የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የይሖዋ ምሥክሮች እነማን ናቸው?
የምንሰብከው ለምንድን ነው?
ከቤት ወደ ቤት፣ በአደባባይና ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ የምናከናውነው ሰፊ የስብከት ሥራ በዋነኝነት ተለይተን የምንታወቅበት ተግባር ነው። የምንሰብከው ለምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩት አምላክ እንዲከበርና ስሙ እንዲታወቅ ስለሚፈልጉ ነው። (ዕብራውያን 13:15) በተጨማሪም ክርስቶስ ኢየሱስ ‘ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ያዘዝኳችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ በማለት የሰጠውን ትእዛዝ ማክበር ስለምንፈልግ ነው።—ማቴዎስ 28:19, 20
ከዚህም ሌላ ሰዎችን ሁሉ እንወዳለን። (ማቴዎስ 22:39) እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ ሰዎች የራሳቸው እምነት እንዳላቸውና መልእክታችንን መስማት የሚፈልገው ሁሉም ሰው እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ያም ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሕይወት እንደሚያስገኝ እናምናለን። ከዚህም የተነሳ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች እንዳደረጉት ሁሉ ‘ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ምሥራች ያለማሰለስ ማስተማራችንንና ማወጃችንን’ እንቀጥላለን።—የሐዋርያት ሥራ 5:41, 42
የሥነ ኅብረተሰብ ጥናት ባለሙያ የሆኑት አንቶኒዮ ኮቫ ማዱሮ “የይሖዋ ምሥክሮች በብዙ ጥረትና ልፋት፣ ጉልበታቸውን ምንም ሳይቆጥቡ . . . የቅዱስ ጽሑፉን መልእክት እስከ ምድር ዳር ድረስ አዳርሰዋል” በማለት ጽፈዋል።—ኤል ኡኒቨርሳል ጋዜጣ፣ ቬንዙዌላ
ጽሑፎቻችንን የሚያነቡ አብዛኞቹ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች አይደሉም። እንዲሁም ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ናቸው። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታቸው መጥተው ስለሚያነጋግሯቸው አመስጋኞች ናቸው።
እርግጥ፣ የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ሌሎች ጥያቄዎችም ሊኖሩህ ይችላሉ። ከሆነ በሚከተሉት መንገዶች መልሶቹን ማግኘት ትችላለህ፦
-
የይሖዋ ምሥክሮችን በመጠየቅ።
-
www.pr418.com ድረ ገጻችንን በመጎብኘት።
-
ክፍያ በማይጠየቅባቸውና ለሁሉም ሰው ክፍት በሆኑት ስብሰባዎቻችን ላይ በመገኘት።