ጥያቄ 3፦ አምላክ መከራ እንዲደርስብኝ የሚፈቅደው ለምንድን ነው?
የኢየን አባት ጠጪ ነበር። ኢየን ከልጅነቱ ጀምሮ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ምንም ባያጣም ይጓጓለት የነበረውን የአባቱን ፍቅር ግን አግኝቶ አያውቅም። ኢየን “አባቴ ጠጪ በመሆኑና እናቴን ይበድላት ስለነበር ለእሱ ምንም ፍቅር አልነበረኝም” በማለት ይናገራል። ኢየን እያደገ ሲሄድ አምላክ መኖሩን መጠራጠር ጀመረ። “‘በእርግጥ አምላክ ካለ ሰዎች መከራ እንዲደርስባቸው የሚፈቅደው ለምንድን ነው?’ ብዬ አስብ ነበር” ብሏል።
ይህ ጥያቄ የሚነሳው ለምንድን ነው?
የአንተ ሕይወት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ችግር የሌለበት ቢሆንም እንኳ ንጹሐን ሰዎች ሲሠቃዩ ስትመለከት ፍትሕ መዛባቱ ያንገበግብህ ይሆናል። ‘አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ይበልጥ የሚያሳስብህ ግን አንተም እንደ ኢየን በራስህ ላይ መከራ ሲደርስ ወይም የምትወደው ሰው ሲታመም አሊያም ሲሞት ነው።
አንዳንዶች ምን መልስ ይሰጣሉ?
አንዳንዶች፣ አምላክ መከራ እንዲደርስብን የሚፈቅደው ትሑትና ርኅሩኅ እንድንሆን ሊያስተምረን እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ ሰዎች በአሁኑ ሕይወት መከራ የሚደርስባቸው ከመወለዳቸው በፊት በነበረው የቀድሞ ሕይወታቸው ኃጢአት ስለሠሩ እንደሆነ ያምናሉ።
መልሳቸው ምን አንድምታ አለው?
አምላክ በሰዎች ላይ ስለሚደርሰው ሥቃይ ምንም ደንታ የለውም፤ እንዲሁም ጨካኝ ነው። በመሆኑም እንዲህ ያለውን አምላክ መውደድ አስቸጋሪ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራ አምላክ ተጠያቂ እንዳልሆነ በግልጽ ይናገራል። “ማንም ሰው ፈተና በሚደርስበት ጊዜ ‘አምላክ እየፈተነኝ ነው’ አይበል። ምክንያቱም አምላክ በክፉ ነገሮች ሊፈተን አይችልም፤ እሱ ራሱም ማንንም አይፈትንም።” (ያዕቆብ 1:13) እንዲያውም አምላክ በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው መከራ ተጠያቂ እንደሆነ የሚገልጸው ሐሳብ ስለ አምላክ ባሕርይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተገለጸው ነገር ጋር አይስማማም። እንዴት?
ከአምላክ ዋነኛ ባሕርያት አንዱ ፍቅር ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህን ነጥብ ለማጉላት ሲባል አምላክ የምታጠባ እናት ያላት ዓይነት ስሜት እንዳለው ተደርጎ ተገልጿል። አምላክ “እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለችን? ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን?” የሚል ጥያቄ ካቀረበ በኋላ “ምናልባት እርሷ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን አልረሳሽም” ብሏል። (ኢሳይያስ 49:15) አንዲት አፍቃሪ እናት ሆን ብላ ልጇን የሚጎዳ ነገር ታደርጋለች ብሎ ማሰብ ይከብዳል። እንዲያውም ልጇን የምትወድ እናት የልጇን ሥቃይ ለማስታገሥ የምትችለውን ሁሉ ታደርጋለች። አምላክም ቢሆን በንጹሐን ሰዎች ላይ መከራ አያመጣም።—ዘፍጥረት 18:25
እርግጥ ነው፣ አምላክ ለሰዎች የሚያስብ ቢሆንም እንኳ ንጹሐን ሰዎች አሁንም መከራ እየደረሰባቸው ነው። ‘ታዲያ አምላክ የሚያስብልን ከሆነና ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ኃይል ካለው ለመከራ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ለምን አያስወግዳቸውም?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።
አምላክ በአሁኑ ጊዜ መከራ እንዲቀጥል የፈቀደው በቂ ምክንያት ስላለው ነው። ከምክንያቶቹ አንዱን እንመልከት፦ ብዙውን ጊዜ በሌሎች ላይ መከራ የሚያደርሱት ራሳቸው ሰዎች ናቸው። በሌሎች ላይ መከራና ሥቃይ የሚያደርሱ በርካታ ጨካኝና አምባገነን ሰዎች አካሄዳቸውን ለመለወጥ ፈቃደኞች አይደሉም። ስለዚህ አምላክ የመከራን ዋነኛ መንስኤ ለማስወገድ እንዲህ ያሉትን ሰዎች ማጥፋት ይኖርበታል።
ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ አምላክ መጥፎ ሰዎችን እስካሁን ድረስ ያላጠፋበትን ምክንያት ሲገልጽ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ይሖዋ የገባውን ቃል ለመፈጸም አይዘገይም፤ ይሁንና እናንተን የታገሠው፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው።” (2 ጴጥሮስ 3:9) ይሖዋ አምላክ ትዕግሥተኛ መሆኑ አፍቃሪና መሐሪ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
ይሁንና በቅርቡ ይሖዋ አምላክ እርምጃ ይወስዳል። በንጹሐን ሰዎች ላይ ‘መከራን ለሚያመጡ በአጸፋው መከራን ይከፍላቸዋል።’ በሌሎች ላይ ግፍ የሚፈጽሙ ሰዎች “ዘላለማዊ ጥፋት [ይፈረድባቸዋል]።”—2 ተሰሎንቄ 1:6-9
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኢየን መከራን በተመለከተ ለነበሩት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ አግኝቷል። የተማረው ነገር ለሕይወት የነበረውን አመለካከት ለወጠው። የእሱን ታሪክ “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በሚለው ርዕስ ላይ ማግኘት ትችላለህ።