በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ትችላለህ

ሁሉም ሰው ሊረዳው የሚገባ መጽሐፍ

ሁሉም ሰው ሊረዳው የሚገባ መጽሐፍ

መጽሐፍ ቅዱስ ዕድሜ ጠገብ መጽሐፍ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። ለመሆኑ ምን ያህል ዘመን አስቆጥሯል? መጽሐፍ ቅዱስን መጻፍ የተጀመረው ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ ነበር። ይህም ማለት በቻይና ኃያሉ የሻንግ ሥርወ መንግሥት ይገዛ በነበረበት ዘመን እንዲሁም በሕንድ የቡድሃ ሃይማኖት ከመቋቋሙ ከአሥር መቶ ዓመታት ገደማ በፊት መሆኑ ነው።—“ መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከቱ መረጃዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ለሚነሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል

አንድ መጽሐፍ ለሰዎች ሕይወት የሚጠቅምና መመሪያ የያዘ እንዲሆን ከተፈለገ ሊረዱት የሚችሉትና እነሱን የሚመለከት ሊሆን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ ነው። በሕይወታችን ውስጥ ለሚነሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።

ለምሳሌ ያህል ‘የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ አሳስቦህ ያውቃል? ይህ ጥያቄ የሰው ልጆችን ለበርካታ ሺህ ዓመታት ግራ ሲያጋባ ቆይቷል፤ ዛሬም እውነታው ይኸው ነው። ሆኖም የዚህ ጥያቄ መልስ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ክፍል በሆነው በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ እና ሁለት ላይ ይገኛል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዓመታት ወደኋላ መልሶን የከዋክብት ረጨቶችን፣ ከዋክብትንና ምድርን የያዘው ግዑዙ ጽንፈ ዓለም እንዴት ወደ ሕልውና እንደመጣ ይገልጽልናል። (ዘፍጥረት 1:1) ከዚያም ምድር ለሰው ልጆች መኖሪያነት እንዴት ምቹ እንደተደረገች፣ ሕይወት ያላቸው የተለያዩ ነገሮች እንዴት ወደ ሕልውና እንደመጡ፣ ሰዎች እንዴት እንደተፈጠሩ እንዲሁም እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተፈጠሩበት ዓላማ ምን እንደሆነ ደረጃ በደረጃ ይገልጻል።

ሰዎች ሊረዱት በሚችል መንገድ የተጻፈ

መጽሐፍ ቅዱስ በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንድንወጣ የሚያስችል ተግባራዊ ምክር ይዟል። ምክሩ ደግሞ ለመረዳት አያዳግትም። ይህንን ከሁለት አቅጣጫ ማየት እንችላለን።

በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ግልጽ፣ ቀጥተኛ እና ማራኪ በሆነ መንገድ ነው። ለመረዳት የሚከብዱ ወይም ሚስጥራዊ የሆኑ አገላለጾችን ብዙ ቦታዎች ላይ አናገኝም፤ ከዚህ ይልቅ ተጨባጭ የሆኑና ሊገቡን የሚችሉ መግለጫዎችን ይጠቀማል። ለመረዳት አስቸጋሪ የሆኑት ሐሳቦች እንኳ የተገለጹት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በምንጠቀምባቸው ቃላት ነው።

ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ የሰዎችን ልብ በሚነካ መንገድ ለማስተማር በየዕለቱ በሚያዩአቸው ነገሮች ላይ የተመሠረቱ በርካታ ቀላል ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ፣ በተለምዶ የተራራው ስብከት ተብሎ በሚጠራው ላይ የተጠቀሱ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 ላይ ተመዝግበው ይገኛሉ። አንድ ተንታኝ ይህን ስብከት “ጠቃሚ ሐሳቦችን የያዘ ንግግር” በማለት የገለጸ ከመሆኑም ሌላ ዓላማውን በተመለከተ ያስተዋለውን ሲናገር “ጭንቅላታችንን በእውቀት መሙላት ሳይሆን ድርጊታችንን መምራትና መቆጣጠር ነው” ብሏል። እነዚህን ምዕራፎች በ15 ወይም በ20 ደቂቃ ውስጥ አንብበህ መጨረስ ትችላለህ፤ ደግሞም ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት ቀላል ሆኖም አሳማኝ በመሆኑ መገረምህ አይቀርም።

