የሕይወት ታሪክ
ለሰባት ትውልዶች ሲተላለፍ የቆየ ውርስ
ሰዎች በብዙ ነገር አባቴን እንደምመስል ይናገራሉ። የሰውነት አቋሜ፣ ዓይኔና ተጫዋችነቴ ከአባቴ ጋር ያመሳስለኛል። ይሁን እንጂ አባቴ ሌላም ነገር አውርሶኛል፤ ይህም በቤተሰቤ ውስጥ ለሰባት ተከታታይ ትውልዶች ሲተላለፍ የቆየ ውርስ ነው። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ላውጋችሁ።
ጥር 20, 1815 ቶማስ1 * ዊሊያምስ፣ ሆርንካስል፣ እንግሊዝ ውስጥ ተወለደ፤ ቶማስ በአባቴ የዘር ሐረግ ወደኋላ ስንቆጥር ሰባተኛው ነው። እናቱ እሱ ከተወለደ ከሁለት ዓመት በኋላ ስለሞተች እሱንም ሆነ ሁለት ወንድሞቹንና እህቱን ያሳደጋቸው አባታቸው ጆን ዊሊያምስ ነበር። ጆን፣ ቶማስን በአናጺነት ሙያ ያሠለጠነው ቢሆንም ቶማስ ግን የሚጓጓለት ሌላ ሙያ ነበር።
በዚያን ጊዜ ሃይማኖታዊ ተሃድሶ በመላዋ እንግሊዝ ተስፋፍቶ ነበር። ሰባኪ ጆን ዌስሊ ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ተገንጥሎ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትንና ወንጌላዊነትን የሚያበረታታውን የሜቶዲስቶች ማኅበር መሥርቶ ነበር። የዌስሊ ትምህርቶች እንደ ሰደድ እሳት የተዛመቱ ሲሆን የዊሊያምስ ቤተሰብም በእነዚህ ትምህርቶች ተማረከ። ቶማስ የዌስሊን እምነት የሚያስፋፋ ሰባኪ ሆነ፤ ወዲያውኑም በደቡብ ፓስፊክ ሚስዮናዊ ሆኖ ለማገልገል ራሱን በፈቃደኝነት አቀረበ። ሐምሌ 1840 እሱና ባለቤቱ ሜሪ፣2 በወቅቱ የሰው ሥጋ ይበሉ የነበሩ ሕዝቦች ወደሚኖሩባት በፊጂ ወደምትገኘው ላኬባ የተባለች በእሳተ ገሞራ የተፈጠረች ደሴት * ደረሱ።
የሰውን ሥጋ በሚበሉ ሰዎች መካከል መኖር
ቶማስና ሜሪ በፊጂ ባሳለፏቸው በመጀመሪያዎቹ ዓመታት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት አሳልፈዋል። እጅግ ኋላ ቀር በሆኑ ሁኔታዎችና በኃይለኛ ሙቀት ውስጥ ለረጅም ሰዓት የጉልበት ሥራ ይሠሩ ነበር። በተጨማሪም በቃላት ሊገለጹ የማይችሉ አስፈሪ ሁኔታዎችን ይመለከቱ ነበር፤ የጎሳ ጦርነቶች፣ መበለቶችን ማነቅ፣ ሕፃናትን መግደልና የሰው ሥጋ መብላት የተለመዱ ነገሮች ነበሩ፤ የአካባቢው ሕዝብም በጥቅሉ ሲታይ መልእክታቸውን ይቃወም ነበር። ሜሪና የበኩር ልጇ ጆን በጠና በመታመማቸው ሊሞቱ ተቃርበው ነበር። በ1843 ቶማስ “በጣም ተጨንቄ ነበር። . . . ተስፋ ቆረጥኩ” በማለት ጽፎ ነበር። ሆኖም እሱና ሜሪ በጽናት የቀጠሉ ሲሆን በይሖዋ አምላክ ላይ ያላቸው እምነት ኃይል ሰጥቷቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቶማስ የአናጺነት ሙያ ስለነበረው በፊጂ የመጀመሪያው የሆነውን እንደ አውሮፓውያን ያለ ቤት ሠራ። ይህ ቤት ከመሬት ከፍ ብሎ የተሠራ መሆኑ ቤቱ ቀዝቀዝ እንዲል አድርጎታል፤ ይህም ሆነ ሌሎቹ የፈጠራ ሥራዎቹ የፊጂ ተወላጆች የሆኑትን የአካባቢውን ሕዝቦች የማወቅ ጉጉት ቀስቅሶ ነበር። ቤቱ ተሠርቶ ሊጠናቀቅ ትንሽ ሲቀረው ሜሪ ሁለተኛውን ወንድ ልጇን ቶማስ ዊተን3 ዊሊያምስን ወለደች።
