ታሪካዊ የሆነ መንፈሳዊ ክንውን!
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በአማርኛ ወጣ
ታኅሣሥ 13, 2014 ታሪካዊ የሆነ አንድ መንፈሳዊ ክንውን ተከናውኗል፤ በዚህ ዕለት አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በአማርኛ ወጣ።
አዲስ ዓለም ትርጉም በኢትዮጵያ የሚገኙ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች፣ ለብዙ ዓመታት ሲጠቀሙባቸው ከነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አንዱ ለመሆን በቃ። ይሁንና ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማዘጋጀት ያስፈለገው ለምንድን ነው? ሥራውን ያከናወነው ማን ነው? አዲስ ዓለም ትርጉም እምነት የሚጣልበት ትርጉም ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ያስፈለጉት ለምንድን ነው?
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እጅግ በርካታ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ተዘጋጅተዋል። አንዳንዶቹ አዳዲስ ትርጉሞች የአምላክ ቃል በአንዳንድ ቋንቋዎች ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲገኝ አስችለዋል። ይሁን እንጂ በሌሎች ቋንቋዎች ለረጅም ጊዜ ሲሠራባቸው የቆዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቢኖሩም አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ማዘጋጀት አስፈልጓል። ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? በሳካኢ ኩቦ እና ዎልተር ስፔችት የተዘጋጀው ሶ ሜኒ ቨርዥንስ? የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ቢሆን የመጨረሻው ትርጉም ነው ሊባል አይችልም። በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ የሚደረጉ ጥናቶች አዳዲስ ነገሮችን ስለሚያስገኙና ቋንቋ እየተለወጠ ስለሚሄድ ከዚህ ጋር እኩል ለመራመድ አዳዲስ የትርጉም ሥራዎች የግድ ያስፈልጋሉ።”
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተጻፈባቸውን ቋንቋዎች ይኸውም ዕብራይስጥ፣ አረማይክና ግሪክኛ ቋንቋዎችን በመረዳት ረገድ ከፍተኛ እመርታ ታይቷል። ከዚህም በተጨማሪ ቀደም ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ይጠቀሙባቸው ከነበሩት ጥንታዊ ቅጂዎች ይበልጥ እጅግ ጥንታዊ የሆኑና ሐሳቡን በተሻለ ሁኔታ የሚያስተላልፉ ቅጂዎች ተገኝተዋል። በመሆኑም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ የአምላክን ቃል በትክክል መተርጎም ተችሏል።
የዓለም አቀፍ ንግድ ፕሮፌሰር የሆኑት ዴክላን ሃይስ “መጽሐፍ ቅዱስ በየዓመቱ በብዛት በመሸጥ ረገድ ተወዳዳሪ የማይገኝለት
መጽሐፍ ነው” ብለው ጽፈዋል። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች መጽሐፉ በብዛት እንዲሸጥ ለማድረግ ያላቸው ፍላጎት መልእክቱን በትክክል የማስተላለፉን ጉዳይ ቸል እንዲሉ አድርጓቸዋል። የአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አሳታሚዎች ለአንባቢዎች “አሰልቺ” ይሆንባቸዋል ብለው ያሰቡትን ክፍል እስከማውጣት ደርሰዋል። ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ያሳተሙ ሰዎች ደግሞ የዘመኑን አንባቢዎች ቅር ያሰኛሉ ብለው ያሰቧቸውን ቃላት ወይም አባባሎች ለውጠዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክን “አባት-እናት” ብለው በመግለጽ አንዳንድ አንባቢዎችን ለማስደሰት ሞክረዋል።መለኮታዊውን ስም መሰወር
ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው ነገር ይሖዋ ከሚለው የአምላክ የግል ስም ጋር በተያያዘ እየተለመደ የመጣው አሠራር ሳይሆን አይቀርም። (አንዳንድ ምሁራን የአምላክን ስም “ያህዌህ” ብለው ተርጉመውታል።) ጥንታዊ በሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ መለኮታዊው ስም ተነባቢ በሆኑ አራት የዕብራይስጥ ፊደላት ተጽፎ የሚገኝ ሲሆን ፊደላቱ የሐወሐ ተብለው በቀጥታ ሊተረጎሙ ይችላሉ። ይህ ልዩ ስም በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብሎ በሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ብቻ 7,000 ጊዜ ያህል ይገኛል። (ዘፀአት 3:15፤ መዝሙር 83:18) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደምንችለው ፈጣሪያችን አገልጋዮቹ ስሙን እንዲያውቁና በስሙ እንዲጠሩት ይፈልጋል!
