ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆቻችሁ ጋር ሳትጨቃጨቁ መነጋገር
“ልጄ 14 ዓመት ሲሆናት ከእኔ ጋር እኩል መመላለስ ጀመረች። ለምሳሌ ‘ራት ቀርቧል’ ስላት ‘አሁን አላሰኘኝም፤ ስፈልግ እበላለሁ’ ትለኛለች። የቤት ውስጥ ሥራዎቿን ጨርሳ እንደሆነ ስጠይቃት ‘ኡፋ፣ እንግዲህ አትጨቅጭቂኝ!’ ብላ ትመልስልኛለች። በዚህ የተነሳ ብዙ ጊዜ የምንጨቃጨቅ ከመሆኑም ሌላ እንጯጯሃለን።”—ማኪ፣ ጃፓን *
በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ካላችሁ ከምንም በላይ አስቸጋሪ የሚሆንባችሁ እንዲሁም ትዕግሥታችሁን የሚፈታተነው ነገር ከልጃችሁ ጋር የሚፈጠረው ጭቅጭቅ ሊሆን ይችላል። * በብራዚል የምትኖረውና የ14 ዓመት ልጅ ያላት ማሪያ እንዲህ ብላለች፦ “ልጄ ሥልጣኔን ለመቀበል ስታንገራግር ደሜ ይፈላል። ሁለታችንም በጣም ስለምንበሳጭ መጯጯህ እንጀምራለን።” በጣሊያን የምትኖረው ካርሜላም ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሟታል። እንዲህ ብላለች፦ “ከልጄ ጋር የማንግባባበት ነገር ሲያጋጥመን ሁልጊዜ እንደተነታረክን ነው፤ በመጨረሻም ክፍሉ ገብቶ በሩን ይዘጋብኛል።”
በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ አንዳንድ ልጆች መሟገት የሚወዱት ለምንድን ነው? እንዲህ የሚሆኑት በእኩዮች ተጽዕኖ የተነሳ ይሆን? ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጓደኞች በመጥፎም ይሁን በጥሩ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይናገራል። (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) በሌላ በኩል ደግሞ በዛሬው ጊዜ ለወጣቶች የሚቀርበው አብዛኛው መዝናኛ፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ማመፃቸው ስህተት እንዳልሆነ የሚጠቁም መልእክት የሚያስተላልፍ ነው።
ይሁንና በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ እንዲያሳዩ የሚያደርጓቸው ሌሎች ነገሮችም አሉ፤ እነዚህ ነገሮች በልጃችሁ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት እንደሆነ መገንዘባችሁ ለጉዳዩ እልባት ማግኘት ቀላል እንዲሆንላችሁ ያደርጋል። ከእነዚህ መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።
“የማሰብ ችሎታ” ማዳበር
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሕፃን በነበርኩበት ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር፣ እንደ ሕፃን አስብ እንዲሁም እንደ ሕፃን አመዛዝን ነበር፤ አሁን ሙሉ ሰው ከሆንኩ በኋላ ግን የሕፃንነትን ጠባይ ትቻለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 13:11) ጳውሎስ ከተናገረው ሐሳብ መመልከት እንደሚቻለው ልጆችና አዋቂዎች የሚያስቡበት መንገድ ይለያያል። እንዴት?
ልጆች አንድን ነገር የሚያስቡት ‘ትክክል ነው ወይስ አይደለም’ ከሚለው አንጻር ብቻ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ብዙውን ጊዜ አዋቂዎች ከአንድ ነገር በስተጀርባ ያሉ ሁኔታዎችን የሚያመዛዝኑ ሲሆን አንድ መደምደሚያ ወይም ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ ይመረምራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አዋቂዎች አንድን ነገር ከማድረጋቸው በፊት ድርጊቱ ተቀባይነት ያለው መሆን አለመሆኑን እንዲሁም ሌሎችን እንዴት እንደሚነካ ያስባሉ። ለአዋቂዎች በዚህ መንገድ ማሰብ አይከብዳቸው ይሆናል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ግን እንዲህ ማድረግን ገና አልለመዱም።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወጣቶች “ልባም” እንዲሆኑ በሌላ አባባል የማመዛዘን ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ያበረታታል። (ምሳሌ 1:4) ለነገሩ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሁሉንም ክርስቲያኖች ‘የማሰብ ችሎታቸውን’ እንዲጠቀሙበት ያሳስባል። (ሮም 12:1, 2፤ ዕብራውያን 5:14) አንዳንድ ጊዜ ግን ልጃችሁ የሚያስብበት መንገድ ከእናንተ የተለየ ይሆንና በትናንሹ ጉዳይም እንኳ ሳይቀር ይሞግታችሁ ይሆናል። ወይም ደግሞ ትክክል እንዳልሆነ ለእናንተ በግልጽ የሚታያችሁን ሐሳብ ያቀርብ ይሆናል። (ምሳሌ 14:12) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ከመጨቃጨቅ ይልቅ ነጥቡን በሚያሳምን መንገድ ልታስረዱት የምትችሉት እንዴት ነው?