በ1843 ትልቁ ቶማስ የዮሐንስ ወንጌልን ወደ ፊጂኛ ቋንቋ በመተርጎሙ ሥራ የተካፈለ ሲሆን ይህም ተፈታታኝ ሆኖበት ነበር። * ይሁን እንጂ ስለ ሰው ልጅ አኗኗርና ባሕል ጥሩ እውቀት ስለነበረው ነገሮችን በጥልቀት የማጤን ችሎታ ነበረው። ፊጂ ኤንድ ዘ ፊጂያንስ (1858) በተሰኘው መጽሐፉ ላይ በ19ኛው መቶ ዘመን ስለነበረው የፊጂያውያን አኗኗር የሚገልጽ ልዩ ዘገባ አዘጋጅቶ የምርምር ውጤቱን በጥንቃቄ አስፍሯል።
ቶማስ በፊጂ ያሳለፋቸው 13 ዓመታት በመከራ የተሞሉ ስለነበሩ በመጨረሻ ጤንነቱ እየተቃወሰ መጣ፤ በመሆኑም እሱና ቤተሰቡ ወደ አውስትራሊያ ተዛወሩ። ቶማስ ለረጅም ዓመታት ቄስ ሆኖ ሲያገለግል ከኖረ በኋላ በ1891 ቪክቶሪያ ውስጥ በባላራት ከተማ ሞተ።
በምዕራብ የተገኘ “ወርቅ”
በ1883 ቶማስ ዊተን ዊሊያምስና ባለቤቱ ፊቢ4 ቤተሰባቸውን ይዘው በምዕራብ አውስትራሊያ ወደምትገኘው ወደ ፐርዝ ሄዱ። ሁለተኛው ልጃቸው አርተር ቤክዌል5 ዊሊያምስ በዚያን ጊዜ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነበር።
አርተር 22 ዓመት ሲሆነው ከፐርዝ በስተ ምሥራቅ 600 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘውና የወርቅ ማዕድን በብዛት በሚገኝባት በካልጉሊ ከተማ ሀብት ፍለጋ ሄደ። በዚያም ሳለ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስያሜ ነበር) ያዘጋጇቸውን አንዳንድ ጽሑፎች አነበበ። በተጨማሪም የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ኮንትራት ገባ። አርተር ባነበበው ነገር ስለተመሰጠ ያገኘውን እውቀት ለሌሎች ማካፈልና መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠናባቸውን ስብሰባዎች ማዘጋጀት ጀመረ። በምዕራብ አውስትራሊያ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር።
በተጨማሪም አርተር ያገኘውን እውቀት ለቤተሰቡ መንገር ጀመረ። አባቱ ቶማስ ዊተን፣ አርተር ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር የነበረውን ግንኙነት ይደግፍ የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ሞተ። እናቱ ፊቢ እንዲሁም እህቶቹ ቫዮሌት እና ሜሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሆኑ። በኋላም ቫዮሌት የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ወይም አቅኚ ሆነች። አርተር ስለ ቫዮሌት ሲናገር “ምዕራብ አውስትራሊያ ካፈራቻቸው አቅኚዎች መካከል ምርጥ፣ እጅግ ቀናተኛና ጽኑ አቅኚ ነበረች” ብሏል። አርተር ይህን የተናገረው ምናልባት ለእህቱ አድልቶ ሊሆን ቢችልም የቫዮሌት የቅንዓት ምሳሌ ግን በቀጣዮቹ የዊሊያምስ ትውልዶች ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል።
