በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

አሁን ሌሎችን መርዳት እንደምችል ይሰማኛል

አሁን ሌሎችን መርዳት እንደምችል ይሰማኛል
  • የትውልድ ዘመን፦ 1981

  • የትውልድ አገር፦ ጓቲማላ

  • የኋላ ታሪክ፦ አሳዛኝ የልጅነት ሕይወት

የቀድሞ ሕይወቴ፦

የተወለድኩት በጓቲማላ ምዕራባዊ ክፍል በሚገኘው ተራራማ አካባቢ ባለችው አኩል የምትባል ገለልተኛ ከተማ ውስጥ ነው። ቤተሰቦቼ የማያ ዘር የሆኑ ኢሲል የሚባል ጎሣ አባላት ናቸው። ከስፓንኛ ቋንቋ በተጨማሪ በተወለድኩበት አካባቢ የሚነገረውን ቋንቋ ከልጅነቴ ጀምሮ እናገራለሁ። የልጅነት ዕድሜዬን ያሳለፍኩት በጓቲማላ ለ36 ዓመታት የዘለቀው አሰቃቂ የእርስ በርስ ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ነው። በዚያ ወቅት ብዙ የኢሲል ጎሣ አባላት አልቀዋል።

የአራት ዓመት ልጅ ሳለሁ፣ ሰባት ዓመት የሆነው ታላቅ ወንድሜ በእጅ ቦምብ እየተጫወተ ሳለ ድንገት ፈነዳበት። በአደጋው ሳቢያ እኔ የማየት ችሎታዬን ያጣሁ ሲሆን ወንድሜ ደግሞ ሕይወቱን ማጣቱ እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነበር። ከዚያ በኋላ የልጅነት ሕይወቴን ያሳለፍኩት በጓቲማላ ሲቲ ዓይነ ስውራን ለሆኑ ልጆች በተዘጋጀ ተቋም ውስጥ ነው፤ በዚያም ብሬል ማንበብ ተማርኩ። እዚያም ሠራተኞቹ እኔ ፈጽሞ በማላውቀው ምክንያት ከሌሎች ልጆች ጋር እንዳላወራ ከለከሉኝ፤ አብረውኝ የሚማሩት ልጆች ደግሞ ይሸሹኝ ነበር። ሁልጊዜ ብቸኛ የነበርኩ ሲሆን በየዓመቱ ለሁለት ወር ቤት ሄጄ ከእናቴ ጋር የማሳልፈው ጊዜ ይናፍቀኛል፤ እሷ ምንጊዜም ደግነትና ርኅራኄ ታሳየኝ ነበር። የሚያሳዝነው፣ የአሥር ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ ሞተች። በዚህ ዓለም ላይ ያለ እሷ የሚወደኝ ሰው እንደሌለ አስብ ስለነበር እሷን ማጣቴ በእጅጉ ጎዳኝ።

በ11 ዓመቴ ወደተወለድኩበት ከተማ ተመልሼ በአባት ከምንገናኘው ከታላቅ ወንድሜና ከቤተሰቡ ጋር መኖር ጀመርኩ። እነሱ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ያሟሉልኝ ቢሆንም ስሜታዊ ድጋፍ ሊሰጠኝ የቻለ ሰው ግን አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ “እናቴ ለምን ሞተች? እኔስ ለምን ዓይነ ስውር ሆንኩ?” ብዬ ወደ አምላክ እጮኽ ነበር። ሰዎች እነዚህ አሳዛኝ ነገሮች የደረሱብኝ በአምላክ ፈቃድ እንደሆነ ይነግሩኝ ነበር። እኔም አምላክ ጨካኝና ኢፍትሐዊ ነው ብዬ ደመደምኩ። ሕይወቴን ያላጠፋሁበት ብቸኛው ምክንያት ራሴን የምገድልበት መንገድ ስላልነበረ ነው።

ዓይነ ስውር መሆኔ ለአካላዊም ሆነ ለስሜታዊ ጥቃት አጋልጦኛል። ልጅ ሳለሁ በተደጋጋሚ ጊዜ በፆታ የመነወር ጥቃት ደርሶብኛል። ለእኔ ግድ የሚሰጠው ሰው ይኖራል ብዬ ስላላሰብኩ የተፈጸመብኝን በደል ለሰው ተናግሬ አላውቅም። በወቅቱ የሚያናግረኝ ሰው የለም ቢባል ይቀልላል፤ እኔም ብሆን ከማንም ጋር አላወራም ነበር። ራሴን ከሰው አገል የነበረ ሲሆን የመንፈስ ጭንቀትም ነበረብኝ፤ ደግሞም ሰውን ማመን ይከብደኝ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ሳለሁ በትምህርት ቤት የእረፍት ሰዓት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች (ባልና ሚስት) ሊያነጋግሩኝ መጡ። በትምህርት ቤቱ የምታስተምር አንዲት መምህር የእኔ ሁኔታ ስለሚያሳዝናት መጥተው እንዲጠይቁኝ ነግራቸው ነበር። ባልና ሚስቱ ሙታን እንደሚነሱና ዓይነ ስውራን የሚያዩበት ቀን እንደሚመጣ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ነገሩኝ። (ኢሳይያስ 35:5፤ ዮሐንስ 5:28, 29) ሐሳቡን ወደድኩት፤ ነገር ግን ማውራት ከተውኩ ብዙ ጊዜ ስለሆነኝ ከእነሱ ጋር መነጋገር ተቸገርኩ። ይሁን እንጂ ከሌሎች ራሴን የማገል ብሆንም ባልና ሚስቱ ደግነትና ትዕግሥት ያሳዩኝ ከመሆኑ ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር እኔ ጋ መምጣታቸውን ቀጠሉ። እነዚህ ባልና ሚስት እኔ ወደምኖርበት ከተማ የሚመጡት ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘውና ተራራ አቋርጠው ነበር።

