤ 28:15, 45) በሕዝቅኤል ዘመን በኢየሩሳሌም እና በይሁዳ የነበሩ መሳፍንት ግን ሥልጣናቸውን ርኅራኄ በጎደለው መንገድ አላግባብ ይጠቀሙበት ነበር። እስቲ በወቅቱ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደነበረ እንመልከት።

የእስራኤል መሳፍንት ‘ሥልጣናቸውን በመጠቀም ደም ያፈስሱ’ ነበር። (ቁጥር 6) ታዲያ ሕጉን የመታዘዝና ሌሎች እንዲህ እንዲያደርጉ የማስተማር ኃላፊነት ያለባቸው መሪዎች፣ ሥልጣናቸውን አላግባብ እየተጠቀሙ እንዲሁም የንጹሕ ሰው ደም እያፈሰሱ እንዴት ፍትሕ ሊሰፍን ይችላል?

ሕዝቅኤል ያወገዘው መሪዎቹን ብቻ ሳይሆን የእነሱን ፈለግ ተከትለው የይሖዋን ሕግ ያልታዘዙትን ሌሎች ሰዎች ጭምር እንደሆነ ግልጽ ነው። ሕዝቅኤል አክሎ ሲናገር “አባቶችና እናቶች በውስጥሽ ተዋረዱ” ብሏል። (ቁጥር 7) ሕዝቡ፣ ይሖዋ ለወላጆች የሰጣቸውን ቦታ በማቃለል ለብሔሩ ሕልውና እንደ ምሰሶ የሆነው የቤተሰብ ተቋም እንዲፈራርስ አድርገዋል።​—ዘፀአት 20:12

ብልሹ ምግባር ያላቸው ሰዎች በሕዝቡ መካከል የነበሩ ረዳት የሌላቸው ምስኪኖችን ይበዘብዙ ነበር። እነዚህ ሰዎች የሚፈጽሙት እያንዳንዱ መጥፎ ድርጊት አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ፍቅር የተንጸባረቀበት ሕግ እንዳቃለሉ የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን በመካከላቸው ለሚኖሩ የባዕድ አገር ሰዎች ለየት ያለ አሳቢነት እንዲያሳዩ የአምላክ ሕግ ያዝዝ ነበር። (ዘፀአት 22:21፤ 23:9፤ ዘሌዋውያን 19:33, 34) ይሁን እንጂ ሕዝቡ ‘መጻተኞችን ይጨቁኑ’ ነበር።​—ቁጥር 7

ከዚህም ሌላ ሕዝቡ ረዳት የሌላቸውን ማለትም ‘ድኻ አደጎችንና መበለቶችን’ ያንገላቱ ነበር። (ቁጥር 7) ይሁንና ይሖዋ ወላጅ ወይም የትዳር ጓደኛ የሞተባቸው ሰዎች ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ለየት ያለ ትኩረት ይሰጣል። አምላክ፣ ረዳት የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን በሚበድሉ ሰዎች ላይ ራሱ እርምጃ እንደሚወስድ ቃል ገብቷል።​—ዘፀአት 22:22-24

በሕዝቅኤል ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ድርጊቶችን በመፈጸም በፍቅር ላይ የተመሠረቱትን የአምላክ ሕግጋት አቃልለዋል። ታዲያ ይሖዋ ምን ያደርግ ይሆን? ይሖዋ “መዓቴን አፈስባቸዋለሁ” በማለት ተናግሯል። (ቁጥር 31) አምላክ፣ ባቢሎናውያን በ607 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌምን እንዲደመስሱና ሕዝቡን በምርኮ እንዲወስዱ በማድረግ የተናገረውን ቃል ፈጽሟል።

ሕዝቅኤል ያሰፈረው ሐሳብ ስለ ይሖዋና ስለ ፍትሕ መጓደል ሁለት ቁም ነገሮችን ያስገነዝበናል። አንደኛ፣ አምላክ የፍትሕ መጓደልን ይጠላል፤ ሁለተኛ ደግሞ በፍትሕ መጓደል ምክንያት በደል ለሚደርስባቸው ሰዎች ይራራል። አምላክ አሁንም አልተለወጠም። (ሚልክያስ 3:6) በቅርቡ የፍትሕ መጓደልን እንዲሁም ለዚህ ምክንያት የሆኑትን ሁሉ ለማስወገድ ቃል ገብቷል። (ምሳሌ 2:21, 22) ታዲያ ‘ፍትሕን ስለሚወደው’ አምላክና ወደ እሱ መቅረብ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ይበልጥ ለማወቅ ለምን ጥረት አታደርግም?​—መዝሙር 37:28

በነሐሴ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

ከሕዝቅኤል 21 እስከ 38

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ይሖዋ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች ሥልጣናቸውን ፈጽሞ አላግባብ መጠቀም እንደሌለባቸው በግልጽ ተናግሯል