ይሁን እንጂ ከበርካታ መቶ ዘመናት በፊት አይሁዳውያን ከአጉል እምነት በመነጨ ፍርሃት የተነሳ መለኮታዊውን ስም መጥራት አቆሙ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ እንዲህ ያለው በአጉል እምነት ላይ የተመሠረተ አመለካከት ወደ ክርስቲያኖችም ተጋባ። (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1) የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መለኮታዊውን ስም “ጌታ” በሚለው የማዕረግ ስም መተካታቸው የተለመደ እየሆነ መጣ። በዛሬው ጊዜ በአብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ የአምላክ ስም ፈጽሞ አይገኝም። አንዳንድ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ዮሐንስ 17:6 ላይ ኢየሱስ “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ” ብሎ በተናገረበት ቦታ ላይ የሚገኘውን “ስምህን” የሚለውን ቃል እንኳ ሳይቀር አውጥተውታል። በ1980 የታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሱን “የአንተን ማንነት ገለጥኩላቸው” ብሎ ተርጉሞታል።
ታዲያ ተርጓሚዎቹ ለአምላክ ስም ይህን ያህል ጥላቻ ያደረባቸው ለምንድን ነው? ፕራክቲካል ፔፐርስ ፎር ዘ ባይብል ትራንስሌተር (ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የተዘጋጀ ጠቃሚ መመሪያ) በተባለው መጽሔት ላይ የወጣውን ሐሳብ እንመልከት። መጽሔቱን ያዘጋጀው፣ የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት በመባል የሚታወቀው አብዛኛውን የዓለም አቀፉን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ የሚያስተባብረው ማኅበር ነው። ይህ መጽሔት በአንድ ርዕስ ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ አውጥቷል፦ “የሐወሐ የግል ስም መሆኑ የታወቀ ነው፤ በመሆኑም በደንቡ መሠረት ስሙ ሳይተረጎም እንዳለ መቀመጡ ተገቢ የሆነ የትርጉም አሠራር መርሕ ነው።” ይሁንና ጽሑፉ በመቀጠል “መዘንጋት የማይኖርባቸው አንዳንድ እውነታዎች ግን አሉ” ሲል ማስጠንቀቂያ አዘል ሐሳብ አስፍሯል።
እነዚህ “እውነታዎች” ምን ያህል ተቀባይነት አላቸው? መጽሔቱ እንደሚለው አንዳንድ ምሁራን እንዲህ የሚል አስተሳሰብ አላቸው፦ “ያህዌህ እንደሚለው ያለ ስም ማስገባታችን የተሳሳተ መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል፤ . . . ይህም የሚሆነው ሰዎች፣ ‘ያህዌህ’ የተባለው አምላክ እነሱ ከሚያውቁት አምላክ የተለየ እንደሆነ ስለሚያስቡ ነው፤ ስለ አንድ ባዕድ አምላክ ወይም መጤና የማይታወቅ አምላክ እየተናገርን እንዳለ ሊሰማቸው ይችላል።” ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አምላክ ከእውነተኛው ክርስትና ውጭ ያሉ ሰዎች ከሚያመልኳቸው አማልክት የተለየ እንደሆነ በማያሻማ መንገድ ያስተምራል!—ኢሳይያስ 43:10-12፤ 44:8, 9
አንዳንድ ምሁራን የአምላክን ስም “ጌታ” በሚለው የማዕረግ ስም የሚተኩት የቆየውን ልማድ በመከተል እንደሆነ ይናገራሉ። ኢየሱስ ግን ለአምላክ ክብር የማይሰጡ ልማዶችን መከተልን አውግዟል። (ማቴዎስ 15:6) ከዚህ በተጨማሪ አንድን ስም በማዕረግ ስም ለመተካት የሚያስችለን ምንም ዓይነት ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ አናገኝም። ኢየሱስ ክርስቶስ “የአምላክ ቃል” እና “የነገሥታት ንጉሥ” እንደሚሉት ያሉ ብዙ የማዕረግ ስሞች አሉት። (ራእይ 19:11-16) ታዲያ ኢየሱስ የሚለው ስም ከእነዚህ የማዕረግ ስሞች በአንዱ መተካት ይኖርበታል?