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ፣ በማመዛዘን ችሎታው ለመጠቀም እየሞከረ ሊሆን እንደሚችል አስቡ፤ ምናልባትም የተናገረውን ነገር ያን ያህል አያምንበት ይሆናል። አመለካከቱን በትክክል ለመረዳት እንድትችሉ በመጀመሪያ፣ የራሱ አመለካከት ያለው መሆኑን እንደምታደንቁ ንገሩት። (“በደረስክበት መደምደሚያ ሙሉ በሙሉ ባልስማማም ያሰብክበት መንገድ ጥሩ ነው።”) ከዚያም አመለካከቱን እንዲገመግም እርዱት። (“አንተ ያልከው ነገር ሁልጊዜ ሊሠራ የሚችል ይመስልሃል?”) እንዲህ ስታደርጉ ልጃችሁ አመለካከቱን እንደገና ሊገመግምና ሊያስተካክል ይችላል።
ይሁንና ልትጠነቀቁበት የሚገባ ነገር አለ፦ ከልጃችሁ ጋር ስትነጋገሩ፣ ሁልጊዜ እናንተ ትክክል መሆናችሁን ማሳየት እንዳለባችሁ ሊሰማችሁ አይገባም። አንዳንድ ጊዜ ልጃችሁ ለምትነግሩት ነገር ጆሮ ዳባ እንዳለ ይሰማችሁ ይሆናል፤ እሱም ቢሆን ሐሳባችሁን እንደተቀበለ አይናገር ይሆናል፤ ያም ቢሆን እናንተ ከምታስቡት በላይ ከውይይቱ ሊጠቀም ይችላል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ በድንገት ሐሳቡን ቢቀይር እንዲያውም እናንተ ያቀረባችሁለትን ሐሳብ የራሱ ሐሳብ እንደሆነ ቢናገር አይግረማችሁ።
“እኔና ልጄ አንዳንድ ጊዜ የምንጨቃጨቀው ጥቃቅን በሆኑ ጉዳዮች ነው፤ ለምሳሌ፣ አባካኝ እንዳይሆን ወይም እህቱ ላይ እንዳያሾፍ ስነግረው መቀበል ስለማይፈልግ ይሞግተኛል። አብዛኛውን ጊዜ ግን እንዲህ የሚያደርገው የእሱ አመለካከት ምን እንደሆነ እንድጠይቀው እንዲሁም ሐሳቡን እንደተረዳሁለት በሚያሳይ መንገድ እንዳነጋግረው ስለሚፈልግ ይመስለኛል፤ ለምሳሌ፣ ‘አሃ፣ እንደዚህ አስበህ ነው እንዴ?’ ወይም ‘እንዲህ ተሰምቶህ ነው ማለት ነው?’ ብለው የተሻለ ይሆን እንደነበር ይሰማኛል። አሁን መለስ ብዬ ሳስበው እንዲህ ብዬው ቢሆን ኖሮ ብዙ ንትርክ ማስቀረት እንችል ነበር።”—ኬንጂ፣ ጃፓን
የራሱ የሆነ አመለካከት መያዝ
ልጆቻችሁ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ማድረግ ከሚገቧችሁ ነገሮች ዋነኛው፣ ራሳቸውን ችለው መኖር ሲጀምሩ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እንዲሆኑ ማሠልጠን ነው። (ዘፍጥረት 2:24) እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና ልጁ የራሱ ማንነት እንዲኖረው መርዳትን ይኸውም እሱነቱን ለይተው የሚያሳውቁትን ባሕርያት፣ እምነቶች እና እሴቶች እንዲያዳብር ማገዝን ያካትታል። ምን ዓይነት ሰው መሆን እንደሚፈልግ በደንብ የሚያውቅ ወጣት፣ ተገቢ ያልሆነ ነገር እንዲያደርግ ተጽዕኖ ሲደርስበት ያንን ነገር መፈጸሙ የሚያስከትለውን ጉዳት ከማሰብ ያለፈ ነገር ያደርጋል። ራሱን እንዲህ እያለ ይጠይቃል፦ ‘እኔ ማን ነኝ? ከፍ አድርጌ የምመለከታቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? እንደ እኔ ዓይነት አመለካከት ያለው ሰው በዚህ ወቅት ምን ዓይነት እርምጃ ይወስዳል?’—2 ጴጥሮስ 3:11
