በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙስናን ማጥፋት ያልተቻለው ለምንድን ነው?

ሙስናን ማጥፋት ያልተቻለው ለምንድን ነው?

“ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ።”—መክብብ 8:9

ይህ ጥቅስ፣ ሰብዓዊ አገዛዝ ያስመዘገበውን ታሪክ ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው። ሰብዓዊ አገዛዝ፣ በሰው ልጆች ላይ ይህ ነው የማይባል ሥቃይና መከራ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል። ባለፉት ዘመናት ሁሉ ቀና አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ፍትሕ ለማስፈን ቢጥሩም ስግብግብነትና ሙስና እንቅፋት ሲፈጥሩባቸው ኖረዋል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ሙስናን ማጥፋት ያልተቻለው ለምንድን ነው? ለዚህ በዋነኝነት አስተዋጽኦ ያደረገው ከታች የተዘረዘሩት ሦስት ነገሮች የሚያሳድሩት ጎጂ ተጽዕኖ ነው።

1. ኃጢአት

መጽሐፍ ቅዱስ “[ሁላችንም] የኃጢአት ተገዥዎች” እንደሆንን በግልጽ ይናገራል። (ሮም 3:9) ፈውስ እንደሌለው በዘር የሚተላለፍ በሽታ ኃጢአትም በውስጣችን ‘ይኖራል።’ ኃጢአት በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የሰውን ዘር እንደ ንጉሥ ሲገዛ ቆይቷል። “የኃጢአት ሕግ” ሁልጊዜም በውስጣችን ይሠራል። ይህ የኃጢአት ዝንባሌ ብዙዎች የራሳቸውን ጥቅም እንዲያስቀድሙ ያነሳሳቸዋል፤ አሊያም ቁሳዊ ነገሮችን ለማካበት ወይም ሥልጣን ለማግኘት ትልቅ ቦታ ስለሚሰጡ በሌሎች ላይ ተረማምደውም ቢሆን እነዚህን ነገሮች ለማግኘት እንዲጥሩ ይገፋፋቸዋል።—ሮም 5:21፤ 7:17, 20, 23, 25

2. የምንኖርበት ክፉ ዓለም

ዓለማችን ስግብግብና ራስ ወዳድ በሆኑ ሰዎች የተሞላ ነው። እንዲህ ባለው ዓለም ውስጥ አንዳንዶች ለየት ብሎ መታየት ይከብዳቸዋል። ራስ ወዳድ መሆናቸው ለሥልጣን እንዲቋምጡ ያደርጋቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከሚያስፈልጋቸው በላይ ገንዘብና ንብረት የማግበስበስ ከፍተኛ ፍላጎት ያድርባቸዋል። የሚያሳዝነው ነገር እንዲህ ያሉት ሰዎች እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ሲሉ ሐቀኝነት የጎደለው ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። እነዚህ ሰዎች ጎጂ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም ከመጣር ይልቅ “ክፉ በማድረግ ብዙዎችን [ይከተላሉ።]”—ዘፀአት 23:2

3. ሰይጣን ዲያብሎስ

ሰይጣን የተባለው ዓመፀኛ መንፈሳዊ ፍጡር “መላውን ዓለም እያሳሳተ” ነው። (ራእይ 12:9) ሰይጣን የሰው ልጆችን በቁጥጥሩ ሥር ማድረግ ያስደስተዋል። መሠሪ የሆነው ይህ ፍጡር፣ የሰው ልጆች በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ምቹና የተደላደለ ሕይወት ለመምራት ያላቸውን ተፈጥሯዊ ፍላጎት ተጠቅሞ የማታለል ድርጊት እንዲፈጽሙ ሊያነሳሳቸው ይችላል።

ታዲያ ይህ ሲባል ሰይጣን እጁ ላይ እንዳሉ አሻንጉሊቶች እንደፈለገ ሊያሽከረክረን ይችላል ማለት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።