ከላይ የተጠቀሰው መጽሔት ባወጣው ሌላ ርዕስ ላይ “በመሠረቱ ‘ይሖዋ’ በሚለው ስም ከመጠቀም መቆጠብ ይኖርብናል” ሲል በአጽንኦት ገልጿል። ምክንያቱ ምንድን ነው? “የስሙን የመጀመሪያ አጠራር በተሻለ ሁኔታ የሚገልጸው ‘ያህዌህ’ የሚለው አጠራር እንደሆነ አብዛኞቹ ምሁራን ይስማማሉ።” ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስና ኢየሱስ የሚሉት የታወቁ ስሞች ከመጀመሪያው የዕብራይስጥ አጠራር (የሻያሁ፣ ዪርሚያህ እና ዬሆህሹአ) ጋር እምብዛም ተመሳሳይነት የላቸውም። “ይሖዋ” የሚለው ተቀባይነት ያለው አጠራር ለብዙ መቶ ዓመታት በአማርኛም ሆነ በሌሎች ቋንቋዎች ሲሠራበት የቆየ ከመሆኑ አንጻር መለኮታዊው ስም በዚህ መንገድ መጠራት የለበትም የሚለው ተቃውሞ አሳማኝ አይደለም። በእርግጥም መለኮታዊውን ስም ለመጠቀም አለመፈለግ በግል አመለካከትና በጭፍን ጥላቻ ላይ የተመሠረተ እንጂ በጥናታዊ መረጃ የተደገፈ አይደለም።
ዘፀአት 34:6, 7) መጽሐፍ ቅዱስ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ይላል። (ሮም 10:13) በእርግጥም፣ የአምላክ አገልጋዮች በስሙ መጠቀማቸው የግድ አስፈላጊ ነው!
ይሁን እንጂ ይህ፣ ተጨባጭ ማስረጃዎቹ የሚሉትን የማወቅ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በሕንድ የሚገኝ የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት አማካሪ የሆነ ግለሰብ መለኮታዊውን ስም ቀድሞ ከሚገኝባቸው እትሞች ውስጥ ማውጣት የሚያስከትለውን ችግር በተመለከተ አንድ ጽሑፍ አውጥቶ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሂንዱዎች ለአምላክ የሚሰጠው የማዕረግ ስም ብዙም ትርጉም አይሰጣቸውም፤ እነሱ ማወቅ የሚፈልጉት የአምላክን የግል ስም ነው፤ ስሙን ካላወቁ ከስሙ ባለቤት ጋር እንዴት ሊዛመዱ እንደሚችሉ አይገባቸውም።” አምላክን ማወቅ የሚፈልጉ ሁሉ እንዲህ ዓይነት ስሜት እንደሚኖራቸው ግልጽ ነው። የአምላክን ማንነት ማወቅ ከፈለግን ስሙን ማወቃችን ወሳኝ ነገር ነው፤ ደግሞም በሁሉም ቦታ የሚገኝ ኃይል ሳይሆን ራሱን የቻለ አካል መሆኑን ስንገነዘብ ከእሱ ጋር መቀራረብ እንደምንችል እንረዳለን። (አምላክን የሚያስከብር የትርጉም ሥራ
በመሆኑም በ1950 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም (እንግሊዝኛ) ለመጀመሪያ ጊዜ መውጣቱ ታሪካዊ ክንውን ነበር። በቀጣዩ አሥር ዓመት ውስጥ ደግሞ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት (በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብሎ ይጠራል) በተለያዩ ክፍሎች ታትመው ወጡ። ከዚያም በ1961 ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በእንግሊዝኛ በአንድ ጥራዝ ወጣ። አዲስ ዓለም ትርጉም፣ በብሉይ ኪዳን ውስጥ “ይሖዋ” የሚለውን መለኮታዊ ስም 7,000 የሚያህሉ ቦታዎች ላይ መልሶ ማስገባቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። በተለይም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ወይም “በአዲስ ኪዳን” ውስጥ መለኮታዊው ስም 237 በሚያህሉ ቦታዎች ላይ ተመልሶ እንዲገባ መደረጉ ትኩረት ይስባል።
