የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ልጆች አምላክን እንዲወዱ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?
ልጆቻችሁ አምላክን ሊወዱ የሚችሉት አምላክ መኖሩንና ለእነሱም ፍቅር እንዳለው የሚያረጋግጥ ማስረጃ ካገኙ ብቻ ነው። ልጆች አምላክን እንዲወዱት ከተፈለገ ስለ እሱ ማወቅ ይኖርባቸዋል። (1 ዮሐንስ 4:8) ለምሳሌ ያህል፣ ‘አምላክ ሰውን የፈጠረበት ዓላማ ምንድን ነው? አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? አምላክ ወደፊት ለሰው ልጆች ምን ያደርግላቸዋል?’ ስለሚሉት ጉዳዮች ማወቅ አለባቸው።—ፊልጵስዩስ 1:9ን አንብብ።
ልጆቻችሁ አምላክን እንዲወዱት ለመርዳት እናንተ ራሳችሁ እሱን እንደምትወዱት ልታሳዩአቸው ይገባል። ለአምላክ ያላችሁን ፍቅር ሲመለከቱ የእናንተን ምሳሌ መከተላቸው አይቀርም።—ዘዳግም 6:5-7ን እና ምሳሌ 22:6ን አንብብ።
የልጆቻችሁን ልብ መንካት የምትችሉት እንዴት ነው?
የአምላክ ቃል ኃይል አለው። (ዕብራውያን 4:12) በመሆኑም ልጆቻችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ትምህርቶች እንዲያውቁ እርዷቸው። ኢየሱስ የሚያስተምራቸውን ሰዎች ልብ ለመንካት ሲል ጥያቄዎችን ይጠይቃቸው፣ ያዳምጣቸው እንዲሁም ጥቅሶችን ያብራራላቸው ነበር። እናንተም የልጆቻችሁን ልብ ለመንካት የኢየሱስን የማስተማሪያ ዘዴዎች መኮረጅ ትችላላችሁ።—ሉቃስ 24:15-19, 27, 32ን አንብብ።
በተጨማሪም አምላክ ከሰዎች ጋር ስለነበረው ግንኙነት የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ልጆቻችሁ አምላክን እንዲያውቁትና እንዲወዱት ሊረዷቸው ይችላሉ። ለዚህ ዓላማ ተብለው የተዘጋጁ ጽሑፎችን www.pr418.com/am በተባለው ድረ ገጽ ላይ ማግኘት ይቻላል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16ን አንብብ።