ከጊዜ በኋላ አርተር ትዳር መሥርቶ በደቡባዊ ምዕራብ አውስትራሊያ ወደምትገኘውና የፍራፍሬ ከተማ ወደሆነችው ወደ ዶኒብሩክ ተዛወረ። እዚያም “አረጋዊው እብድ 1914!” የሚል ቅጽል ስም የወጣለት ሲሆን ይህን ስያሜ ያተረፈው 1914ን አስመልክቶ የተነገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በቅንዓት ያውጅ ስለነበረ ነው። * አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ ግን ይሰነዘርበት የነበረው ፌዝ አቆመ። አርተር በሱቁ ውስጥ አዘውትሮ ለደንበኞቹ ይመሠክር ነበር፤ በዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን መስኮቱ ላይ ያስቀምጥ ነበር። መስኮቱ ላይ አርተር፣ አጥብቆ ይቃወመው የነበረውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የሌለውን የሥላሴ ትምህርት ሊያስረዳው ለሚችል ሰው 100 ፓውንድ እንደሚሰጥ የሚናገር ማስታወቂያም ተለጥፎ ነበር። ይህ መሠረተ ትምህርት እውነት መሆኑን ሊያረጋግጥለት የቻለና ገንዘቡን የወሰደ ማንም አልነበረም።
የነዊሊያም ቤት በዶኒብሩክ ውስጥ የቡድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የጉባኤ ስብሰባዎች የሚደረጉበት ቦታ ሆነ። በኋላም አርተር በምዕራብ አውስትራሊያ በመጀመሪያ ከተገነቡት የመንግሥት
አዳራሾች ወይም የመሰብሰቢያ ቦታዎች አንዱን በከተማው ውስጥ ሠራ። አርተር በ70ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለ ሙሉ ልብስ ከነከረባቱ በመልበስ ዶል ተብሎ በሚጠራው ፈረሱ ላይ ተቀምጦ በመላው የዶኒብሩክ አውራጃ ይሰብክ ነበር።አርተር ዝምተኛና ጭምት ቢሆንም ቀናተኛ ሰባኪ መሆኑ በልጆቹ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ፍሎረንስ6 የምትባለው ሴት ልጁ ሕንድ ውስጥ ሚስዮናዊ ሆና አገልግላለች። ወንዶች ልጆቹ አርተር ሊንድሴይ7 እና ቶማስ እንደ አባታቸው ለብዙ ዓመታት የጉባኤ ሽማግሌ ሆነው አገልግለዋል።
ስዊት ሌዲ ዊሊያምስ
ቅድመ አያቴ አርተር ሊንድሴይ ዊሊያምስ በደግነት ባሕርይው የሚታወቅና የሚወደድ ሰው ነበር። ምንጊዜም ለሰዎች ጊዜ ይሰጥና በአክብሮት ይይዛቸው ነበር። በተጨማሪም በ12 ዓመታት ውስጥ በአካባቢው በተደረጉ የእንጨት ፈለጣ ውድድሮች 18 ጊዜ በአሸናፊነት ተሸልሞ ነበር።
አርተር የሁለት ዓመት ልጁ ሮናልድ8 (አያቴ) ደጃፋቸው ላይ የሚገኘውን አንድ ትንሽ የፖም ዛፍ በመጥረቢያ ሲመታ ሲያየው ተገርሞ ነበር። በዚህ ጊዜ የሮናልድ እናት የዛፉን ግንድ በጥንቃቄ አሰረችው፤ ዛፉ ከጊዜ በኋላ የተለየ ጣፋጭነት ያላቸውን ፍሬዎች ማፍራት ጀመረ። ሌዲ ዊሊያምስ ፖም ተብሎ የተሰየመው ይህ ፍሬ በዓለም ላይ በጣም ተወዳጅ ለሆነው ሮዝ ቀለም ያለው የክሪፕስ ፖም ዝርያ መገኛ ሆኗል።
ግራምፕ ብዬ የምጠራው ሮናልድ በኋላ ላይ ወደ ግንባታ ሙያ እያዘነበለ መጣ። እሱና ሴት አያቴ በአውስትራሊያና በሰለሞን ደሴቶች በተካሄዱት የይሖዋ ምሥክሮች የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ለብዙ ዓመታት በፈቃደኝነት አገልግለዋል። አሁን ዕድሜው ወደ 80 ዓመት የተጠጋው አያቴ እስካሁንም ድረስ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ሲሆን በምዕራብ አውስትራሊያ የመንግሥት አዳራሾችን በመገንባቱና በማደሱ ሥራ ይካፈላል።
