መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት
መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ለምን አስፈለገ?
የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ምን ዓይነት ውይይት እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ምሳሌ ከዚህ በታች ቀርቧል። ቢንያም የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር ኤርምያስ የሚባልን ሰው እያወያየው እንዳለ አድርገን እናስብ።
መጽሐፍ ቅዱስ—ትክክለኛ ታሪክ የያዘ መጽሐፍ
ኤርምያስ፦ እኔ ሃይማኖተኛ ሰው አይደለሁም። ስለዚህ ብዙ መወያየት የምንችል አይመስለኝም።
ቢንያም፦ ይህን በግልጽ ስለነገርከኝ አመሰግናለሁ። በነገራችን ላይ ቢንያም እባላለሁ። አንተስ?
ኤርምያስ፦ ኤርምያስ እባላለሁ።
ቢንያም፦ በመተዋወቃችን ደስ ብሎኛል።
ኤርምያስ፦ አመሰግናለሁ።
ቢንያም፦ እስቲ አንድ ነገር ልጠይቅህ። ያደግከው ሃይማኖተኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው?
ኤርምያስ፦ አዎ። ኮሌጅ ስገባ ግን ሃይማኖተኛ መሆኔን ተውኩ።
ቢንያም፦ አሃ፤ ለመሆኑ ኮሌጅ ገብተህ ያጠናኸው ምን ነበር?
ኤርምያስ፦ ማኅበራዊ ሳይንስ እና ታሪክ ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ ታሪክ መማር ያስደስተኝ ነበር።
ቢንያም፦ ልክ ነህ፣ ታሪክን ማወቅ ያስደስታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይም የተለያዩ ታሪኮች እንደሚገኙ ልብ ሳትል አትቀርም። እንደው፣ ከትምህርትህ ጋር በተያያዘ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ታሪኮች ላይ ምርምር አድርገህ ታውቃለህ?
ኤርምያስ፦ አይ፣ እንደ እሱ እንኳ አድርጌ አላውቅም። እርግጥ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ መጽሐፍ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ከታሪክ አንጻር የሚጠቅም መጽሐፍ እንደሆነ ግን ተሰምቶኝ አያውቅም።
ቢንያም፦ እንደማይህ ከሆነ ሰፊ አመለካከት ያለህ ሰው ነህ። ጥቂት ደቂቃ ካለህ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ታሪክ እንደያዘ የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ላሳይህ።
ኤርምያስ፦ እሺ። ግን መጽሐፍ ቅዱስ የለኝም።
ቢንያም፦ ችግር የለም። ከእኔ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ላሳይህ እችላለሁ። የመጀመሪያው ምሳሌ የሚገኘው 1 ዜና መዋዕል ምዕራፍ 29፣ ቁጥር 26 እና 27 ላይ ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “የእሴይ ልጅ ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር። እርሱም በኬብሮን ሰባት ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት፣ በአጠቃላይ አርባ ዓመት ነገሠ።”
ኤርምያስ፦ ታዲያ ይህ ጥቅስ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ታሪክ እንደያዘ የሚያሳየው እንዴት ነው?
ቢንያም፦ ይኸውልህ ኤርምያስ፣ አንዳንድ ሰዎች ንጉሥ ዳዊት የሚባል ሰው ኖሮ እንደማያውቅ ይናገሩ ነበር።
ኤርምያስ፦ ኧረ? እንዲህ የሚሉት ለምን ነበር?
ቢንያም፦ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ፣ ዳዊት በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ሰው መሆኑን የሚጠቁም በቂ ማስረጃ ስላልነበረ ነው። ይሁን እንጂ በ1993 የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች “የዳዊት ቤት” የሚል ትርጉም ያለው ጽሑፍ የተቀረጸበት በጣም ጥንታዊ የሆነ ድንጋይ በቁፋሮ አገኙ።
ኤርምያስ፦ ኧረ ባክህ፣ በጣም ይገርማል።
ቢንያም፦ በሕይወት የነበረ ስለ መሆኑ ጥያቄ የተነሳበት ሌላው ሰው ደግሞ በኢየሱስ ዘመን ገዢ የነበረው ጳንጥዮስ ጲላጦስ ነው። በሉቃስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 1 ላይ ከተጠቀሱት ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ይህ ሰውም ይገኝበታል።
