በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ግብዝነት! ማብቂያ ይኖረው ይሆን?

ግብዝነት! ማብቂያ ይኖረው ይሆን?

ፓናዮታ ያደገችው በሜድትራንያን በሚገኝ አንድ ደሴት ላይ ነው። ወጣት ሳለች ለፖለቲካ ከፍተኛ ፍቅር ነበራት። ከጊዜ በኋላ በምትኖርበት መንደር ውስጥ ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ጸሐፊ ሆና ያገለገለች ሲሆን ለፓርቲው ከቤት ወደ ቤት እየሄደች ገንዘብ ታሰባስብ ነበር። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን ፓናዮታ ግራ መጋባት ጀመረች። የፓርቲው አባላት እርስ በእርሳቸው ጓድ እየተባባሉ ይጠራሩ የነበረ ቢሆንም በመካከላቸው መድሎ፣ የሥልጣን ጥም፣ አለመግባባትና ቅናት ተንሰራፍቶ ነበር።

ዳንኤል ያደገው አየርላንድ ውስጥ በሚኖር አጥባቂ ሃይማኖተኛ ቤተሰብ ውስጥ ነበር። የሚያሳዝነው ነገር፣ የሃይማኖቱ አስተማሪዎች ኃጢአት ከሠራ በእሳታማ ሲኦል እንደሚቃጠል ዘወትር እያስተማሩት እነሱ ግን በጣም ይጠጡ፣ ቁማር ይጫወቱና ከሙዳየ ምጽዋት ውስጥ ይሰርቁ ነበር፤ ይህ ግብዝነታቸው ፈጽሞ ከአእምሮው አልጠፋም።

ጄፍሪ መቀመጫውን በብሪታንያ እና በዩናይትድ ስቴትስ ባደረገ አንድ የመርከብ ባለቤቶች ዓለም አቀፍ ኩባንያ ውስጥ በገበያ ጥናትና በሽያጭ ሠራተኛነት አብዛኛውን ሕይወቱን አሳልፏል። ደንበኞችና ተፎካካሪዎች ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በሚደራደሩበት ጊዜ ከማጭበርበር ወደኋላ እንደማይሉ ብዙ ጊዜ ተመልክቷል። ውላቸው እንዲጸና ለማድረግ በግብዝነት የማይገቡት ቃል አልነበረም።

የሚያሳዝነው ነገር፣ ከግብዝነት ጋር በተያያዘ የሚጠቀሱት ሁኔታዎች እነዚህ ብቻ አይደሉም። በዛሬው ጊዜ ሰዎች በሚያደርጉት ማንኛውም እንቅስቃሴ ውስጥ ማለት ይቻላል ይኸውም በፖለቲካ፣ በሃይማኖትና በንግዱ ዓለም ግብዝነት ማየት የተለመደ ነው። “ግብዝ” ተብሎ የተተረጎመው የእንግሊዝኛ ቃል ከግሪክኛ ቃል የተገኘ ሲሆን ይህ ቃል አብዛኛውን ጊዜ ጭምብል አጥልቆ የሚናገርን ሰው ወይም የመድረክ ተዋናይን ያመለክታል። ከጊዜ በኋላ ቃሉ ሌሎችን ለማታለል ወይም የግል ጥቅሙን ለማሳካት አስመስሎ የሚያቀርብን ሰው ለማመልከት ይሠራበት ጀመር።

በግብዝነት የተነሳ የተጎዱ ሰዎች እንደ ምሬት፣ ብስጭት እና ቂም የመሳሰሉ ባሕርያት ይታዩባቸዋል። በዚህ የተጎዱ ሰዎች በምሬት “ግብዝነት! ማብቂያ ይኖረው ይሆን?” ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ። የሚያስደስተው ነገር፣ የአምላክ ቃል ይህ ይፈጸማል ብለን እንድናምን የሚያስችሉ ማስረጃዎች ይዟል።

