መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
“ቄስ የመሆን ፍላጎት ነበረኝ”
የትውልድ ዘመን፦ 1957
የትውልድ አገር፦ ሜክሲኮ
የኋላ ታሪክ፦ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብቶ የተማረ እና ግልፍተኛ የነበረ
የቀድሞ ሕይወቴ፦
የተወለድኩት ቴክስኮኮ በተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው። በወቅቱ በከተማይቱ ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ መንገዶች በደንብ ያልተሠሩና አቧራማ ነበሩ። በአቅራቢያው ባሉት መንደሮች ያሉ ነዋሪዎች ሸቀጦቻቸውን በአህያ ጭነው ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ ገበያ ይመጡ ነበር። ቤተሰቦቼ በጣም ድሆች ነበሩ፤ ስምንት ወንድሞች እና እህቶች ያሉኝ ሲሆን እኔ ሰባተኛ ልጅ ነኝ። አባቴ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ጉዋራቼስ የተባሉትን የአካባቢው ሰዎች የሚያደርጓቸውን ጫማዎች በመጠገን ነበር። ይሁን እንጂ ገና የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ አባቴ ሞተ። በመሆኑም እናቴ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ ትታገል ጀመር።
አያቴ ቫዮሊን ይጫወት የነበረ ሲሆን መንፈሳዊ መዝሙሮችን የሚጫወት ኦርኬስትራ መሪ ነበር። አብዛኞቹ የቤተሰባችን አባላት አንድ ዓይነት የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት ይችላሉ። እናቴ የቤተ ክርስቲያን መዘምራን ቡድን አባል ነበረች፤ አጎቴ ደግሞ የኦፔራ ዘፋኝ ከመሆኑም ሌላ ፒያኖ ይጫወት ነበር። ቤተሰባችን አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነበር፤ እኔም ከልጅነቴ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገለግል የነበረ ሲሆን የካቶሊክ ሚስዮናዊ የመሆን ፍላጎት ነበረኝ። በሌላ በኩል ደግሞ የካራቴ ፊልሞችን ማየት በጣም እወድ ነበር። እነዚህን ፊልሞች አዘውትሬ እመለከት ስለነበር ዓመፀኛ እየሆንኩ ሄድኩ።
ከጊዜ በኋላ ፑዌብላ በሚገኝ አንድ መንፈሳዊ ኮሌጅ ውስጥ ገብቼ መማር ጀመርኩ። በወቅቱ የካቶሊክ ቄስ የመሆን ግብ ነበረኝ። ይሁን እንጂ ትምህርቴን በማጠናቅቅበት ዓመት በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ላይ የነበረኝ እምነት ጠፋ። በዚህ ወቅት አንዲት ወጣት መነኩሴ ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት እንድፈጽም የሚጋብዙ ነገሮችን ታደርግ ጀመር። እሷ ላቀረበችልኝ ግብዣ ባልሸነፍም ሁኔታው የማግባት ፍላጎት እንዲያድርብኝ አደረገ። ከዚህም ሌላ በርካታ ቄሶች ግብዞች እንደሆኑ አስተዋልኩ። በመሆኑም ቄስ ለመሆን የነበረኝን ፍላጎት እርግፍ አድርጌ ተውኩ።
በልጅነቴ በቤተ ክርስቲያን አገለግል የነበረ ሲሆን የካቶሊክ ሚስዮናዊ የመሆን ግብ ነበረኝ፤ በሌላ በኩል ግን የካራቴ ፊልሞችን እወድ ስለነበር ዓመፀኛ እየሆንኩ መጣሁ
ከዚያም በሜክሲኮ ሲቲ በሚገኝ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብቼ ለመሠልጠን ወሰንኩ። ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ አግብቼ አራት ልጆች ወለድኩ። ቤተሰቤን የማስተዳድረው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመዘመር በማገኘው ገቢ ነበር።