ኤርምያስ፦ አዎ። “ጳንጥዮስ ጲላጦስ የይሁዳ አገረ ገዥ” እንደነበር ይናገራል።
ቢንያም፦ ልክ ነህ። ለብዙ ዓመታት አንዳንድ ምሁራን
ጳንጥዮስ ጲላጦስ በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን ይጠራጠሩ ነበር። በኋላም ከ50 ዓመታት ገደማ በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ የጲላጦስ ስም የተቀረጸበት አንድ ድንጋይ ተገኘ።ኤርምያስ፦ ይገርማል። ስለዚህ ጉዳይ ሰምቼ አላውቅም።
ቢንያም፦ ስለ እነዚህ ጉዳዮች የመነጋገር አጋጣሚ በማግኘታችን ደስ ብሎኛል።
ኤርምያስ፦ እውነቱን ለመናገር ከድሮም ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ የሥነ ጽሑፍ ሥራ እንደሆነ አምን ነበር፤ ለዚህ ዘመን የሚጠቅም ቁም ነገር ይገኝበታል ብዬ ግን አስቤ አላውቅም። ትክክለኛ ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ሊሆን ቢችልም ለእኛ የሚጠቅም መረጃ ይገኝበታል ብሎ ማመን ይከብደኛል።
መጽሐፍ ቅዱስ—ጥንታዊ ሆኖም ዘመናዊ መጽሐፍ
ቢንያም፦ ብዙ ሰዎች እንዲህ ይሰማቸዋል። እኔ ግን እንዲህ ብዬ አላምንም። ለምን መሰለህ፣ ሰዎች ስንባል መሠረታዊ ፍላጎቶቻችን ምንጊዜም ቢሆን ተመሳሳይ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ጥንትም ሆነ ዛሬ ማንኛውም ሰው ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ያስፈልገዋል። ያኔም ሆነ አሁን ሰዎች እርስ በርስ መጨዋወት ያስደስታቸዋል፤ እንዲሁም በአጠቃላይ ሲታይ ደስተኛ ቤተሰብ እንዲኖረን እንፈልጋለን። ሁላችንም ለእነዚህ ነገሮች ትልቅ ቦታ እንሰጣለን ቢባል አትስማማም?
ኤርምያስ፦ ልክ ነህ።
ቢንያም፦ የሚገርምህ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከእነዚህ ነገሮች ጋር በተያያዘ ሊጠቅመን የሚችል ሐሳብ ይዟል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ ሆኖም ዘመናዊ መጽሐፍ ነው ልንል እንችላለን።
ኤርምያስ፦ ምን ማለትህ ነው?
ቢንያም፦ ምን መሰለህ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ቢሆንም በውስጡ የሚገኙት መመሪያዎች ለዘመናችንም ቢሆን ይጠቅማሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ቢሆንም በውስጡ የሚገኙት መመሪያዎች ለዘመናችንም ቢሆን ይጠቅማሉ
ኤርምያስ፦ እንዴት?
ቢንያም፦ ለምሳሌ ለገንዘብ ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት፣ የቤተሰብ ሕይወትን አስደሳች ስለ ማድረግ ወይም ጥሩ ጓደኛ ስለ መሆን የሚገልጹ መመሪያዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ስኬት የምናገኝበትን አቅጣጫ የሚጠቁመን ካርታ ነው ሊባል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በዛሬው ጊዜ ጥሩ ባልና ጥሩ አባት መሆን ተፈታታኝ ነው፣ አይደል?
ኤርምያስ፦ አዎ፣ ልክ ነህ። ከባለቤቴ ጋር ከተጋባን አንድ ዓመት ሆኖናል፤ አለመግባባት እንዳይፈጠር ማድረግ ግን ሁልጊዜ ቀላል አይደለም።
ቢንያም፦ ትክክል ነህ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጠቃሚ የሆኑ መመሪያዎችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ ኤፌሶን ምዕራፍ 5ን ተመልከት። እስቲ ቁጥር 22ን፣ 23ን እና 28ን እናንብብ። ከፈለግህ እነዚህን ጥቅሶች አንተ ልታነብባቸው ትችላለህ።
ኤርምያስ፦ እሺ። “ሚስቶች ለጌታ እንደሚገዙ ሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ፤ ምክንያቱም ክርስቶስ አካሉ ለሆነውና አዳኙ ለሆነለት ጉባኤ ራስ እንደሆነ ሁሉ ባልም የሚስቱ ራስ ነው።” ቁጥር 28 ደግሞ “በዚህ መንገድ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል። ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል” ይላል።
ቢንያም፦ አመሰግናለሁ። ታዲያ ባልም ሆነ ሚስት ይህን ቀላል ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ቢያደርጉ የቤተሰብ ሕይወታቸው አስደሳች የሚሆን አይመስልህም?