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዮሴፍ ስለተባለ ወጣት ይናገራል፤ ዮሴፍ ማንነቱን በደንብ የሚያውቅ ሰው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የጲጥፋራ ሚስት ከእሷ ጋር እንዲተኛ በጎተጎተችው ጊዜ፣ ዮሴፍ “ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” ብሏታል። (ዘፍጥረት 39:9) ምንዝር መፈጸምን የሚከለክለው ሕግ ለእስራኤላውያን የተሰጠው ከረጅም ጊዜ በኋላ ቢሆንም ዮሴፍ አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ያለውን አመለካከት አስተውሎ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ዮሴፍ ‘እኔ እንዴት ይህን አደርጋለሁ?’ የሚል ዓይነት መልስ መስጠቱ ማንነቱ በአምላክ አመለካከት እንደተቀረጸ ይኸውም የአምላክ ዓይነት አመለካከት እንዳዳበረ የሚያሳይ ነው።—ኤፌሶን 5:1
በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁም የራሱ ማንነት ያለው ሰው ለመሆን እየጣረ ነው። ይህ ደግሞ ጥሩ ነገር ነው፤ ምክንያቱም የራሱ አመለካከት ካለው እኩዮቹ የሚያደርሱበትን ተጽዕኖ መቋቋምና ለሚያምንበት ነገር አቋም መውሰድ ይችላል። (ምሳሌ 1:10-15) በሌላ በኩል ግን የራሱን አመለካከት ማዳበሩ ከእናንተም የተለየ አቋም እንዲይዝ ሊያደርገው ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ጭቅጭቅ ውስጥ ከመግባት ተቆጠቡ፤ ከዚህ ይልቅ እሱ ያቀረበውን ሐሳብ ደግማችሁ በመናገር አመለካከቱ ገብቷችሁ እንደሆነ ለማወቅ ሞክሩ። (“ሐሳብህ ገብቶኝ እንደሆነ ለማወቅ ብዬ ነው፤ እያልክ ያለኸው . . . ነው?”) ከዚያም ጥያቄዎች አቅርቡለት። (“እንዲህ የተሰማህ ለምንድን ነው?” ወይም “እንዲህ ዓይነት መደምደሚያ ላይ እንድትደርስ ያደረገህ ምንድን ነው?”) ልጃችሁ ሐሳቡን አውጥቶ እንዲናገር ለማድረግ ሞክሩ። አመለካከቱን እንዲነግራችሁ አበረታቱት። በልጃችሁ አመለካከት
ያልተስማማችሁት፣ የተናገረው ነገር ስህተት ሆኖ ሳይሆን ምርጫችሁ ስለተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ሁኔታው እንዲህ ከሆነ በሐሳቡ ሙሉ በሙሉ ባትስማሙም እንኳ አመለካከቱን እንደምታከብሩለት አሳዩት።በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ የራሱን ማንነት ማዳበሩና በዚህም የተነሳ የራሱ አመለካከት ያለው መሆኑ የሚጠበቅ ነገር ብቻ ሳይሆን ጠቃሚም ነው። ደግሞም ክርስቲያኖች፣ እንደ ትናንሽ ልጆች ‘በማዕበል የሚነዱ ይመስል በማንኛውም የትምህርት ነፋስ የሚንገዋለሉና ወዲያና ወዲህ የሚሉ’ መሆን እንደሌለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኤፌሶን 4:14) በመሆኑም ልጃችሁ የራሱን ማንነት እንዲያዳብርና የራሱ አመለካከት እንዲኖረው ልትፈቅዱለት አልፎ ተርፎም ልታበረታቱት ይገባል።
“ሴት ልጆቼ፣ አመለካከታቸውን በሚገልጹበት ጊዜ ለማዳመጥ ፈቃደኛ እንደሆንኩ ሲመለከቱ፣ የእኔ ሐሳብ ከእነሱ የተለየ ቢሆንም እንኳ እኔ የምለውን ለመስማት ይበልጥ ፈቃደኞች እንደሚሆኑ አስተውያለሁ። የእኔን አመለካከት በእነሱ ላይ ላለመጫን እጠነቀቃለሁ፤ ከዚህ ይልቅ የራሳቸውን አመለካከት እንዲያዳብሩ አበረታታቸዋለሁ።”—ኢቫና፣ ቼክ ሪፑብሊክ
ጥብቅ ሆኖም ምክንያታዊ