ታላቅ ወንድሜ፣ ባልና ሚስቱ ልብሳቸው ንጹሕ እንደሆነና ኑሯቸው ግን ዝቅተኛ እንደሚመስል ነገረኝ። ሆኖም ምንጊዜም አሳቢነት ያሳዩኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ አነስ ያሉ ስጦታዎችን ያመጡልኝ ነበር። እንዲህ ዓይነት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚያሳዩት እውነተኛ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው ብዬ ደመደምኩ።

በብሬል በተዘጋጁ ጽሑፎች አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ አጠናሁ። የምማረውን ነገር መረዳት ብችልም በውስጤ ግን አንዳንድ ነገሮችን መቀበል ከበደኝ። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ለእኔ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልኝና ሌሎች ሰዎችም አምላክ ለእኔ ያለው ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚችል ለማመን ተቸግሬ ነበር። ይሖዋ ለጊዜው ክፋትን የፈቀደው ለምን እንደሆነ ቢገባኝም እሱን እንደ አንድ አፍቃሪ አባት ማየት ግን ተሳነኝ። *

ይሁንና ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርኩት ነገር ቀስ በቀስ አመለካከቴን እንድለውጥ አስቻለኝ። ለምሳሌ፣ አምላክ መከራ ለሚደርስባቸው ሰዎች ከልብ እንደሚያዝን ተገነዘብኩ። አምላክ ግፍ ይደርስባቸው የነበረ አገልጋዮቹን በተመለከተ “የሕዝቤን መከራ በእርግጥ አይቻለሁ፤ . . . እየደረሰባቸው ያለውንም ሥቃይ በሚገባ አውቃለሁ” ብሏል። (ዘፀአት 3:7) ተወዳጅ የሆኑትን የይሖዋን ባሕርያት መገንዘብ ስጀምር ሕይወቴን ለእሱ ለመወሰን ተነሳሳሁ። ከዚያም በ1998 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

የምኖረው ከዚህ ወንድም ቤተሰብ ጋር ነው

ከተጠመቅሁ ከአንድ ዓመት በኋላ በኤስክዊንትላ ከተማ አቅራቢያ ለዓይነ ስውራን የተዘጋጀ አንድ ሥልጠና ወሰድኩ። አንድ የጉባኤያችን ሽማግሌ ከምኖርበት ከተማ ወደ ስብሰባ ለመሄድ በጣም እንደምቸገር ተገነዘበ። ለእኔ ቅርብ የሆነው ጉባኤ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሊያስጠኑኝ ይመጡ የነበሩት ባልና ሚስት ከሚያቋርጡት የተራራ ሰንሰለት ማዶ በመሆኑ ጉዞው አስቸጋሪ ነበር። ይህ ሽማግሌ እኔን ለመርዳት ሲል ኤስክዊንትላ ውስጥ አብሬአቸው እንድኖር ፈቃደኛ የሆኑ አንድ የቤተሰብ አባላት አፈላልጎ አገኘልኝ፤ ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች የሚወስዱኝም እነሱ ናቸው። እስከ ዛሬም ድረስ እንደ ቤተሰባቸው ቆጥረው ይንከባከቡኛል።

የጉባኤው አባላት ለእኔ እውነተኛ ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳዩ ብዙ ነገሮችን መጥቀስ እችላለሁ። እነዚህ ተሞክሮዎች የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን የእውነተኛ ክርስቲያኖች አባል እንደሆንኩ እንዳምን አድርገውኛል።—ዮሐንስ 13:34, 35

ያገኘሁት ጥቅም፦

በአሁኑ ጊዜ፣ የማልረባና ተስፋ ቢስ እንደሆንኩ አይሰማኝም። እንዲያውም ሕይወቴ ዓላማ አለው። የይሖዋ ምሥክሮች በሚያካሂዱት መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ በሙሉ ጊዜ ስለምካፈል ትኩረት የማደርገው የአካል ጉዳተኛ በመሆኔ ላይ ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስን ውድ እውነቶች ለሌሎች በማስተማር ላይ ነው። በተጨማሪም የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የማገልገልና በአካባቢው ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሕዝብ ንግግር የመስጠት መብት አግኝቻለሁ። አልፎ ተርፎም በሺዎች የሚቆጠሩ ተሰብሳቢዎች በሚገኙባቸው የክልል ስብሰባዎች ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን አቀርባለሁ።

የብሬል መጽሐፍ ቅዱሴን ተጠቅሜ ንግግር ሳቀርብ

በ2010፣ በኤል ሳልቫዶር ከተካሄደው የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት (አሁን የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተብሎ ከሚጠራው) ተመረቅሁ። ይህ ትምህርት ቤት በጉባኤ ውስጥ ያሉኝን ኃላፊነቶች ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ መወጣት እንድችል አስታጥቆኛል። ይህን ሥልጠና ማግኘቴ፣ ማንኛውንም ሰው ለሥራው ብቁ ማድረግ በሚችለው በይሖዋ አምላክ ዘንድ እጅግ ተፈላጊና ተወዳጅ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርጓል።

ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) በአሁኑ ወቅት ደስተኛ እንደሆንኩ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፤ አሁን ሌሎችን መርዳት እንደምችል ይሰማኛል። ይሁንና ቀደም ሲል እንዲህ አደርጋለሁ ብዬ አስቤ እንኳ አላውቅም።

^ አን.13 አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።