ኤርምያስ፦ አዎ፣ ይመስለኛል። ግን ይህን ማድረግ የመናገሩን ያህል ቀላል አይደለም።
ቢንያም፦ እውነት ነው፣ ፍጹም የሆነ ሰው የለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያታዊ እንድንሆን ያበረታታናል። * በማንኛውም ዓይነት ዝምድና ቢሆን ምክንያታዊ መሆንና ከራስ ፍላጎት ይልቅ የሌላውን ማስቀደም አስፈላጊ ነው። እኔና ባለቤቴ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ እንድናዳብር መጽሐፍ ቅዱስ ረድቶናል።
ኤርምያስ፦ ጥሩ ሐሳብ ነው።
ቢንያም፦ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ከትዳርና ከቤተሰብ ሕይወት ጋር በተያያዘ ጥሩ ምክር የሚሰጥ ድረ ገጽ አላቸው። ጊዜ ካለህ ድረ ገጹ ላይ ከወጡት ምክሮች መካከል አንዱን አብረን ማየት እንችላለን።
ኤርምያስ፦ እሺ። የተወሰኑ ደቂቃዎች መቆየት እችላለሁ።
ቢንያም፦ የድረ ገጻችን አድራሻ www.pr418.com/am ነው። የድረ ገጹ መነሻ ገጽ ይኸውልህ።
ኤርምያስ፦ ፎቶዎቹ ደስ ይላሉ።
ቢንያም፦ እነዚህ ፎቶዎች በዓለም ዙሪያ የምናከናውነውን
የስብከት ሥራ የሚያሳዩ ናቸው። እሺ፣ ቅድም ያልኩህ ይኸውልህ። “ለባለትዳሮችና ለወላጆች” የሚለው ክፍል ውስጥ ስንገባ የተለያዩ ጉዳዮችን የሚዳስሱ በርካታ አጫጭር ርዕሶች አሉ። ከእነዚህ መካከል የትኛውን ብናይ ደስ ይልሃል?ኤርምያስ፦ “በትዳር ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት” የሚለውን። ሐሳቡ የሚጠቅመኝ ይመስለኛል!
ቢንያም፦ ይህ ርዕስ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዱ አራት ነገሮችን ይዘረዝራል። እስቲ ይህን ዓረፍተ ነገር ልብ በለው። ልታነበው ትችላለህ?
ኤርምያስ፦ እሺ። “የሐሳብ ግንኙነት ለአንድ ትዳር የደም ሥር ከሆነ ፍቅርና አክብሮት ደግሞ እንደ ልብና እንደ ሳምባ ሊታዩ ይችላሉ።” ደስ የሚል አባባል ነው።
ቢንያም፦ አመሰግንሃለሁ። እዚህ ላይ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ተጠቅሷል። ጥቅሱን ጠቅ በማድረግ ሐሳቡን ማንበብ ትችላለህ።
ኤርምያስ፦ አዎ፣ ልክ ነህ። ኤፌሶን 5:33 ነው፣ አይደል? ሐሳቡ እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ልታከብር ይገባል።”
ቢንያም፦ ጥቅሱ፣ ባለትዳሮች አንዳቸው ሌላው የሚፈልገውን ነገር መስጠት እንዳለባቸው አጉልቶ የሚገልጽ ነው።
ኤርምያስ፦ ምን ለማለት እንደፈለግህ አልገባኝም።
ቢንያም፦ ይኸውልህ፣ አንድ ባል ሚስቱ እንድታከብረው እንደሚፈልግ ግልጽ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት ሚስት ባሏ ሁልጊዜ እንደሚወዳት እንዲሰማት ትፈልጋለች።
ኤርምያስ፦ አዎ፣ ልክ ነህ።
ቢንያም፦ አንድ ባል ለሚስቱ ያለውን ፍቅር ዘወትር ለማሳየት ጥረት የሚያደርግ ከሆነ ሚስቱ እሱን ማክበር ቀላል ይሆንላታል ቢባል አትስማማም?
ኤርምያስ፦ እውነትህን ነው።
ቢንያም፦ ባልም ሆነ ሚስት ከትዳራቸው የሚፈልጉት ምን እንደሆነ የሚገልጸው ይህ ጥቅስ የተጻፈው ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ቢሆንም ለባለትዳሮች ጠቃሚ ምክር ይዟል፤ ባለትዳሮች ይህን ምክር ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሆነ ትዳራቸው የሰመረ ይሆናል፤ በሌላ አባባል ቀደም ሲል ባነበብነው ዓረፍተ ነገር ላይ የተጠቀሱት የትዳር “ልብና ሳንባ” ጤናማ ይሆናሉ።
ኤርምያስ፦ በጣም ይገርማል፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት ምክሮችን ይዟል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር።
ቢንያም፦ እንደዚህ ስለተሰማህ ደስ ብሎኛል። በዚሁ ርዕስ ላይ “ችግሮችን ለመፍታት የሚረዱ አራት ነጥቦች” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ሌሎች ሐሳቦችም ተገልጸዋል፤ በሌላ ጊዜ ተገናኝተን በእነዚህ ሐሳቦች ላይ ብንነጋገር ደስ ይለኛል። *
ኤርምያስ፦ እኔም ደስ ይለኛል። እንዲያውም ርዕሱን ከባለቤቴ ጋር ሆነን እናነበዋለን።
ግራ የሚያጋባህ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ አለ? የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ወይም ስለ ሃይማኖታቸው ማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስትገናኝ ጥያቄህን ከማቅረብ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከአንተ ጋር መወያየት ያስደስታቸዋል።
^ አን.43 ፊልጵስዩስ 4:5ን ተመልከት።
^ አን.63 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 14 ተመልከት።