በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

“አየሁ፤ ነገር ግን አላስተዋልሁትም”

“አየሁ፤ ነገር ግን አላስተዋልሁትም”

እናቴ፣ የሆነ ችግር እንዳለብኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የጠረጠረችው በ1975 የሁለት ዓመት ልጅ ሳለሁ ነው። እናቴ አቅፋኝ ሳለ አንዲት ጓደኛዋ ከባድ ዕቃ ከእጇ ላይ ወድቆ ኃይለኛ ድምፅ ያሰማል። ሆኖም ይህ ድምፅ ቅንጣት ታክል እንዳላስደነገጠኝ እናቴ አስተዋለች። እንዲሁም ሦስት ዓመት ቢሞላኝም መናገር አልችልም ነበር። ከዚያም ቤተሰቤ አንድ አስደንጋጭ ዜና ሰማ፤ የሕክምና ባለሙያዎች ጭራሽ መስማት እንደማልችል አረጋገጡ!

ገና ሕፃን ሳለሁ ወላጆቼ ስለተፋቱ እናቴ እኔንና ታላላቆቼን ማለትም ሁለት ወንድሞቼንና እህቴን ብቻዋን ለማሳደግ ተገደደች። በዚያን ጊዜ በፈረንሳይ መስማት የማይችሉ ልጆች የሚማሩት እንደ አሁኑ አልነበረም፤ በወቅቱ የነበረው የማስተማር ዘዴ አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትል ነበር። ያም ሆኖ፣ ከልጅነቴ ጀምሮ መስማት የተሳናቸው ብዙ ሰዎች ያላገኙትን አጋጣሚ አግኝቻለሁ። ስለዚህ ጉዳይ እስቲ ላጫውታችሁ።

የአምስት ዓመት ገደማ ልጅ ሳለሁ

ከዚህ በፊት ብዙ የትምህርት ባለሙያዎች መስማት የተሳናቸው ልጆች መማር ያለባቸው ከንፈር በማንበብ መሆን እንዳለበትና መናገር እንዳለባቸው ያምኑ ነበር። እንዲያውም በፈረንሳይ፣ በትምህርት ቤት ውስጥ የምልክት ቋንቋ መጠቀም ፈጽሞ የተከለከለ ነበር። አልፎ ተርፎም አንዳንድ መስማት የተሳናቸው ልጆች በትምህርት ሰዓት ሐሳባቸውን በምልክት እንዳይገልጹ እጃቸው የኋሊት ይታሰር ነበር።

ገና በልጅነቴ ከንግግር ችሎታ ጋር ለሚገናኙ ችግሮች ሕክምና ከምትሰጥ አንዲት ባለሙያ ጋር በየሳምንቱ ረጅም ሰዓት አሳልፍ ነበር። የማወጣውን ድምፅ መስማት ባልችልም አገጬን ወይም ራሴን ተይዤ አንዳንድ ድምፆችን ደጋግሜ እንድጠራ እገደድ ነበር። ከሌሎች ልጆች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ አልችልም ነበር። እነዚያ ዓመታት ለእኔ የሥቃይ ዘመናት ነበሩ።

ከዚያም ስድስት ዓመት ሲሞላኝ ልዩ ሥልጠና ወደሚሰጥበት አዳሪ ትምህርት ቤት ገባሁ። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ መስማት ከተሳናቸው ልጆች ጋር የተገናኘሁት በዚህ ጊዜ ነበር። በዚያም ቢሆን የምልክት ቋንቋ መጠቀም ክልክል ነበር። በክፍል ውስጥ ሐሳብ ለመለዋወጥ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ስናደርግ ከታየን እጃችንን ይመቱን ወይም ፀጉራችንን ይጎትቱን ነበር። ይሁን እንጂ እኛው ራሳችን የፈጠርናቸውን ምልክቶች በመጠቀም ሳይታወቅብን እንነጋገር ነበር። በመሆኑም በዚህ መንገድ ከሌሎች ልጆች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ቻልኩ። በዚህ ቦታ አራት አስደሳች ዓመታት አሳለፍኩ።

