በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ አምላክ ቅረብ

‘ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው?’

‘ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው?’

ይሖዋ፣ እሱን በሚያስደስተው መንገድ ሊያመልኩት ከሚፈልጉ ሰዎች ምን ይጠብቃል? ፍጹም እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል? እንዲህ ቢሆን ኖሮ ማንኛውም ፍጽምና የጎደለው ሰው እሱን ጨርሶ ማስደሰት አይችልም ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው የአቅማችንን ያህል እንድናደርግ ይሆን? አምላክን በማገልገል ደስታ ማግኘት ከፈለግን የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቃችን አስፈላጊ ነው። ነቢዩ ሚክያስ፣ አምላክ ከአገልጋዮቹ የሚፈልገውን ነገር ጠቅለል አድርጎ የገለጸው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።—ሚክያስ 6:8ን አንብብ።

“መልካም የሆነውን አሳይቶሃል።” አምላክ ከእኛ የሚጠብቀው ምን እንደሆነ መገመት አያስፈልገንም። ከእኛ የሚፈልገውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ነግሮናል። ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው “መልካም የሆነውን” ነገር ነው። ደግሞም መልካም ያልሆነ ነገር እንድናደርግ አይጠብቅብንም። “አምላክ ፍቅር [ስለሆነ]” ምንጊዜም የሚያስበው ለእኛ የሚጠቅመንን ነው። (1 ዮሐንስ 4:8፤ 5:3) ይሖዋ የሚጠብቅብንን ስናደርግ እሱን የምናስደስት ከመሆኑም በላይ ራሳችንንም እንጠቅማለን።—ዘዳግም 10:12, 13

“እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው?” አምላክ፣ አንድ ነገር እንድናደርግ የመጠበቅ መብት አለው? እንዴታ! ሕይወት የሰጠንና በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች የሚያቀርብልን እሱ በመሆኑ ልንታዘዘው ይገባል። (መዝሙር 36:9) ታዲያ ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? ሚክያስ፣ አምላክ ከእኛ የሚፈልገውን ነገር በሦስት ሐረጎች ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሐረጎች ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት የሚነኩ ሲሆኑ ሦስተኛው ደግሞ ከአምላክ ጋር ያለንን ግንኙነት የሚመለከት ነው።

“ፍትሕን ታደርግ ዘንድ።” አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው “ፍትሕ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ትክክለኛ እና የማያዳሉ መሆንን ይጨምራል።” አምላክ፣ በእሱ መሥፈርት መሠረት ትክክለኛ በሆነና አድልዎ በሌለበት መንገድ ሌሎችን እንድንይዝ ይፈልግብናል። ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ባለማዳላት፣ ትክክለኛ የሆነውን ነገር በማድረግና ሐቀኛ በመሆን ፍትሕን ማድረግ እንችላለን። (ዘሌዋውያን 19:15፤ ኢሳይያስ 1:17፤ ዕብራውያን 13:18) ለሌሎች ፍትሕን የምናደርግ ከሆነ እነሱም በምላሹ ለእኛ ፍትሕን ለማድረግ ይነሳሳሉ።—ማቴዎስ 7:12

“ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ።” አምላክ ምሕረትን ወይም ደግነትን እንድናሳይ ብቻ ሳይሆን እንድንወድድም ይፈልግብናል። እዚህ ጥቅስ ላይ “ምሕረት” (ሄሴድ) ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ፍቅራዊ ደግነት” ወይም “ታማኝ ፍቅር” ሊባልም ይችላል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “[ሄሴድ] የሚለውን ቃል ፍቅር፣ ምሕረት እና ደግነት በተናጠል በደንብ ሊገልጹት አይችሉም፤ ይህ ባሕርይ ሦስቱንም ነገሮች ያጠቃልላል።” ምሕረትን ወይም ደግነትን የምንወድድ ከሆነ በራሳችን ተነሳስተን ይህንን ባሕርይ እናሳያለን፤ እንዲሁም እርዳታ የሚያሻቸውን መርዳት ያስደስተናል። እንዲህ በማድረጋችንም መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ እናጭዳለን።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

“በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ።” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘መራመድ’ ወይም ‘መሄድ’ የሚለው ቃል “አንድን ዓይነት አካሄድ መከተል” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። አምላክ ሕይወታችንን የምንመራበትን መንገድ በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሰፈረልንን ብቃቶች በመከተል ከእሱ ጋር መራመድ ወይም መሄድ እንችላለን። እንዲህ ያለውን አካሄድ ስንከተል ‘ትሑቶች’ መሆን አለብን። ትሕትና የምናሳየው እንዴት ነው? በአምላክ ፊት ትሕትና ለማሳየት የእሱ ፍጥረታት መሆናችንን እና የአቅም ገደብ ያለብን መሆኑን በሐቀኝነት መገንዘብ አለብን። በመሆኑም ከአምላክ ጋር ‘በትሕትና መራመድ’ ማለት እሱ ከእኛ ስለሚጠብቀውና እኛ ልንሰጠው ስለምንችለው ነገር ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር ማለት ነው።

ደስ የሚለው ነገር ይሖዋ ከአቅማችን በላይ እንድናደርግ ፈጽሞ አይጠብቅብንም። እሱን በሙሉ ልባችን ለማገልገል የምናደርገውን ጥረት ያደንቃል። (ቆላስይስ 3:23) አቅማችን ውስን እንደሆነ ይረዳልናል። (መዝሙር 103:14) እኛም ትሑቶች በመሆን ይህን አምነን ከተቀበልን ከእሱ ጋር በመራመድ ወይም በመሄድ ደስታ እናገኛለን። አንተስ ከአምላክ ጋር ለመሄድ ልትወስደው የሚገባው የመጀመሪያ እርምጃ ምን እንደሆነ ለምን አትመረምርም? እንዲህ ያለው አካሄድ የአምላክን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝልሃል።—ምሳሌ 10:22

በኅዳር ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

ከኢዩኤል 1-3 እስከ ሚክያስ 1-7