አምላክና ልጁ ስለ ግብዝነት ያላቸው አመለካከት

መጽሐፍ ቅዱስ ግብዝነት የጀመረው በሰዎች መካከል ሳይሆን በማይታዩ መንፈሳዊ ፍጥረታት ዘንድ መሆኑን ይገልጻል። በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ ላይ ሰይጣን ዲያብሎስ የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን ለማታለል በእባብ የተጠቀመ ከመሆኑም ሌላ ለእሷ የተቆረቆረ መስሎ ቀርቧታል። (ዘፍጥረት 3:1-5) በተመሳሳይም ከዚያን ጊዜ አንስቶ ብዙ ሰዎች ያልሆኑትን መስለው መቅረብ የጀመሩ ሲሆን ይህንንም የሚያደርጉት ሌሎችን ለማታለልና የራስ ወዳድነት ፍላጎታቸውን ለማሳካት ነው።

የጥንቶቹ እስራኤላውያን በሐሰት አምልኮና በመንፈሳዊ ግብዝነት ወጥመድ ሲወድቁ አምላክ በተደጋጋሚ ጊዜ መዘዙን በመግለጽ አስጠንቅቋቸው ነበር። ይሖዋ አምላክ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ይህ ሕዝብ ወደ እኔ የሚቀርበው በአፉ ብቻ ነው፤ በከንፈሩም ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው።” (ኢሳይያስ 29:13) ብሔሩ ለመስተካከል ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ አምላክ፣ የጠላት ሠራዊት የእስራኤል የአምልኮ ማዕከል የሆኑትን ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን እንዲያጠፉ ፈቀደ፤ ይህም የሆነው በመጀመሪያ በ607 ዓ.ዓ. በባቢሎናውያን በመጨረሻም በ70 ዓ.ም. በሮማውያን ነበር። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አምላክ ግብዝነትን ዝም ብሎ አያይም።

በሌላ በኩል ደግሞ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ታማኝና ቅን የሆኑ ሰዎችን ከፍ አድርገው ይመለከታሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ አካባቢ ናትናኤል የሚባል ሰው ወደ እሱ ሲመጣ አይቶ “ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ ይኸውላችሁ!” አለ። (ዮሐንስ 1:47) በርቶሎሜዎስ ተብሎም የሚጠራው ናትናኤል ከጊዜ በኋላ ከኢየሱስ 12 ሐዋርያት አንዱ ሆኗል።—ሉቃስ 6:13-16

ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር ጊዜ ያሳልፍ ነበር፤ በዚህ ወቅት አምላክ ስለተለያዩ ነገሮች ያለውን አመለካከት አስተምሯቸዋል። በመሆኑም ተከታዮቹ የግብዝነት ባሕርይ ሊያሳዩ አይገባም። ኢየሱስ በወቅቱ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች የሚፈጽሟቸውን የግብዝነት ድርጊቶች በጥብቅ በማውገዝ ለተከታዮቹ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። እስቲ ያደርጓቸው የነበሩትን አንዳንድ ነገሮች እንመልከት።

‘የጽድቅ ሥራቸው’ የታይታ ነበር። ኢየሱስ አድማጮቹን “ሰዎች እንዲያዩላችሁ ብላችሁ የጽድቅ ሥራችሁን በእነሱ ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ . . . ግብዞች አትሁኑ” ብሏቸዋል። እንዲሁም ምጽዋት መስጠት ያለባቸው “በስውር” ወይም ሰው ሳያያቸው መሆን እንዳለበት ነግሯቸዋል። ጸሎት ማቅረብ ያለባቸው ሌሎች እንዲያዩአቸው ብለው ሳይሆን ለብቻቸው ሊሆን እንደሚገባ አስተምሯቸዋል። እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ አምልኳቸው ልባዊ ይሆናል፤ እንዲሁም በአባቱ ዘንድ ተቀባይነት ይኖራቸዋል።—ማቴዎስ 6:1-6

ሌሎችን ለመንቀፍ ፈጣን ነበሩ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አንተ ግብዝ! መጀመሪያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ።” (ማቴዎስ 7:5) አንድ ሰው እሱ የሚሠራው ስህተት ከባድ ሆኖ እያለ በሌሎች ስህተት ላይ ትኩረት በማድረግ ያልሆነውን ሆኖ ለመታየት ጥረት ሊያደርግ ይችላል። እውነታውን ስንመለከት ግን “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል።”—ሮም 3:23