አሥር ዓመት ሲሞላኝ ግን መስማት የሚችሉ ልጆች ወደሚማሩበት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛወርኩ። በዚህ ጊዜ በጣም አዘንኩ! አብሬያቸው ስማር የነበሩት መስማት የተሳናቸው ልጆች በሙሉ እንደሞቱና ብቻዬን እንደቀረሁ ተሰማኝ። ሐኪሞች በምልክት ቋንቋ የሚያናግረኝ ሰው ካገኘሁ መናገር እንድችል ከሚሰጠኝ ሕክምና ምንም ጥቅም እንደማላገኝ ተናግረው ነበር። የቤተሰቤ አባላት፣ ይህን ምክር በመስማት የምልክት ቋንቋ አልተማሩም ነበር፤ መስማት ከተሳናቸው ልጆች ጋር እንድገናኝም አይፈቅዱልኝም ነበር። አንድ የመስማት ችግርን የሚያክም ባለሙያ ዘንድ የሄድኩበትን ጊዜ እስካሁን አስታውሰዋለሁ። በባለሙያው ጠረጴዛ ላይ የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ተቀምጦ ነበር። በመጽሐፉ ሽፋን ላይ ያሉትን ሥዕሎች ሳይ ወደ መጽሐፉ እያመለከትኩ “ይህን መጽሐፍ እፈልገዋለሁ!” አልኩት። ሐኪሙም ቶሎ ብሎ መጽሐፉን ደበቀው። *

መንፈሳዊ ነገሮችን መማር ጀመርኩ

እናቴ በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች መሠረት እኛን ለማሳደግ ጥረት አድርጋለች። በቦርደው አቅራቢያ በሚገኘው የማሪኛክ ጉባኤ የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚያደርጉት ስብሰባ ትወስደን ነበር። በወቅቱ ልጅ ስለነበርኩ ስብሰባው ላይ የሚተላለፈው ትምህርት ብዙም አይገባኝም ነበር። ይሁን እንጂ የጉባኤው አባላት ተራ ገብተው አጠገቤ በመቀመጥ በስብሰባው ላይ የሚነገረውን ነገር እንድከታተል ማስታወሻ ላይ ይጽፉልኝ ነበር። ፍቅራቸውና አሳቢነታቸው ልቤን ነክቶታል። እናቴ፣ ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ታስጠናኝ የነበረ ቢሆንም የምማረውን ነገር ሙሉ በሙሉ ተረድቼ አላውቅም። ከአንድ መልአክ ትንቢት ከተቀበለ በኋላ “ሰማሁ፤ ነገር ግን አላስተዋልሁትም” በማለት ከተናገረው ከነቢዩ ዳንኤል ጋር የሚመሳሰል ስሜት ይሰማኝ ነበር። (ዳንኤል 12:8) እኔ ግን የምለው “አየሁ፤ ነገር ግን አላስተዋልሁትም” ነው።

ያም ቢሆን መሠረታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በልቤ ውስጥ ቀስ በቀስ ሥር መስደድ ጀመረ። በደንብ የገባኝን ትምህርት ከፍ አድርጌ እመለከተው የነበረ ከመሆኑም በላይ ይህን ትምህርት በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ እጥር ነበር። የሌሎችን ምግባር በማየትም እማር ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ታጋሾች እንድንሆን ይነግረናል። (ያዕቆብ 5:7, 8) ትዕግሥት ምን እንደሆነ ብዙም አይገባኝም ነበር። ይሁን እንጂ የእምነት አጋሮቼ ይህን ባሕርይ ሲያሳዩ በመመልከት ትዕግሥት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ችያለሁ። በእርግጥም፣ የክርስቲያን ጉባኤ ካደረገልኝ እገዛ ብዙ ጥቅም አግኝቻለሁ።

ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታና ያልተጠበቀ አስደሳች ነገር

ስቴፋን የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች እንዳስተውል ረድቶኛል

በአሥራዎቹ ዕድሜዬ ውስጥ ሳለሁ አንድ ቀን በመንገድ ላይ መስማት የተሳናቸው ወጣቶች እርስ በርሳቸው በምልክት ቋንቋ ሲነጋገሩ አየሁ። ከእነሱ ጋር በድብቅ መገናኘት የጀመርኩ ሲሆን ፈረንሳይኛ የምልክት ቋንቋ መማር ጀመርኩ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ላይ መገኘቴን የቀጠልኩ ሲሆን ስቴፋን የሚባል አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክርም አሳቢነት ያሳየኝ ጀመር። ከእኔ ጋር ለመነጋገር ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ስለነበር በጣም ቀረብኩት። ይሁን እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ከፊቴ ይጠብቀኝ ነበር። ስቴፋን ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሙን በመጠበቁ ምክንያት ታሰረ። በመሆኑም በጣም አዘንኩ! ስቴፋንን ካጠገቤ በማጣቴ ተስፋ ስለቆረጥኩ በስብሰባዎች ላይ መገኘትን ወደ ማቆም ደርሼ ነበር።