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ቀላል እንዲሆን የሚያደርገው ሌላው ነገር ደግሞ ይዘቱ ነው። የአፈ ታሪክ ወይም የተረት መጽሐፍ አይደለም። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በአብዛኛው “ስለ ታላላቅ ሰዎችም ሆነ ስለ ተራ ሰዎች” እንዲሁም “ስላሳለፉት ውጣ ውረድና ተስፋ ስላደረጉት ነገር ብሎም ስላጋጠማቸው ሽንፈትና ስለተቀዳጁት ድል” እንደሚገልጽ ዘግቧል። በእውን ስለነበሩ ስለ እነዚህ ሰዎችና ክንውኖች የሚገልጹትን ዘገባዎች ከራሳችን ሕይወት ጋር ማያያዝና በውስጣቸው የያዟቸውን ትምህርቶች መረዳት አይከብደንም።—ሮም 15:4

ሁሉም ሰው ሊያገኘው የሚችል

አንድን መጽሐፍ አንብበህ መረዳት እንድትችል በምታውቀው ቋንቋ መጻፍ ይኖርበታል። የምትኖረው የትም ሆነ የት ወይም ዜግነትህ ምንም ይሁን ምን በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን አንተ መረዳት በምትችለው ቋንቋ የማግኘት አጋጣሚ አለህ። ይህን ለማመን የሚያዳግት ክንውን ዳር ለማድረስ ምን ጥረት እንደጠየቀ ተመልከት።

ትርጉም። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተጻፈው በዕብራይስጥ፣ በአረማይክና በግሪክ ነው። ይህ በራሱ የአንባቢዎቹን ቁጥር እንደሚገድበው የታወቀ ነው። በመሆኑም በቅን ልቦና የተነሳሱ ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች ቋንቋዎችም እንዲገኝ ለማስቻል ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ላደረጉት ጥረት ምስጋና ይግባውና፣ በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉም ሆነ በከፊል በ2,700 ገደማ ቋንቋዎች ይገኛል። ይህ ሲባል ከዓለም ሕዝብ መካከል 90 ከመቶ በላይ የሚሆነው መጽሐፍ ቅዱስን በአፍ መፍቻ ቋንቋው ማንበብ ይችላል ማለት ነው።

ሕትመት። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተጻፈው እንደ ፓፒረስና ብራና ባሉ ሊበላሹ በሚችሉ ቁሶች ላይ ነበር። መልእክቱን በቀጣይነት ለማስተላለፍ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ደግሞ ደጋግሞ በእጅ መገልበጥ አስፈልጓል። የእነዚህ ቅጂዎች ዋጋ ውድ በመሆኑ ብዙ ሰዎች መግዛት አይችሉም ነበር። ሆኖም ጉተንበርግ ከ550 ዓመታት በፊት የሠራው የማተሚያ ማሽን መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው እንዲሰራጭ አስችሏል። አንድ ግምታዊ አኃዝ እንደሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉም ሆነ በከፊል ከአምስት ቢሊዮን በላይ በሚሆኑ ቅጂዎች ተሰራጭቷል።

በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስን ሊተካከል የሚችል ሌላ ሃይማኖታዊ ጽሑፍ የለም። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ሊረዱት የሚገባ መጽሐፍ ነው። ሆኖም መጽሐፉን መረዳት ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ይሁንና እርዳታ ማግኘት ትችላለህ። ግን ከየት? ጥቅም ማግኘት የምትችለውስ እንዴት ነው? ቀጣዩ ርዕስ መልሱን ይዟል።