የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
የኢየሱስን ሞት ማስታወስ ያለብን ለምንድን ነው?
በታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት ነገሮች ሁሉ ትልቁ የኢየሱስ ሞት ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ የሞተው የሰው ልጆች ያሉበት ሁኔታ ወደ ቀድሞው እንዲመለስ ለማድረግ ሲል ነው። ሰዎች ሲፈጠሩ መጥፎ ነገሮችን የማድረግ ዝንባሌ አልነበራቸውም፤ እንዲሁም አይታመሙም ወይም አይሞቱም ነበር። (ዘፍጥረት 1:31) ነገር ግን ኃጢአት በመጀመሪያው ሰው በአዳም በኩል ወደ ዓለም ገባ። ኢየሱስ እኛን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ሲል የራሱን ሕይወት ሰጥቷል።—ማቴዎስ 20:28ን እና ሮም 6:23ን አንብብ።
አምላክ ልጁን ወደ ምድር በመላክ እንዲሞትልን ማድረጉ ለእኛ ታላቅ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። (1 ዮሐንስ 4:9, 10) ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ቂጣና የወይን ጠጅ በመጠቀም ቀለል ባለ መንገድ የእሱን ሞት እንዲያስታውሱ አዝዞ ነበር። በየዓመቱ እሱ ባዘዘው መንገድ ሞቱን ማስታወሳችን አምላክና ኢየሱስ ላሳዩን ፍቅር አድናቆታችንን የምንገልጽበት አንዱ መንገድ ነው።—ሉቃስ 22:19, 20ን አንብብ።
ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈል ያለባቸው እነማን ናቸው?
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሞቱን እንዲያስታውሱ መጀመሪያ በተናገረበት ወቅት ስለ አንድ ቃል ኪዳን ወይም ውል ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 26:26-28) ይህ ቃል ኪዳን ለእነሱና የተወሰነ ቁጥር ላላቸው ሌሎች ሰዎች ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ነገሥታትና ካህናት የመሆን አጋጣሚ ከፍቷል። የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ የሚያከብሩት ሰዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቢሆኑም ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈሉት ግን በቃል ኪዳኑ ውስጥ የታቀፉት ብቻ ናቸው።—ራእይ 5:10ን አንብብ።
ይሖዋ ወደ 2,000 ለሚጠጉ ዓመታት ያህል ነገሥታት የሚሆኑትን ሰዎች ሲመርጥ ቆይቷል። (ሉቃስ 12:32) በምድር ላይ በገነት ውስጥ የመኖር ተስፋ ካላቸው ሰዎች ጋር ሲነጻጸር የእነዚህ ሰዎች ቁጥር ጥቂት ነው።—ራእይ 7:4, 9, 17ን አንብብ።