በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ምንድን ነው?

ወደ ሕልውና የመጣነው እንዴት ነው?

ወደ ሕልውና የመጣነው እንዴት ነው?

የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ፣ አጽናፈ ዓለም ከየት እንደመጣ በአጭሩ ሲገልጽ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትና ምድርን ፈጠረ” ይላል። (ዘፍጥረት 1:1) አምላክ፣ ዕፅዋትንና እንስሳትን ከፈጠረ በኋላ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ይኸውም አዳምንና ሔዋንን ፈጠረ። እነዚህ ባልና ሚስት፣ የመምረጥ ነፃነትን ጨምሮ በተወሰነ ደረጃ የአምላክን ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ ስለተሰጣቸው ከእንስሳት የተለዩ ነበሩ። ይህ ደግሞ፣ ለሚወስዷቸው እርምጃዎች በኃላፊነት እንዲጠየቁ ያደርጋል። የአምላክን መመሪያ ቢታዘዙ አምላክ ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆች በምድር ላይ ለዘላለም በሰላም እንዲኖሩ ባለው ዓላማ መሠረት ከዘሮቻቸው ጋር መኖር ይችላሉ።

ይሁን እንጂ አንድ መልአክ ወይም መንፈሳዊ ፍጡር በሰው ልጆች ተጠቅሞ የራሱን ጥቅም ለማራመድ ሞከረ። ይህን በማድረጉም፣ ሰይጣን ማለትም “ተቃዋሚ” ሆነ። ሰይጣን በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን ያናገራት ሲሆን ያለአምላክ መመሪያ ብትኖር ሕይወቷ የተሻለ እንደሚሆን በመግለጽ አታለላት። አዳምና ሔዋን ሰይጣንን ተከትለው ከፈጣሪያቸው ጋር የነበራቸውን ዝምድና አፈረሱ። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን መጥፎ ውሳኔ በማድረጋቸው ፍጻሜ የሌለው ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ አጡ፤ ከዚህም ሌላ ለሁላችንም ኃጢአትን፣ አለፍጽምናንና ልናመልጠው የማንችለውን ሞትን አወረሱን።

ወዲያውኑ አምላክ፣ ይህን አሳዛኝ ሁኔታ ለማስተካከልና የአዳም ዘሮች ፍጻሜ የሌለው ሕይወት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ለማዘጋጀት እንዳሰበ ገለጸ። አምላክ አንድ ‘ዘር’ ማለትም ለየት ያለ ቦታ የተሰጠው አንድ ግለሰብ ሰይጣንን በማጥፋት ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን ያስከተሉትን መከራ እንደሚያስወግድ ትንቢት ተናገረ። (ዘፍጥረት 3:15) ያ ‘ዘር’ ማን ይሆን? ይህ ጊዜው ሲደርስ የሚታወቅ ነገር ነበር።

እስከዚያ ድረስ ግን ሰይጣን የአምላክን በጎ ዓላማ ለማክሸፍ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል። ክፉ ሰዎች እየበዙ ሄዱ። በመሆኑም አምላክ ክፉዎችን በውኃ ለማጥፋት ወሰነ። አምላክ፣ መርከብ ይኸውም ግዙፍ የሆነ ተንሳፋፊ ሣጥን እንዲሠራ ጻድቁን ኖኅን አዘዘው፤ በዚህ መርከብ አማካኝነት ኖኅ፣ ቤተሰቡና ወደ መርከቡ ያስገባቸው እንስሳት ከጥፋቱ ይተርፋሉ።

የጥፋት ውኃው ከመጣ ከአንድ ዓመት በኋላ ኖኅና ቤተሰቡ ከመርከቡ ወጥተው በጸዳች ምድር ላይ መኖር ጀመሩ። ይሁን እንጂ ‘ዘሩ’ ገና አልመጣም ነበር።

በዘፍጥረት ምዕራፍ 1-11፣ በይሁዳ 6, 14, 15 እና በራእይ 12:9 ላይ የተመሠረተ