ስሙ ቦታው ላይ ተመልሶ መግባቱ አምላክን የሚያስከብር ከመሆኑም ሌላ እሱን በትክክል እንድናውቀው ያስችለናል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ብዙ መጽሐፍ ቅዱሶች ማቴዎስ 22:44ን ‘ጌታ ጌታዬን በቀኜ ተቀመጥ አለው’ ብለው ተርጉመውታል። ይሁንና ተናጋሪው ማን ነው? እየተናገረ ያለውስ ለማን ነው? አዲስ ዓለም ትርጉም ከመዝሙር 110:1 ላይ በቀጥታ በመጥቀስ ማቴዎስ 22:44ን ‘ይሖዋ ጌታዬን በቀኜ ተቀመጥ አለው’ ብሎ ተርጉሞታል። ስለዚህ አንባቢዎች ይሖዋ አምላክና ልጁ ፈጽሞ የተለያዩ መሆናቸውን ማስተዋል ይችላሉ።
ሥራውን ያከናወነው ማን ነው?
አዲስ ዓለም ትርጉምን ያዘጋጀው ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ሲሆን ይህ ማኅበር የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙበት ሕጋዊ ድርጅት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ከአንድ መቶ ለሚበልጡ ዓመታት በዓለም ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱሶችን ሲያትሙና ሲያሰራጩ ቆይተዋል። አዲስ ዓለም ትርጉምን ለይሖዋ ምሥክሮች ያበረከተው የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ በሚል ስያሜ የሚጠሩ ክርስቲያኖችን ያቀፈ የተርጓሚዎች ቡድን ነው። የኮሚቴው አባላት ለራሳቸው ክብር ማግኘት ስላልፈለጉ ከሞቱም በኋላ ጭምር ማንነታቸው እንዳይገለጽ ጠይቀዋል።—1 ቆሮንቶስ 10:31
ይህ መጽሐፍ ቅዱስ አዲስ ዓለም ትርጉም የሚል ስያሜ የተሰጠው ለምንድን ነው? የ1950ው እትም በመቅድሙ ላይ ለመጽሐፉ የተሰጠው ስያሜ በ2 ጴጥሮስ 3:13 ላይ በተሰጠው ተስፋ መሠረት የሰው ዘር “አዲሱ ዓለም ደፍ ላይ እንደሚገኝ” ያለንን ጽኑ እምነት እንደሚያንጸባርቅ ገልጾ ነበር። ኮሚቴው “ከአሮጌው ዓለም ጽድቅ ወደሰፈነበት አዲስ ዓለም በምንሸጋገርበት” በዚህ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ንጹሕ የሆነው የአምላክ ቃል እውነት” ቦግ ብሎ እንዲበራ ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው ሲል ጽፏል።
ትክክለኛ ትርጉም
መልእክቱን በትክክል መተርጎም ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ ነው። የእንግሊዝኛውን እትም ያዘጋጁት ተርጓሚዎች ሥራውን ያከናወኑት መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ይኸውም በዕብራይስጥ፣ በአረማይክና በግሪክኛ * የጥንቱን ጽሑፍ በተቻለ መጠን ምንም ሳያዛቡ ለመተርጎም ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገዋል፤ ይሁንና መጽሐፉ የተተረጎመው በዚህ ዘመን ያሉ አንባቢዎች በቀላሉ ሊገባቸው በሚችል መንገድ ነው።
የተዘጋጁትን ከሁሉ የተሻሉ የሚባሉ ቅጂዎች በመጠቀም ነው።አንዳንድ ምሁራን አዲስ ዓለም ትርጉም ወጥነት ያለውና ትክክለኛ ትርጉም መሆኑን አስመልክተው አድናቆታቸውን መግለጻቸው የሚያስገርም አይደለም። በእስራኤል የሚገኙት ዕብራዊው ምሁር ፕሮፌሰር ቤንጃሚን ኬዳር በ1989 እንዲህ ብለው ነበር፦ “ከዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስና ከዕብራይስጥ ከተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶች ጋር በተያያዘ በማካሂደው የቋንቋ ጥናት አዲስ ዓለም ትርጉም ተብሎ የሚጠራውን የእንግሊዝኛ እትም የማመሳከር ልማድ አለኝ። ይህን በማደርግበት ጊዜ የትርጉም ሥራው ጽሑፉን በተቻለ መጠን በትክክል ለመረዳት በቅንነት ጥረት የተደረገበት ሥራ መሆኑን እንዳምን የሚያስችሉኝ ብዙ ማስረጃዎች አግኝቻለሁ።”
