መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
“ምድር ገነት እንደምትሆን የሚገልጸው ተስፋ ሕይወቴን ለወጠው”
-
የትውልድ ዘመን፦ 1974
-
የትውልድ አገር፦ ላትቪያ
-
የኋላ ታሪክ፦ በአደገኛ የሞተር ብስክሌት ውድድር ይካፈል የነበረ
የቀድሞ ሕይወቴ፦
የተወለድኩት የላትቪያ ዋና ከተማ በሆነችው በሪጋ ነው። እኔንና እህቴን ያሳደገችን እናታችን ናት። እናቴ ካቶሊክ ብትሆንም ቤተ ክርስቲያን የምንሄደው በሃይማኖታዊ በዓላት ቀን ብቻ ነበር። ከሁሉ በላይ የሆነ አካል እንዳለ ምንጊዜም አምን ነበር፤ በወጣትነት ዕድሜ ላይ ስሆን ግን ትኩረቴን የሚከፋፍሉ ሌሎች ነገሮች አጋጠሙኝ።
እያደግሁ ስሄድ፣ ዕቃዎችን መፈታታትና መልሶ መገጣጠም እንደምወድ እናቴ አስተዋለች። ቤት ውስጥ ሊፈታቱ የሚችሉ ብዙ ነገሮች ስላሉ እናቴ፣ ቤት ብቻዬን ትታኝ መሄድ ያስፈራት ነበር። ስለዚህ የሚገጣጠሙ ነገሮች ያሉት መጫወቻ ሰጠችኝ፤ እነዚህን ነገሮች መገጣጠምና መፈታታት በጣም ደስ ይለኝ ነበር። ይህም በጣም ከምወደው ነገር ይኸውም ሞተር ብስክሌት ከመንዳት ጋር አብሮ የሚሄድ ነበር። እናቴ ዛልታ ሞፓትስ (ወርቃማው ቀላል ሞተር ብስክሌት) ተብሎ በሚጠራ ውድድር እንድካፈል አስመዘገበችኝ። ውድድር የጀመርኩት በቀላል ሞተር ብስክሌቶች ሲሆን እያደር በትላልቆቹ ሞተር ብስክሌቶች ውድድር መካፈል ጀመርኩ።
ነገሮችን ለመማር ፈጣን ስለነበርኩ ብዙም ሳይቆይ በዚህ ፈጣንና አደገኛ ስፖርት ውስጥ በጣም ስኬታማ ሆንኩ። በላትቪያ የከፍተኛ ሞተር ብስክሌት ውድድሮች ሦስት ጊዜ አሸናፊ ሆኛለሁ፤ በባልቲክ አገሮች መካከል በተካሄዱ የከፍተኛ ሞተር ውድድሮች ላይ ደግሞ ሁለት ጊዜ አሸንፌያለሁ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?
በሞያዬ በጣም ስኬታማ በሆንኩበት ወቅት የሴት ጓደኛዬ ኤቪያ (ከጊዜ በኋላ ሚስቴ ሆናለች) ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘች። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጇቸውን አንዳንድ ጽሑፎች አግኝታ ነበር፤ በጽሑፎቹ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መጠየቂያ ቅጽ ስለነበር ቅጹን ሞልታ ላከችው። ብዙም ሳይቆይ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን መጡ፤ እሷም ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ባለቤቴ ማጥናቷን ባልቃወምም እኔ ግን በዚያን ጊዜ ለመንፈሳዊ ነገሮች ያን ያህል ፍላጎት አልነበረኝም።
ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮቹ፣ ኤቪያ መጽሐፍ ቅዱስ በምታጠናበት ጊዜ ቁጭ ብዬ እንዳዳምጥ ጋበዙኝ። እኔም ግብዣውን የተቀበልኩ ሲሆን የሰማሁትን ነገር ወደድኩት። በተለይ በጣም ልቤን የነካው ምድር በመዝሙር 37:10, 11 ላይ የሚገኘውን “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” የሚለውን ጥቅስ አሳዩኝ። ይህ ተስፋ በጣም ማረከኝ።
ገነት እንደምትሆን የሚገልጸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ተስፋ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ከዚያ በኋላ ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለኝ ፍላጎት እያደገ መጣ። በጣም ብዙ ሃይማኖታዊ ውሸቶች እንዳሉ መገንዘብ ጀመርኩ። በተቃራኒው ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በጣም ምክንያታዊና ግልጽ መሆናቸው አስደነቀኝ።
መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን ስቀጥል ይሖዋ ሕይወትን ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከትና ሕይወት በእሱ ዘንድ እጅግ ክቡር እንደሆነ ተማርኩ። (መዝሙር 36:9) ይህም እኔ ስለምወዳደርበት ስፖርት ቆም ብዬ እንዳስብ አደረገኝ፤ ከዚያ በኋላ ሕይወቴን ለአደጋ ማጋለጥ እንደሌለብኝ ተገነዘብኩ። ከዚህ ይልቅ ሕይወቴን ይሖዋን ለማክበር ልጠቀምበት ፈለግሁ። በመሆኑም በሞተር ብስክሌት ውድድር የሚገኘው ዝና፣ ክብርና ደስታ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነገር መሆኑ ቀረ።
ሕይወት ሰጪ በሆነው በይሖዋ ፊት ስለ ሕይወቴ ተጠያቂ እንደሆንኩ ተገነዘብኩ
በታሊን፣ ኢስቶኒያ ብዙ ጊዜ በሞተር ብስክሌት ውድድር ስካፈልበት በነበረው ስታዲየም አቅራቢያ የይሖዋ ምሥክሮች በ1996 ባደረጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። በስብሰባው ላይ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሰዎች እርስ በርስ ተስማምተውና በሰላም ተሰብስበው አየሁ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ቦርሳዋ ጠፋባት፤ ቦርሳዋን እንደማታገኘው አስቤ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን አንድ የይሖዋ ምሥክር ቦርሳዋን አግኝቶ መለሰላት፤ ከቦርሳዋ ውስጥ ምንም ነገር አልጎደለም። ይህን ሳይ በጣም ገረመኝ! በእርግጥም የይሖዋ ምሥክሮች ከፍ ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መሠረት ሕይወታቸውን እንደሚመሩ ተረዳሁ። ኤቪያና እኔ በጥናታችን የቀጠልን ሲሆን በ1997 ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን።
ያገኘሁት ጥቅም፦
አንዳንድ ጓደኞቼ በሞተር ቢስክሌት ውድድር ላይ አስፈሪ በሆነ ፍጥነት ሲነዱ ሕይወታቸውን አጥተዋል። እኔ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ሳጠና፣ ሕይወት ሰጪ በሆነው በይሖዋ ፊት ስለ ሕይወቴ ተጠያቂ እንደሆንኩ ተገነዘብኩ። ምናልባትም ሕይወቴን ያተረፈልኝ ይህ እውቀት ሳይሆን አይቀርም።
እኔና ኤቪያ በሪጋ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ለአራት ዓመታት ያህል በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመካፈል መብት አግኝተን ነበር። አሁን አሊሴ የተባለች ልጅ የወለድን ሲሆን ልጃችን ይሖዋን እንድትወደው መርዳት ያስደስተናል። በተጨማሪም በየሳምንቱ አንድ ቀን፣ በትርጉም ቢሮው ውስጥ መኪኖችንና ሌሎች የተበላሹ ነገሮችን የመጠገን መብት አግኝቻለሁ። በልጅነቴ ያዳበርኩትን ችሎታ በጥሩ መንገድ ልጠቀምበት በመቻሌ በጣም ደስ ይለኛል! አዎን፣ አሁንም ቢሆን ዕቃዎችን መፈታታትና መልሼ መገጣጠም አላቆምኩም።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ነገር በመማሬ አመስጋኝ ነኝ፤ ከቤተሰቤ ጋር አንድ ላይ በመሆን ብቻውን እውነተኛ ስለሆነው አምላክ የመመስከርን መብቴን ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ። በእርግጥም፣ ምድር ገነት እንደምትሆን የሚገልጸው ተስፋ ሕይወቴን ለውጦታል!