ከአሥራ አንድ ወራት በኋላ ስቴፋን ከእስር ስለተፈታ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ስቴፋን ከእኔ ጋር በምልክት ቋንቋ መነጋገር ሲጀምር ምን ያህል እንደተገረምኩ መገመት ትችላላችሁ። ዓይኔን ማመን አቃተኝ! እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ? ለካስ ስቴፋን እስር ቤት እያለ የፈረንሳይኛ የምልክት ቋንቋ ተምሯል። የእጁን እንቅስቃሴና ፊቱ ላይ የሚነበበውን ስሜት ስመለከት ደስታዬ ይበልጥ እየጨመረ መጣ፤ ምክንያቱም አሁን ስቴፈን እውነትን በሚገባኝ መንገድ ሊያስተምረኝ ይችላል።

በመጨረሻ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መረዳት ቻልኩ

ስቴፋን መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናኝ ጀመር። ቀደም ሲል የተማርኳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ግልጽ የሆኑልኝ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነበር። በልጅነቴ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡትን ውብ ሥዕሎች መመልከት በጣም ያስደስተኝ ነበር፤ ታሪኩ በአእምሮዬ ላይ ታትሞ እንዲቀር ለማድረግ ስል በሥዕሉ ላይ የማያቸውን ሰዎች አነጻጽር እንዲሁም እያንዳንዱን ዝርዝር ነገር እመለከት ነበር። ስለ አብርሃም፣ ስለ ‘ዘሩ’ እና ስለ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” አውቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ የእነዚህ ነገሮች ትርጉም በደንብ የገባኝ በምልክት ቋንቋ ሲብራራልኝ ነው። (ዘፍጥረት 22:15-18፤ ራእይ 7:9) የእኔን ቋንቋ ማለትም ልቤ እንዲነካ የሚያደርገውን ቋንቋ እንዳገኘሁ በግልጽ ይታይ ነበር።

በስብሰባዎች ላይ የሚነገረውን ነገር መረዳት ስጀምር ልቤ የተነካ ከመሆኑም በላይ ለአምላክ ቃል የነበረኝ ጥማት እየጨመረ ሄደ። ስቴፋን ባደረገልኝ እርዳታ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቴ እያደገ በመሄዱ በ1992 ራሴን ለይሖዋ አምላክ ወስኜ ተጠመቅሁ። ጥሩ መንፈሳዊ እድገት እያደረግሁ ብሄድም በልጅነቴ የሐሳብ ልውውጥ አለማድረጌ ዓይናፋር እንድሆን አድርጎኛል።

ዓይናፋርነትን መታገል

መስማት የተሳናቸው ሰዎች ይሰበሰቡበት የነበረው አነስተኛ ቡድን ውሎ አድሮ ከቦርደው ከተማ ወጣ ብሎ ከሚገኘው የፔሳክ ጉባኤ ጋር ተቀላቀለ። ይህ ደግሞ በጣም የረዳኝ ሲሆን መንፈሳዊ እድገት ማድረጌን ቀጠልኩ። ምንም እንኳ ሐሳቤን መግለጽ የሚከብደኝ ቢሆንም ጓደኞቼ የሚሰጠው ትምህርት በደንብ እንዲገባኝ ለማድረግ ይጥሩ ነበር። ጃየልስ እና ኤሎዲ የሚባሉ አንድ ባልና ሚስት ከእኔ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ ልዩ ጥረት ያደርጉ ነበር። ብዙ ጊዜ ከስብሰባዎች በኋላ ከእነሱ ጋር አብሬ እንድመገብ ወይም ቡና እንድጠጣ ይጋብዙኝ ስለነበረ ግሩም ወዳጅነት መሠረትን። የአምላክን የፍቅር መንገድ በሚከተሉ ሰዎች መካከል መሆን ምንኛ አስደሳች ነው!