በሌሎች ቋንቋዎች መተርጎም
የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ዓለም ትርጉምን በእንግሊዝኛ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቋንቋዎችም ማዘጋጀቱን ተገቢ ሆኖ አግኝተውታል። በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በ127 ቋንቋዎች ተተርጉሟል። ሥራውን ለማቀላጠፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ላይ የተደረገውን ጥናት ከኮምፒውተር ጋር በማቀናጀት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ማከናወን የሚቻልበት መንገድ ተዘጋጅቷል። ተርጓሚዎቹን ለመርዳት ደግሞ የትርጉም አገልግሎት ክፍል ተቋቁሟል። የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል፣ በጽሑፍ ኮሚቴው አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎሙን ሥራ በቅርብ ይከታተላል። ለመሆኑ የትርጉም ሥራው የሚከናወነው እንዴት ነው?
በመጀመሪያ፣ ለአምላክ ያደሩ የተወሰኑ ክርስቲያኖች፣ ተርጓሚዎች ሆነው በቡድን እንዲሠሩ ይመደባሉ። ተርጓሚዎች በተናጠል ከሚሠሩ ይልቅ በቡድን ሆነው መተርጎማቸው የተሻለ ጥራት ያለውና ብዙዎችን ያማከለ የትርጉም ሥራ ሊያስገኝ እንደሚችል ከተሞክሮ ታይቷል። (ምሳሌ 11:14) በጥቅሉ ሲታይ የቡድኑ አባላት የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች በመተርጎም ረገድ ልምድ ያካበቱ ናቸው። ከዚያም ተርጓሚዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም የሚያገለግሉትን መሠረታዊ ደንቦችና ለዚህ ተብሎ የተዘጋጀውን የኮምፒውተር ፕሮግራም እንዲያውቁ ሰፋ ያለ ሥልጠና ይሰጣቸዋል።
የትርጉም ቡድኑ ትክክለኛ ሆኖም ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊረዳው የሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዲያዘጋጅ ይጠበቅበታል። የትርጉም ሥራው በተቻለ መጠን ቃል በቃል እንዲሆን የሚፈለግ ቢሆንም መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ሊተላለፍ የተፈለገውን መልእክት የሚያዛባ መሆን ግን የለበትም። ይህን ማሳካት የሚቻለው እንዴት ነው? በቅርቡ የወጣውን መጽሐፍ ቅዱስ ተመልከት። የትርጉም ቡድኑ ሥራውን የጀመረው በእንግሊዝኛ አዲስ ዓለም ትርጉም ውስጥ ለተሠራባቸው ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት የአማርኛ አቻ ቃላት በመስጠት ነው። በኮምፒውተር የሚታገዘው ዎችታወር ትራንስሌሽን ሲስተም ተቀራራቢና ተዛማጅ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትን ደርድሮ ያስቀምጣል። በተጨማሪም ፕሮግራሙ በእንግሊዝኛ የተቀመጡት ቃላት የተገኙባቸውን የግሪክኛ ወይም የዕብራይስጥ ቃላት የሚያሳይ ሲሆን ይህም ተርጓሚዎቹ እነዚህ የግሪክኛ ወይም የዕብራይስጥ ቃላት በሌሎች ቦታዎች ላይ ምን ተብለው እንደተተረጎሙ እንዲያዩ ያስችላቸዋል። ይህ ዝግጅት አቻ የሆኑትን የአማርኛ ቃላት ለመምረጥ ትልቅ እገዛ ያበረክታል። ቡድኑ ቃላቱን ተርጉሞ ከጨረሰ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም ይጀምራል፤ በዚህ ጊዜ ተርጓሚዎቹ እያንዳንዱ ጥቅስ ላይ ሲደርሱ ፕሮግራሙ በጥቅሱ ላይ ላሉት ቃላት አቻ የሆኑትን የአማርኛ ቃላት ያሳያቸዋል።