ውርሻዬን ማድነቅ
ወላጆቼ ጄፍሪ9 እና ጃኒስ10 ዊሊያምስ ከቤተሰባችን ያገኘነውን ውርስ በማድነቅ እኔንና12 እህቴን ካትሪንን11 ክርስቲያናዊ መመሪያዎችን ከፍ አድርገን የምንመለከት እንድንሆን አድርገው አሳድገውናል። የ13 ዓመት ልጅ ሳለሁ የያዝኩት ነገር እውነት መሆኑን ተረዳሁ። በአንድ ትልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ በተገኘሁበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጆን ባር በተሰብሳቢው መካከል የነበርነውን ወጣቶች “ያላችሁን እጅግ ውድ ነገር ይኸውም ይሖዋን የማወቅና የመውደድ አጋጣሚያችሁን ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱት” በማለት አሳሰበን። የዚያን ቀን ምሽት ሕይወቴን ለይሖዋ ወሰንኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ አቅኚ ሆንኩ።
በአሁኑ ጊዜ እኔ እና ባለቤቴ ክሎ በምዕራብ አውስትራሊያ ርቃ በምትገኘው ቶም ፕራይስ የምትባል የማዕድን ማውጫ ከተማ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈልን ነው። ለኑሮ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማግኘት የተወሰነ ሰዓት እንሠራለን። ወላጆቼና እህቴ ካተሪን እንዲሁም ባለቤቷ አንድሩ በስተ ሰሜን 420 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው በፖርት ሄድላንድ በአቅኚነት እያገለገሉ ነው። እኔና አባቴ የጉባኤ ሽማግሌ ሆነን እናገለግላለን።
በአባቴ የዘር ሐረግ ወደኋላ ስንቆጥር ሰባተኛ የሆነው ቶማስ ዊሊያምስ ይሖዋ አምላክን ለማገልገል ቆርጦ ተነስቶ ነበር። ቤተሰቡ የነበረውን እምነትና የአገልግሎት ቅንዓት እኔም ወርሻለሁ። ይህን የመሰለ ውድ መንፈሳዊ ውርስ በማግኘቴ በጣም እንደተባረክሁ ይሰማኛል።
^ በግለሰቡ ስም ላይ ያለው ይህ ቁጥር በፎቶግራፎቹ ላይ ያለውን ግለሰብ የሚያመለክት ነው።
^ ቀደም ሲል ላኬምባ ደሴት ተብላ ትጠራ የነበረ ሲሆን በፊጂ ምሥራቃዊ ላኦ ደሴቶች ውስጥ ትገኛለች።
^ ሚስዮናዊው ጆን ሀንት በ1847 የታተመውን የፊጂኛ አዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ አብዛኛውን ክፍል ተርጉሟል። ይህ ትርጉም “ጂኦቫ” የሚለውን መለኮታዊ ስም የተጠቀመ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።
^ በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ላይ “1914—በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው ዓመት” የሚለውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት። መጽሐፉ www.pr418.com/am ላይም ይገኛል።