በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በሮማውያን ዘመን የባሮች ሕይወት ምን ይመስል ነበር?

የሮማውያን ባሮች አንገታቸው ላይ የሚያጠልቁት ቀለበት

በሮም ግዛት ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌለው ሕዝብ የጦር ምርኮኛ በመሆን ወይም በአፈና ለባርነት ይዳረግ ነበር። እነዚህ ሰዎች ከተሸጡ በኋላ ዳግመኛ ወደ መኖሪያቸው የመመለስም ሆነ ቤተሰባቸውን የማየት አጋጣሚ አያገኙም።

በማዕድን ማውጫ ጉድጓዶች ውስጥ የሚሠሩ አብዛኞቹ ባሮች በሥራው ምክንያት ሕይወታቸው ይቀጫል፤ በእርሻ ወይም በቤት ውስጥ የሚሠሩ ባሮች ግን በአንጻራዊ ሁኔታ የተሻለ ሕይወት ነበራቸው። አንድ ባሪያ የብረት ቀለበት አንገቱ ላይ እንዲያጠልቅ ሊገደድ ይችል ነበር፤ ከጌታው ጠፍቶ ከሄደ በኋላ እሱን ለባለቤቱ የመለሰ ሰው ወሮታ እንደሚከፈለው የሚገልጽ ጽሑፍ በቀለበቱ ላይ ይቀረጻል ወይም ይንጠለጠላል። በተደጋጋሚ ለማምለጥ የሞከሩ ባሮች ኮብላይ የሚል ትርጉም ያለው F (fugitivus) የሚል ፊደል በግምባራቸው ላይ በእሳት በመተኮስ ምልክት ሊደረግባቸው ይችል ነበር።

ፊልሞና የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ከጌታው የኮበለለውን አናሲሞስ የተባለ ባሪያ ወደ ጌታው ወደ ፊልሞና መልሶ እንደላከው ይገልጻል። ፊልሞና አናሲሞስን ከባድ ቅጣት ለመቅጣት ሕጋዊ መብት ቢኖረውም ጳውሎስ ለፍቅርና በመካከላቸው ላለው ወዳጅነት ሲል ‘በደግነት እንዲቀበለው’ ጠይቆታል።—ፊልሞና 10, 11, 15-18

የጥንቷ ፊንቄ ሐምራዊ ቀለም በመሥራት ትታወቅ የነበረው ለምንድን ነው?

በአሁኗ ሊባኖስ አካባቢ ትገኝ የነበረችው የጥንቷ ፊንቄ ‘የጢሮስ ሐምራዊ ቀለም’ ተብሎ የሚጠራውን ማቅለሚያ በመሥራት ትታወቅ ነበር። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ፣ ሰለሞን ቤተ መቅደሱን ከጢሮስ በመጣ የእጅ ባለሙያ በተሠራ ‘ሐምራዊ ግምጃ’ አስጊጦት ነበር።—2 ዜና መዋዕል 2:13, 14

የጢሮስ ሐምራዊ ቀለም በዘመኑ ውድ ቀለም ነበር፤ ይህ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት ቀለሙን ማዘጋጀት አድካሚ ስለነበረ ነው። በመጀመሪያ፣ ዓሣ አጥማጆች ሚውሬክስ የተባሉትን የባሕር ቀንድ አውጣዎች * በገፍ ይሰበስቡ ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት አንድ ልብስ ለማቅለም የሚያስፈልገውን ቀለም ለማምረት 12,000 ያህል የባሕር ቀንድ አውጣዎች ያስፈልጉ ስለነበር ነው። ቀጥሎ ቀለም የሚሠራውን ዕጢያቸውን ለማውጣት ዛጎላቸው ይነሳል። ቀለም ሠሪዎቹ ያወጡትን ዕጢ ከጨው ጋር ካዋሃዱት በኋላ ለሦስት ቀናት ፀሐይ ላይ ያሰጡታል። ከዚያም ግጣም ባለው ዕቃ ውስጥ ካደረጉት በኋላ የባሕር ውኃ ጨምረውበት ለተወሰኑ ቀናት ብዙ ኃይል በሌለው እሳት ላይ ይጥዱታል።

ፊንቄያውያን ባካሄዱት ንግድና ቅኝ ግዛት አማካኝነት በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት የጢሮስን ሐምራዊ ቀለም ማምረቱንም ሆነ ገበያውን ተቆጣጥረውት ቆይተዋል። ፊንቄያውያን ቀለም ያመርቱ እንደነበረ የሚጠቁሙ ቅርሶች በሜድትራንያን ባሕር አካባቢ አልፎ ተርፎም በምዕራብ አቅጣጫ ስፔን ውስጥ ባለች ካዲዝ የተባለች ከተማ ድረስ ተገኝተዋል።

^ አን.8 የቀንድ አውጣዎቹ ዛጎል ከአምስት እስከ ስምንት ሳንቲ ሜትር ርዝመት አለው።