ይሁን እንጂ የትርጉም ሥራ የተወሰኑ ቃላትን በሌላ ቃላት የመተካት ጉዳይ ብቻ አይደለም። የተመረጡት የአማርኛ ቃላት በእያንዳንዱ ጥቅስ ላይ ትክክለኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ የሚያስተላልፉ እንዲሆኑ ማድረግ ከፍተኛ ሥራ ይጠይቃል። የሰዋስው ሥርዓቱና የዓረፍተ ነገር አወቃቀሩ የሚጥምና ጥሩ አማርኛ እንዲሆን አስቦ መሥራት ያስፈልጋል። የትርጉም ሥራው ምን ያህል የተለፋበት እንደሆነ ከራሱ ከመጽሐፉ በግልጽ ማየት ይቻላል። በአማርኛ የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም የአምላክን ቃል ለማንበብ በሚጥም፣ ግልጽ በሆነና በቀላሉ በሚገባ መንገድ በመተርጎም ጥንታዊው ጽሑፍ የያዘውን ሐሳብ በታማኝነት አስተላልፏል። *
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስን እንድታነበው እናበረታታሃለን። መጽሐፉን ከዚህ መጽሔት አሳታሚዎች ወይም በአካባቢህ ካለ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ማግኘት ትችላለህ። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በገዛ ቋንቋህ የአምላክን ቃል ምንም ሳያዛንፍ እንደሚያስተላልፍ እርግጠኛ ሆነህ ማንበብ ትችላለህ። በቅርቡ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱ በእርግጥም ታሪካዊ የሆነ መንፈሳዊ ክንውን ነው፤ አንተም በዚህ እንደምትስማማ ጥርጥር የለውም!
^ አን.24 የመጀመሪያው የእንግሊዝኛ እትም ሲዘጋጅ የግሪክኛውን ጽሑፍ ለመተርጎም በዋነኝነት ያገለገለው በዌስትኮትና ሆርት የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ዚ ኦሪጅናል ግሪክ የተባለው መጽሐፍ ነው። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለመተርጎም በዋነኝነት ያገለገለው ደግሞ በሩዶልፍ ኪትል የተዘጋጀው ቢብሊያ ሂብራይካ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በ2013 ታርሞ የወጣው መጽሐፍ ቅዱስ ሲዘጋጅ በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. እንደተዘጋጁ የሚታመኑ ሌሎች ቀደምት የፓፒረስ ጽሑፎች ጥቅም ላይ ውለዋል። ከዚህም ሌላ በኔልሰንና አላንድ እንዲሁም በተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት እንደተዘጋጁት ያሉትን በቅርቡ የተደረሰባቸውን ጥናታዊ ግኝቶች ያካተቱ ቅጂዎችን ለማመሳከር ጥረት ተደርጓል።
^ አን.30 ለመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረት ሆነው የሚያገለግሉ መመሪያዎችንና የአማርኛው ትርጉም ያሉትን ገጽታዎች በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት አዲስ ዓለም ትርጉም በተጨማሪ መረጃው ሀ1 እና ሀ2 ላይ የያዘውን ሐሳብ ተመልከት።