በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

አንድን ጃንደረባ የሚያሳይ በድንጋይ ላይ የተቀረጸ የአሦራውያን ምስል

“ጃንደረባ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት እንዴት ነው?

ይህ ቃል፣ የተሰለበ ሰውን ለማመልከት የተሠራበት ጊዜ አለ። በጥንት ዘመን የነበረው አንዱ የቅጣት ዓይነት መስለብ ነበር፤ በተጨማሪም በምርኮ ወይም በባርነት የተወሰዱ አንዳንድ ወንዶች ይሰለቡ ነበር። እምነት የሚጣልባቸው የተሰለቡ ወንዶች፣ የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል የሆኑ ሴቶች የሚኖሩባቸውን ቤቶች ያስተዳድሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሄጌና ሻአሽጋዝ የሚባሉት ጃንደረቦች የፋርሱን ንጉሥ (ቀዳማዊ ጠረክሲስ እንደሆነ ይታሰባል) ሚስቶችና ቁባቶች እንዲጠብቁ ተመድበው ነበር።—አስቴር 2:3, 14

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ጃንደረባ ብሎ የሚጠራቸው ሁሉ የተሰለቡ ሰዎች ነበሩ ማለት አይደለም። አንዳንድ ምሁራን እንደሚናገሩት ቃሉ በቤተ መንግሥት ውስጥ ኃላፊነት የተሰጠውን ባለሥልጣን የሚያመለክት ሰፋ ያለ ትርጉም ነበረው። የኤርምያስ ተባባሪ የነበረውን አቤሜሌክንና ወንጌላዊው ፊልጶስ የሰበከለትን ስሙ ያልተጠቀሰ ኢትዮጵያዊ ለማመልከት ጃንደረባ የሚለው ቃል የገባው ከዚህ አንጻር ይመስላል። አቤሜሌክ፣ ንጉሥ ሴዴቅያስን በቀጥታ ያነጋግር እንደነበር ስለተገለጸ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን እንደነበረው ማየት ይቻላል። (ኤርምያስ 38:7, 8) “ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ” የነበረው ኢትዮጵያዊም የንግሥቲቱ ንብረት ኃላፊ እንደነበረ ተገልጿል።የሐዋርያት ሥራ 8:27

ይህን ያውቁ ኖሯል? በጥንት ዘመን፣ እረኞች በጎችን ከፍየሎች የሚለዩት ለምን ነበር?

ኢየሱስ ወደፊት የሚመጣውን የፍርድ ጊዜ አስመልክቶ ሲናገር ‘የሰው ልጅ በክብሩ ሲመጣ፣ እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል’ ብሏል። (ማቴዎስ 25:31, 32) እረኞች፣ እነዚህን እንስሳት ይለያዩአቸው የነበረው ለምንድን ነው?

በአብዛኛው፣ ቀን ላይ በጎችና ፍየሎች አንድ ላይ ተሰማርተው እንዲግጡ ይደረጉ ነበር። ማታ ላይ ደግሞ በጎቹና ፍየሎቹ በዱር አራዊት፣ በሌቦችና በቅዝቃዜ እንዳይጠቁ ሲባል ጉረኖ ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል። (ዘፍጥረት 30:32, 33፤ 31:38-40) ይሁንና በጎቹና ፍየሎቹ የሚያድሩት በተለያዩ ጉረኖዎች ውስጥ ነበር፤ እረኞች ይህን የሚያደርጉት በተፈጥሯቸው ይበልጥ ጠበኛ የሆኑት ፍየሎች በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ገራም የሆኑትን በጎች፣ በተለይም እንስቶቹንና ግልገሎቻቸውን እንዳይጎዷቸው ለመጠበቅ ነበር። በተጨማሪም በጎቹ “በሚወልዱበት፣ በሚታለቡበትና በሚሸለቱበት” ጊዜ እረኛው ከፍየሎቹ ይለያቸው እንደነበር ኦል ቲንግስ ኢን ዘ ባይብል የተሰኘው መጽሐፍ ተናግሯል። በመሆኑም የኢየሱስ ምሳሌ በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ከብት በማርባት በሚተዳደሩ አድማጮች ዘንድ በሚገባ የሚታወቅና በአእምሯቸው ውስጥ ምስል የሚፈጥር ነበር።