ትናንሽ ልጆች፣ አንድ ነገር ሲፈልጉ ወላጆቻቸውን በመነዝነዝ የፈለጉትን እንዲፈጽሙላቸው ለማድረግ ይሞክራሉ፤ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ አንዳንድ ወጣቶችም ይህን ዘዴ ይጠቀማሉ። ልጃችሁ እንዲህ ዓይነት ልማድ ካለው መጠንቀቅ ይኖርባችኋል። ልጃችሁ የሚፈልገውን ነገር ስታደርጉለት ለጊዜው ከጭቅጭቁ ትገላገሉ ይሆናል፤ ሆኖም እንዲህ ስታደርጉ፣ በመሟገት የፈለገውን ማግኘት እንደሚችል ለልጃችሁ እያስተማራችሁት ነው። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? “ቃላችሁ አዎ ከሆነ አዎ ይሁን፣ አይደለም ከሆነ አይደለም ይሁን” የሚለውን የኢየሱስ ምክር ተከተሉ። (ማቴዎስ 5:37) ልጆቻችሁ ወጥ አቋም እንዳላችሁ ካወቁ ከእናንተ ጋር በመጨቃጨቅ የፈለጉትን ለማግኘት አይሞክሩም።
በሌላ በኩል ደግሞ ምክንያታዊ መሆን አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል ልጃችሁ አንድ ምሽት ላይ፣ ለወትሮው ቤት ከሚገባበት ሰዓት አሳልፎ ለመግባት ፈለገ እንበል፤ በዚህ ጊዜ፣ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ያቀረበበትን ምክንያት ጠይቁት። እንዲህ ማድረጋችሁ በልጃችሁ ተጽዕኖ አቋማችሁን እንዳላላችሁ የሚያሳይ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ “ምክንያታዊነታችሁ . . . የታወቀ ይሁን” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እየተከተላችሁ እንደሆነ የሚጠቁም ነው።—ፊልጵስዩስ 4:5
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆናችሁ፣ ልጆች ቤት መግባት ስለሚጠበቅባቸው ሰዓትና ስለ ሌሎች መመሪያዎች ተወያዩ። አንድ ውሳኔ ላይ ከመድረሳችሁ በፊት አመለካከታቸውን ለማዳመጥና የተለያዩ ነገሮችን ከግምት ለማስገባት ፈቃደኞች ሁኑ። በብራዚል የሚኖር ሮቤርቱ የተባለ አባት እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ እስካልተጣሰ ድረስ የልጆቻቸውን ጥያቄ ለመቀበል ፈቃደኞች እንደሆኑ በግልጽ ሊያሳዩ ይገባል።”
እርግጥ ነው፣ ፍጹም የሆነ ወላጅ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን” ይላል። (ያዕቆብ 3:2) ከልጃችሁ ጋር ለተፈጠረው ግጭት በተወሰነ መጠንም ቢሆን ተጠያቂ እንደሆናችሁ ከተሰማችሁ ይቅርታ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበሉ። ስህተታችሁን አምናችሁ ስትቀበሉ ለልጃችሁ ትሕትናን ታስተምሩታላችሁ፤ ልጃችሁም እንዲሁ እንዲያደርግ ምሳሌ ትሆኑለታላችሁ።
“በአንድ ወቅት፣ ከልጄ ጋር ተጨቃጭቀን ነበር፤ ራሴን ካረጋጋሁ በኋላ ግን ቀደም ሲል በቁጣ ገንፍዬ በመናገሬ ልጄን ይቅርታ ጠየቅሁት። ይህን ስለው እሱም የተረጋጋ ሲሆን እኔ የምለውን ለመስማት ፈቃደኛ ሆነ።”—ኬንጂ፣ ጃፓን
^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ስለሚገኙ ልጆች ስንናገር በወንድ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።
ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦
-
ከልጄ ጋር ጭቅጭቅ እንዲፈጠር እኔ ያደረግሁት አስተዋጽኦ ይኖር ይሆን?
-
በዚህ ርዕስ ላይ የሚገኙት ሐሳቦች ልጄ የሚያስብበትን መንገድ ይበልጥ ለመረዳት የሚያስችሉኝ እንዴት ነው?
-
በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኘው ልጄ ጋር ሳንጨቃጨቅ መነጋገር የምንችለው እንዴት ነው?