ባለቤቴ ቨኔሳ ጥሩ ድጋፍ ሆናልኛለች

የደስ ደስ ያላትን ቨኔሳ የተባለች እህት የተዋወቅኩት በዚህ ጉባኤ ነው። ለሌሎች ያላት አሳቢነትና ፍትሕ ወዳድ መሆኗ ማረከኝ። መስማት የተሳነኝ መሆኑ ከእኔ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ አላገዳትም፤ እንዲያውም መስማት ከተሳናቸው ሰዎች ጋር ለመግባባት እንደሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ አድርጋ ትመለከተው ነበር። ቨኔሳን ስላፈቀርኳት በ2005 ተጋባን። ከሰዎች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የሚቸግረኝ ቢሆንም ቨኔሳ ዓይናፋርነቴን እንዳሸንፍና ስሜቴን በግልጽ እንድናገር ረድታኛለች። ኃላፊነቴን ለመወጣት በማደርገው ጥረት ድጋፍ ስለምታደርግልኝ ከልቤ አደንቃታለሁ።

ከይሖዋ ያገኘሁት ሌላ ስጦታ

እኔና ቨኔሳ በተጋባንበት ዓመት በፈረንሳይ፣ ሉቪዬ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ለትርጉም ሥራ የአንድ ወር ሥልጠና እንድወስድ ተጋበዝኩ። ከዚህ በፊት በነበሩት ዓመታት ቅርንጫፍ ቢሮው ብዙ ጽሑፎችን በፈረንሳይኛ የምልክት ቋንቋ በዲቪዲ ለማዘጋጀት ጠንክሮ እየሠራ ነበር። ይሁን እንጂ የትርጉም ቡድኑ ገና ብዙ ሥራ ስለሚጠብቀው መጠናከር ያስፈልገው ነበር፤ በመሆኑም በትርጉም ሥራው እንድካፈል ተጋበዝኩ።

በፈረንሳይኛ የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ስሰጥ

እኔና ቨኔሳ በቅርንጫፍ ቢሮው እንዳገለግል መጋበዜ ትልቅ መብትና ከይሖዋ የተገኘ ስጦታ እንደሆነ ተሰማን። ይሁን እንጂ ስለሚከተሉት ነገሮች ስጋት አድሮብን ነበር፦ የምልክት ቋንቋ ቡድናችን ምን ይሆናል? ቤታችንንስ ምን እናደርገዋለን? ቨኔሳ በአካባቢው ሥራ ታገኝ ይሆን? ደስ የሚለው፣ ይሖዋ አስገራሚ በሆነ መንገድ ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሔ ሰጠን። ይሖዋ እኛንም ሆነ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች እንደሚወድ ይበልጥ ግልጽ ሆነልኝ።

አንድነት ያለው ሕዝብ የሰጠኝ ድጋፍ

በትርጉም ሥራ ውስጥ መግባቴ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች በመንፈሳዊ ለመርዳት እየተደረገ ያለውን ጥረት በተሻለ ሁኔታ እንድረዳ አስችሎኛል። አብረውኝ የሚሠሩ በርካታ የእምነት ባልንጀሮቼ ከእኔ ጋር ለመግባባት ጥረት ሲያደርጉ ማየቴ እጅግ አስደስቶኛል! የሚያውቁት ጥቂት ቃላት ቢሆንም በምልክት ቋንቋ እኔን ለማናገር ሲጥሩ ማየቴ ልቤን ነክቶታል። አሁን ፈጽሞ ብቸኝነት አይሰማኝም። እነዚህ ሁሉ የፍቅር መግለጫዎች በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለውን አስደናቂ አንድነት የሚያሳዩ ናቸው።—መዝሙር 133:1

በቅርንጫፍ ቢሮው በትርጉም ክፍል ስሠራ

ይሖዋ ምንጊዜም በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት የሚረዳኝ ሰው እንዳገኝ ስላደረገ አመሰግነዋለሁ። በተጨማሪም እንደ እኔ መስማት የተሳናቸው ሌሎች ሰዎችን ስለ አፍቃሪው ፈጣሪያችን እንዲያውቁና ወደ እሱ እንዲቀርቡ በመርዳቱ ሥራ የራሴን ትንሽ አስተዋጽኦ ማበርከት በመቻሌ አመስጋኝ ነኝ። የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮች በሙሉ ተወግደው ሁሉም ሰዎች አንድነት ያለው ሰብዓዊ ቤተሰብ አባላት በመሆን ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጸውን እውነት የሚያመለክተውን “ንጹሑን ልሳን” የሚናገሩበትን ቀን በናፍቆት እጠባበቃለሁ።—ሶፎንያስ 3:9

^ አን.9 የፈረንሳይ መንግሥት መስማት የተሳናቸውን ልጆች ለማስተማር በምልክት ቋንቋ መጠቀምን እስከ 1991 ድረስ በይፋ አልፈቀደም ነበር።