ትዳራችን ገና ከጅምሩ ሰላም አልነበረውም። እኔና ባለቤቴ ስለምንቀናና ብዙ ጊዜ እንጣላ ነበር። መጀመሪያ ላይ እንሰዳደብ ነበር፤ በኋላ ግን መደባደብ ጀመርን። በትዳር 13 ዓመት አብረን ካሳለፍን በኋላ በመጨረሻ ለመለያየት ወሰንን፤ በኋላም ተፋታን።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘሁት ከባለቤቴ ጋር ከመለያየቴ በፊት ነው። ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን መጥተው ከእነሱ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንድንወያይ ግብዣ አቀረቡልን። ስለ ሃይማኖት ብዙ እንደማውቅ ይሰማኝ ስለነበር እነዚህ ሰዎች እንደተሳሳቱ ለማሳየት ፈለግሁ። በመሆኑም መልስ እንደማያገኙላቸው ያሰብኳቸውን ከባድ ጥያቄዎች ጠየቅኳቸው። የይሖዋ ምሥክሮቹ ለጥያቄዎቼ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አጥጋቢ መልስ ሲሰጡኝ ግን በጣም ተገረምኩ። ምንም ያህል እንደማላውቅ የተገነዘብኩት በዚህ ወቅት ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ በሥራ በጣም ተጠምጄ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ባለቤቴ የይሖዋ ምሥክሮቹን ትጠላቸው ስለነበር ወደ ቤታችን መምጣት አቆሙ።
ከአምስት ዓመታት በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንደገና ተገናኘሁ፤ በወቅቱ ኤልቪራ ከተባለች ሌላ ሴት ጋር መኖር ጀምሬ ነበር። ኤልቪራ የይሖዋ ምሥክሮችን ስለማትቃወም ከእነሱ ጋር በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ቻልኩ። እንደዚያም ሆኖ በአኗኗሬ ላይ ለውጥ ለማድረግ በርካታ ዓመታት ፈጅቶብኛል።
ይሖዋን በሙሉ ልቤ ማምለክ ከፈለግሁ በሕይወቴ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። በመጀመሪያ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መዘመሬን ማቆም ነበረብኝ፤ ይህም ሌላ ዓይነት መተዳደሪያ መፈለግ ይጠይቅብኝ ነበር። (ራእይ 18:4) ከዚህም ሌላ ከኤልቪራ ጋር ጋብቻችንን ሕጋዊ ማድረግ ነበረብን።
ከሁሉ የበለጠ ተፈታታኝ የሆነብኝ ግን ቁጣዬን መቆጣጠር ነው። በዚህ ረገድ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ረድተውኛል፤ አንደኛው ጥቅስ መዝሙር 11:5 ሲሆን ይሖዋ ዓመፅን እንደሚጠላ ይናገራል፤ በ1 ጴጥሮስ 3:7 ላይ የሚገኘው ጥቅስ ደግሞ ይሖዋ ጸሎቴን እንዲሰማ ከፈለግሁ ባለቤቴን ማክበር እንዳለብኝ አስገንዝቦኛል። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ አሰላስል እንዲሁም ይሖዋ እንዲረዳኝ እጸልይ ስለነበር ቀስ በቀስ ቁጣዬን መቆጣጠር ቻልኩ።
ይሖዋ ጸሎቴን እንዲሰማልኝ ከፈለግኩ ባለቤቴን ማክበር እንዳለብኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምሬያለሁ
ያገኘሁት ጥቅም፦
አሁን በቤተሰብ ሕይወቴ ደስተኛ ነኝ። ከመጀመሪያዋ ባለቤቴ ከወለድኳቸው ወንዶች ልጆቼ ጋር ያለኝን ግንኙነት ለማሻሻል እንዲሁም አሁን ያለኝ ቤተሰብ በመንፈሳዊ ጠንካራ እንዲሆን ለመርዳት ጥረት እያደረግሁ ነው።
ትንሽ ልጅ እያለሁ ቄስ የመሆን እና ሰዎችን የመርዳት ፍላጎት ነበረኝ። አሁን ግን ትርጉም ያለው ሕይወት እየመራሁ እንደሆነ ይሰማኛል። ቤተሰቤን የማስተዳድረው ሙዚቃ በማስተማር ነው። ይሖዋ ትዕግሥቱን በማሳየት ለውጥ ለማድረግ እና የተሻልኩ ሰው ለመሆን የሚያስችል አጋጣሚ ስለሰጠኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ!