በእምነታቸው ምሰሏቸው | ማርያም
የሐዘንን ሰይፍ ተቋቁማለች
ማርያም በጉልበቷ ተደፍታለች፤ የደረሰባት ሐዘን በቃላት ሊገለጽ የሚችል አይደለም። ልጇ ለብዙ ሰዓት ከተሠቃየ በኋላ ሊሞት ሲል ያሰማው የመጨረሻ ጩኸት አሁንም በጆሮዋ እያስተጋባ ነው። ገና እኩለ ቀን ቢሆንም ሰማዩ ጨልሟል። ድንገት ምድሪቱ በኃይል ተናወጠች። (ማቴዎስ 27:45, 51) ማርያም ይህንን ማየቷ ስለ ይሖዋ አንድ ነገር ሳያስገነዝባት አልቀረም፤ በልጁ መሞት ከማንም በላይ ያዘነው እሱ መሆኑን ለዓለም ማሳየት ፈልጎ ሊሆን እንደሚችል ተሰምቷት ሊሆን ይችላል።
ጎልጎታን ወይም የራስ ቅል ቦታ የተባለውን ስፍራ የዋጠው ጨለማ መገፈፍ ቢጀምርም ማርያም ግን በልጇ ሞት ምክንያት በሐዘን እንደተዋጠች ናት። (ዮሐንስ 19:17, 25) በዚህ ወቅት ብዙ ትዝታዎች ወደ አእምሮዋ ሳይመጡ አልቀሩም። ምናልባትም ከ33 ዓመታት ገደማ በፊት የሰማችውን ነገር አስታውሳ ሊሆን ይችላል። በወቅቱ እሷና ዮሴፍ በጣም የሚወዱትን ልጃቸውን ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ሲወስዱት ስምዖን የተባለ አንድ አረጋዊ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ ታላላቅ ነገሮችን እንደሚያከናውን ትንቢት ተናገረ፤ አክሎ ግን አንድ ቀን ማርያም ትልቅ ሰይፍ በውስጧ ያለፈባት ያህል ሆኖ እንደሚሰማት ተናገረ። (ሉቃስ 2:25-35) የእነዚህ ቃላት ትርጉም ሙሉ በሙሉ የገባት ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ሲደርስባት ነው።
ልጅን በሞት ከማጣት የበለጠ ሐዘን እንደማይኖር ብዙዎች ይሰማቸዋል። ሞት ክፉ ጠላት ስለሆነ የሚያደርሰው ቁስል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሁላችንንም ያሠቃየናል። (ሮም 5:12፤ 1 ቆሮንቶስ 15:26) ታዲያ እንዲህ ካለው ቁስል ማገገም ይቻላል? ኢየሱስ አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከሞተበት ጊዜ እንዲሁም ከዚያም በኋላ ያለውን የማርያምን ሕይወት ስንቃኝ እምነቷ የሐዘንን ሰይፍ እንድትቋቋም የረዳት እንዴት እንደሆነ ብዙ የምንማረው ነገር አለ።
“የሚላችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ”
እስቲ ሦስት ዓመት ተኩል ወደኋላ እንመለስ፤ ማርያም የሆነ ለውጥ እንደሚመጣ ተሰምቷታል። በትንሿ የናዝሬት ከተማም እንኳ ሰዎች ስለ መጥምቁ ዮሐንስና ቀስቃሽ ስለሆነው የንስሐ መልእክቱ እየተነጋገሩ ነው። የበኩር ልጇ ይህን አዋጅ አገልግሎቱን የሚጀምርበት ጊዜ መድረሱን እንደሚጠቁም ጥሪ አድርጎ መመልከቱን ማርያም ሳታስተውል አልቀረችም። (ማቴዎስ 3:1, 13) ኢየሱስ ከቤት መውጣቱ ለማርያምና ለቤተሰቧ በጣም የሚከብድ ነገር ነው። ለምን?
በዚህ ወቅት የማርያም ባል የነበረው ዮሴፍ ሳይሞት አልቀረም። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ደግሞ የቤተሰብ አባልን በሞት መነጠቅ ለማርያም አዲስ ነገር አይደለም ማለት ነው። * ኢየሱስ በዚህ ጊዜ ‘የአናጺው ልጅ’ ብቻ ሳይሆን “አናጺው” ተብሎ ተጠርቷል። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ የአባቱን ሥራ ተረክቦ መሥራት የጀመረ ሲሆን ከእሱ በኋላ የተወለዱትን ቢያንስ ስድስት ልጆች ጨምሮ ቤተሰቡን ያስተዳድር ነበር። (ማቴዎስ 13:55, 56፤ ማርቆስ 6:3) ኢየሱስ ከቤቱ ሁለተኛ ልጅ እንደሆነ ለሚታሰበው ለያዕቆብ የአናጺነት ሙያ አስተምሮት ሊሆን ቢችልም እንኳ የበኩር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ከቤት መውጣቱ ለቤተሰቡ ቀላል ነገር እንደማይሆን ግልጽ ነው። ማርያም ቀድሞውንም ቢሆን ያለባት ኃላፊነት ከባድ ነው፤ ታዲያ አሁን የተከሰተው ለውጥ አስፈርቷት ይሆን? እርግጥ ነው፣ ከመገመት በቀር ምን እንደተሰማት በትክክል ማወቅ አንችልም። ይሁን እንጂ ከዚህ ይበልጥ የሚያሳስበው ጥያቄ ‘የናዝሬቱ ኢየሱስ ለረጅም ጊዜ ተስፋ የተደረገው መሲሕ ማለትም ክርስቶስ በሚሆንበት ጊዜ ምን ይሰማት ይሆን?’ የሚለው ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በዚህ ረገድ የሚገልጽልን ነገር አለ።—ዮሐንስ 2:1-12
ኢየሱስ ወደ ዮሐንስ ሄዶ በመጠመቅ የአምላክ ቅቡዕ ወይም መሲሕ ሆነ። (ሉቃስ 3:21, 22) ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን መምረጥ ጀመረ። የሚያከናውነው ሥራ አጣዳፊ ቢሆንም እንኳ ከቤተሰብና ከወዳጆቹ ጋር አስደሳች ጊዜ ያሳልፍ ነበር። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ከእናቱ፣ ከደቀ መዛሙርቱና ከሥጋ ወንድሞቹ ጋር ሆኖ በአንድ የሠርግ ድግስ ላይ ለመታደም ከናዝሬት 13 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘውና በኮረብታ አናት ላይ ወደተቆረቆረችው የቃና ከተማ አመራ። ማርያም በግብዣው ላይ አንድ ችግር እንደተፈጠረ አስተዋለች። ምናልባትም ይህንን የተገነዘበችው የሙሽራው ቤተሰብ በጭንቀት ሲተያዩና ሲንሾካሾኩ በማየቷ ሊሆን ይችላል። ትርምሱ የተፈጠረው ወይን ጠጅ በማለቁ ነው! በባሕላቸው ደግሞ እንግዳ ጋብዞ እንዲህ ያለ ነገር መከሰቱ ቤተሰቡን ለኀፍረት የሚዳርግ ከመሆኑም ሌላ የድግሱን ድባብ የሚያጠፋ ነው። ማርያም ችግራቸው ስለተሰማት ጉዳዩን ለኢየሱስ አዋየችው።
“የወይን ጠጅ እኮ አለቀባቸው” ብላ ለልጇ ነገረችው። ማርያም ይህን ያለችው ምን እንዲያደርግ ጠብቃ ይሆን? የዚህን ጥያቄ መልስ ከመገመት በቀር ይህ ነው ማለት አንችልም፤ ይሁን እንጂ ማርያም ልጇ ድንቅ ነገሮችን ማድረግ የሚችል ታላቅ ሰው እንደሆነ ታውቃለች። ምናልባትም አስደናቂ ነገሮች መፈጸሙን አሁን እንደሚጀምር ተስፋ አድርጋ ሊሆን ይችላል። ማርያም “እባክህ ልጄ፣ አንድ ነገር አድርግ እንጂ!” ያለችው ያህል ነበር። በዚህ ወቅት ኢየሱስ የሰጣት መልስ አስገርሟት መሆን አለበት። “አንቺ ሴት፣ ከአንቺ ጋር ምን ጉዳይ አለኝ?” አላት። አንዳንዶች በተሳሳተ መንገድ ቢረዱትም የኢየሱስ አነጋገር አክብሮት እንደጎደለው የሚያሳይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህን የተናገረው ፍቅራዊ እርማት መስጠት ፈልጎ ነው። ኢየሱስ ለእናቱ፣ አገልግሎቱን የሚያከናውንበትን መንገድ በተመለከተ እሱን የማዘዝ ሥልጣን እንደሌላት እየገለጸ ነበር፤ እንዲህ ያለ መብት ያለው አባቱ ይሖዋ ነው።
ማርያም የሰው ስሜት የምትረዳ ትሑት ሴት ስለነበረች ልጇ የሰጣትን እርማት ተቀብላለች። ከዚያም ለአስተናጋጆቹ “የሚላችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። ማርያም ከእንግዲህ ለልጇ መመሪያ የመስጠት መብት እንደሌላት ከዚህ ይልቅ እሷም ሆነች ሌሎች መመሪያ መቀበል ያለባቸው ከእሱ እንደሆነ ተገነዘበች። ኢየሱስም ቢሆን የእናቱን ስሜት በመጋራት ለሙሽሮቹ አዝኗል። በመሆኑም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ በመለወጥ የመጀመሪያውን ተአምር ፈጸመ። በዚህ ጊዜ ‘ደቀ መዛሙርቱ በእሱ አመኑ።’ ማርያምም ብትሆን በኢየሱስ አምናለች። ልጇን ኢየሱስን እንደ ጌታዋና አዳኟ አድርጋ መመልከት ጀመረች።
በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች ማርያም ካሳየችው እምነት ብዙ መማር ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ እንደ ኢየሱስ ያለ ልጅ ያሳደገ ሌላ ሰው የለም። ይሁን እንጂ አንድ ልጅ ፍጹም ሆነም አልሆነ፣ አድጎ ትልቅ ሰው ሲሆን ለውጡን መቀበል ለወላጅ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። አንድ ወላጅ ልጆቹ አድገው አዋቂ ከሆኑ በኋላም ልጆቹን እንደ ሕፃን መመልከቱን መቀጠል ይቀናው ይሆናል፤ ይሁንና እንዲህ ማድረግ ተገቢ ላይሆን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 13:11) ታዲያ አንድ ወላጅ፣ አዋቂ የሆነውን ልጁን እንዴት ሊረዳው ይችላል? አንዱ መንገድ ልጁ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረጉን እንደሚቀጥልና በውጤቱም የይሖዋን በረከት እንደሚያገኝ ያለውን እምነት በመግለጽ ነው። አንድ ወላጅ በዕድሜ ትልቅ በሆነው ልጁ ላይ ያለውን እምነትና መተማመን ከልብ በመነጨ ስሜት መግለጹ ልጁ ለመልካም ነገር ይበልጥ እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል። ኢየሱስም በቀጣዮቹ ዓመታት በሕይወቱ ብዙ ነገሮች ያጋጠሙት ከመሆኑ አንጻር ከማርያም ያገኘውን ድጋፍ ከፍ አድርጎ እንደተመለከተው ጥርጥር የለውም።
“ወንድሞቹ . . . አላመኑበትም ነበር”
ወንጌሎች ሦስት ዓመት ተኩል በዘለቀው የኢየሱስ አገልግሎት ወቅት ስለ ማርያም የሚነግሩን ነገር በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቂት ነው። ይሁንና በዚህ ወቅት ማርያም መበለት ልትሆን እንደምትችልና በቤት ውስጥም ትናንሽ ልጆች ሳይኖሯት እንደማይቀሩ ማስታወስ ይገባል። በመሆኑም ኢየሱስ በትውልድ አገሩ እየተዘዋወረ በሚሰብክበት ጊዜ እሱን መከተል ባትችል፣ ምክንያቱን መረዳት አያዳግትም። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ያም ሆኖ ስለ መሲሑ በተማረቻቸው መንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማሰላሰሏን እንዲሁም ቤተሰቡ ድሮም ጀምሮ የነበረውን ልማድ ተከትላ በአካባቢዋ በሚገኝ ምኩራብ መሰብሰቧን ቀጥላ ነበር።—ሉቃስ 2:19, 51፤ 4:16
ከዚህ ልማዷ አንጻር፣ ኢየሱስ በናዝሬት በነበረው ምኩራብ ውስጥ ሲናገር ከአድማጮቹ መካከል ተቀምጣ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ልጇ ከብዙ ዘመናት በፊት መሲሑን አስመልክቶ የተነገረ ትንቢት በእሱ ላይ እንደተፈጸመ ሲናገር ስትሰማ ምንኛ ተደስታ ይሆን! ይሁንና የአገሯ የናዝሬት ሰዎች እንዳልተቀበሉት ስታይ አዝና መሆን አለበት። እንዲያውም ሊገድሉት ሞክረው ነበር።—ሉቃስ 4:17-30
ሌላው የሚያስጨንቀው ጉዳይ ደግሞ የተቀሩት ልጆቿ ለኢየሱስ ያላቸው አመለካከት ነው። ከዮሐንስ 7:5 እንደምንረዳው አራቱ የኢየሱስ ወንድሞች የእናታቸው ዓይነት እምነት አልነበራቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ “ወንድሞቹም ቢሆኑ አላመኑበትም ነበር” በማለት ይናገራል። ስለ ኢየሱስ እህቶች ግን፣ (ቢያንስ ሁለት እህቶች ነበሩት) መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም። * ያም ሆነ ይህ፣ ማርያም በአንድ ቤት ውስጥ በሃይማኖት ረገድ የተለያየ አቋም መያዝ የሚያስከትለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ማወቅ ችላለች። ማርያም በአንድ በኩል ለመለኮታዊው እውነት ታማኝ ለመሆን በሌላ በኩል ደግሞ የቤተሰቧን አባላት ሳትጫናቸው ወይም ሳትነዘንዛቸው ልባቸውን ለመንካት በምታደርገው ጥረት ሚዛናዊ መሆን አስፈልጓት ነበር።
በአንድ ወቅት የኢየሱስ ዘመዶች ተሰባስበው፣ ወንድሞቹም ሳይኖሩበት አይቀርም፣ ሄደው ኢየሱስን “ሊይዙት” ፈልገው ነበር። ይህን ያደረጉት “አእምሮውን ስቷል” ብለው ስላሰቡ ነው። (ማርቆስ 3:21, 31) እርግጥ ነው፣ ማርያምም አብራቸው ሄዳለች፤ ይህን ያደረገችው ግን እንደ እንደ እነሱ አስባ ሳይሆን ልጆቿ በኢየሱስ ላይ እምነት እንዲያሳድሩ የሚያደርግ አንድ ነገር እንዲያገኙ ተስፋ በማድረግ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ያሰበችው ተሳክቶ ይሆን? ኢየሱስ አስገራሚ ተግባራትን ማከናወኑንና አስደናቂ እውነቶችን ማስተማሩን ቢቀጥልም ወንድሞቹ አላመኑበትም። ታዲያ ‘ልባቸው የሚነካው ምን ቢደረግ ነው?’ ብላ በማሰብ አዝናባቸው ይሆን?
የምትኖረው በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ከሆነ ከማርያም እምነት ብዙ ልትማር ትችላለህ። ማርያም በማያምኑ ዘመዶቿ ተስፋ አልቆረጠችም። ከዚህ ይልቅ እምነቷ ያስገኘላትን ደስታና የአእምሮ ሰላም እንዲመለከቱ አድርጋለች። በሌላ በኩል ደግሞ ታማኝ የሆነውን ልጇን መደገፏን ቀጥላለች። ኢየሱስ ከቤት በመውጣቱ ትናፍቀው ይሆን? ከእሷም ሆነ ከቤተሰቧ ጋር በቤት አብሮ እንዲኖር የተመኘችባቸው ጊዜያት ይኖሩ ይሆን? ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ተቆጣጥራው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስን መደገፍና ማበረታታት ልዩ መብት እንደሆነ አድርጋ ተመልክታዋለች። አንተስ እንደ ማርያም ልጆችህ በሕይወታቸው ውስጥ አምላክን እንዲያስቀድሙ ትረዳቸዋለህ?
“በአንቺም ነፍስ ትልቅ ሰይፍ ያልፋል”
ማርያም በኢየሱስ ላይ እምነት ማሳደሯ ወሮታ አስገኝቶላታል? ይሖዋ አገልጋዮቹ ለሚያሳዩት እምነት ወሮታ ከመክፈል ወደኋላ የሚል አምላክ አይደለም፤ ለማርያምም የሚገባትን ዋጋ ከፍሏታል። (ዕብራውያን 11:6) ልጇ ሲያስተምር ስትሰማው ወይም ሰዎች የእሱን ስብከት ሰምተው ሲነግሯት ምን ስሜት ሊያድርባት እንደሚችል አስቲ አስበው።
ልጇ የተናገራቸው ምሳሌዎች በናዝሬት ያሳለፈውን የልጅነት ሕይወት እንድታስታውስ አድርገዋት ይሆን? ምናልባትም ኢየሱስ፣ የጠፋባትን ሳንቲም ለመፈለግ ቤቷን ስለምትጠርግ አንዲት ሴት፣ እህል ስለ መፍጨት ወይም መብራት አብርቶ በመቅረዝ ላይ ስለማስቀመጥ ሲናገር ማርያም የዕለት ተዕለት ተግባሯን ስታከናውን ልጇ ከሥር ከሥሯ ሲከተላት የነበረው ሁኔታ ትዝ ብሏት ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 11:33፤ 15:8, 9፤ 17:35) ኢየሱስ ቀንበሩ ልዝብ ሸክሙም ቀላል እንደሆነ ሲናገር ማርያም ከረጅም ዓመታት በፊት ዮሴፍ ትንሽ ልጅ የነበረውን ኢየሱስን ለበሬ የሚመች ቀንበር እንዴት እንደሚሠራ በጥንቃቄ ሲያስተምረው ያየችበትን አስደሳች ጊዜ መለስ ብላ አስባ ይሆን? (ማቴዎስ 11:30) ማርያም ይሖዋ የሰጣትን ልዩ መብት፣ ይኸውም መሲሕ የሚሆነውን ልጅ የማሳደግና የማሠልጠን ኃላፊነት ማግኘቷን ስታስብ ከፍተኛ ደስታ እንዳገኘች የተረጋገጠ ነገር ነው። ታላቁ አስተማሪ በየቤቱ ያሉ ቁሳቁሶችንና በዕለት ተዕለት ሕይወት የሚያጋጥሙ ሁኔታዎችን በመጠቀም ጥልቅ የሆነ ትምህርት ሲሰጥ በማዳመጥ ልዩ ደስታ አግኝታ መሆን አለበት!
ያም ቢሆን ማርያም ትሑት ሴት ነበረች። ልጇ ለእሷ አምልኮታዊ ክብር ይቅርና ከልክ ያለፈ ትኩረት እንዲሰጣት አላደረገም። በአንድ ወቅት እያስተማረ ሳለ ከሕዝቡ መካከል አንዲት ሴት፣ እናቱ እሱን በመውለዷ ደስተኛ እንደሆነች ጮክ ብላ ተናገረች። እሱ ግን “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!” በማለት መልስ ሰጠ። (ሉቃስ 11:27, 28) በሌላ ጊዜ ደግሞ ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶች እናቱና ወንድሞቹ መምጣታቸውን ለኢየሱስ ሲነግሩት በእሱ የሚያምኑ ሁሉ እናቶቹና ወንድሞቹ እንደሆኑ ተናግሯል። ማርያም በዚህ የኢየሱስ አነጋገር ቅር ከመሰኘት ይልቅ ኢየሱስ መግለጽ የፈለገውን ነጥብ እንዳስተዋለች ይኸውም መንፈሳዊ ዝምድና ከሥጋዊ ዝምድና እንደሚበልጥ እንደተረዳች የተረጋገጠ ነው።—ማርቆስ 3:32-35
ያም ሆኖ ማርያም ልጇ በመከራ እንጨት ላይ ተሠቃይቶ ሲሞት የተሰማት ሐዘን በምን ቃል ሊገለጽ ይችላል? ኢየሱስ ሲገደል በቦታው የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ ከጊዜ በኋላ በጻፈው የወንጌል ዘገባ ላይ ማርያም በመከራው ሰዓት “ኢየሱስ በተሰቀለበት የመከራ እንጨት አጠገብ” ቆማ እንደነበረ ገልጿል። ታማኝና አፍቃሪ የሆነችውን ይህችን እናት እስከ መጨረሻው ድረስ ከልጇ ጎን ከመቆም ሊያግዳት የቻለ ምንም ነገር አልነበረም። ኢየሱስ ትንፋሹን በሳበ ወይም በተናገረ ቁጥር ከፍተኛ ሥቃይ የሚሰማው ቢሆንም እሷን ባያት ጊዜ ከመናገር ወደኋላ አላለም። እናቱን ለሚወደው ሐዋርያ ለዮሐንስ አደራ ሰጣት። የኢየሱስ የሥጋ ወንድሞች አሁንም የማያምኑ ስለነበሩ ኢየሱስ ማርያምን አደራ የሰጠው ለእነሱ ሳይሆን ለታማኝ ተከታዩ ነው። በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ አንድ የእምነት ሰው ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ማቅረቡ በተለይ ደግሞ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ማርካቱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አሳይቷል።—ዮሐንስ 19:25-27
በመጨረሻም ኢየሱስ ሲሞት ማርያም ከረጅም ጊዜ በፊት በትንቢት የተነገረው ሥቃይ ይኸውም የሐዘን ሰይፍ በውስጧ ሲያልፍ ተሰማት። በዚያ ወቅት ምን ያህል ጥልቅ ሐዘን ተሰምቷት እንደሚሆን መገመት ከባድ ከሆነብን ከሦስት ቀናት በኋላ የነበራትን ደስታ መገመትማ ይበልጥ አስቸጋሪ እንደሚሆንብን ጥያቄ የለውም! ማርያም ከተአምራት ሁሉ የሚበልጠውን ተአምር፣ ይኸውም ኢየሱስ መነሳቱን አወቀች! ቆየት ብሎ ደግሞ ለወንድሙ ለያዕቆብ (ለብቻው ሳይሆን አይቀርም) እንደተገለጠለት ባወቀች ጊዜ ደስታዋ እጥፍ ድርብ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። (1 ቆሮንቶስ 15:7) ያዕቆብ ከኢየሱስ ጋር መገናኘቱ በእሱም ሆነ በሌሎቹ ወንድሞቹ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። በኋላም ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ተቀብለዋል። ብዙም ሳይቆይ ከእናታቸው ጋር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት “ተግተው ይጸልዩ ነበር።” (የሐዋርያት ሥራ 1:14) ሁለቱ ወንድሞቹ ማለትም ያዕቆብና ይሁዳ ከጊዜ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ጽፈዋል።
ማርያም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ የተጠቀሰችው ከልጆቿ ጋር በስብሰባዎች ተገኝታ ትጸልይ እንደነበረ በሚገልጸው ዘገባ ላይ ነው። ይህ መደምደሚያ ለማርያም ታሪክ እንዴት ያለ ተስማሚ መቋጫ ነው! ደግሞም ለሁላችንም ግሩም ምሳሌ ትታለች! እምነቷ የሐዘንን ሰይፍ እንድትቋቋም ያስቻላት ሲሆን በመጨረሻም ክብራማ ወሮታ ተከፍሏታል። ማርያምን በእምነቷ የምንመስላት ከሆነ፣ ይህ ክፉ ዓለም የሚያደርስብን ቁስል ምንም ሆነ ምን ችግሩን መቋቋም እንችላለን፤ ደግሞም ከምናስበው በላይ ታላቅ ወሮታ እናገኛለን።