መጥፎ የልብ ዝንባሌ ነበራቸው። በአንድ ወቅት የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርትና የሄሮድስ መንግሥት ደጋፊዎች ስለ ግብር ሊጠይቁት ኢየሱስ ጋር መጡ። ኢየሱስን ለመሸንገል በማሰብ “መምህር፣ አንተ እውነተኛ እንደሆንክና የአምላክን መንገድ በትክክል እንደምታስተምር . . . እናውቃለን” አሉት። ከዚያም “ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” የሚል ጥያቄ በማቅረብ ወጥመድ ውስጥ ሊያስገቡት ሞከሩ። ኢየሱስ ግን “እናንተ ግብዞች፣ ለምን ትፈትኑኛላችሁ?” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስ ጥያቄ ያቀረቡለት መልሱን ለማወቅ ብለው ሳይሆን “በንግግሩ ሊያጠምዱት” ፈልገው በመሆኑ እነሱን ግብዞች በማለት መጥራቱ ትክክል ነበር።—ማቴዎስ 22:15-22

እውነተኛ ክርስቲያኖች “ከንጹሕ ልብ፣ ከጥሩ ሕሊናና ግብዝነት ከሌለበት እምነት የሚመነጭ ፍቅር” ያሳያሉ።—1 ጢሞቴዎስ 1:5

በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ ዕለት የክርስቲያን ጉባኤ ሲመሠረት እውነትና ሐቀኝነት የሚስፋፋበት ምቹ ሁኔታ ተፈጠረ። እውነተኛ ክርስቲያኖች የግብዝነትን ባሕርይ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ልባዊ ጥረት ማድረግ ጠይቆባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮቹን “ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ” እንዲያሳዩ አበረታቷቸዋል። (1 ጴጥሮስ 1:22) ሐዋርያው ጳውሎስም የሥራ ባልደረቦቹ “ከንጹሕ ልብ፣ ከጥሩ ሕሊናና ግብዝነት ከሌለበት እምነት የሚመነጭ ፍቅር” እንዲያሳዩ አሳስቧቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 1:5

የአምላክ ቃል ያለው ኃይል

መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ኢየሱስና ሐዋርያት ያስተማሩት ትምህርት እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም ከፍተኛ ኃይል አለው። ይህን አስመልክቶ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን እንዲሁም መገጣጠሚያንና መቅኒን እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል፤ የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።” (ዕብራውያን 4:12) ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ማወቃቸውና ከዚያ ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረት ማድረጋቸው ከግብዝነት እንዲርቁ እንዲሁም ቅንነትና ሐቀኝነትን እንዲያሳዩ ረድቷቸዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ሦስት ሰዎች ተሞክሮ እንመልከት።

“ለሰዎች እውነተኛ ፍቅርና ልባዊ አሳቢነት እንደሚያሳዩ ተመልክቻለሁ።”—ፖናዮታ

ፖናዮታ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያካሂዱት ስብሰባ ላይ እንድትካፈል የቀረበላትን ግብዣ ተቀብላ በዚያ መገኘቷ በሕይወቷ ከፍተኛ ለውጥ እንድታደርግ አስችሏታል። በስብሰባው ላይ የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ ሲሉ ጻድቅ መስለው ለመታየት ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች አላየችም። እንዲህ ብላለች፦ “በዚያ፣ ለሰዎች እውነተኛ ፍቅርና ልባዊ አሳቢነት እንደሚያሳዩ ተመልክቻለሁ፤ በፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ አደርግ በነበረባቸው ዓመታት ሁሉ እንዲህ ያለ ነገር አይቼ አላውቅም።”

ከዚያም ፖናዮታ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረች ሲሆን እድገት አድርጋ ለመጠመቅ በቅታለች። ይህ የሆነው ከ30 ዓመት በፊት ነበር። አሁን እንዲህ ትላለች፦ “አባል ለነበርኩበት የፖለቲካ ፓርቲ ድጋፍ ለማሰባሰብ ከቤት ወደ ቤት እሄድ በነበረ ጊዜ ሕይወቴ ትርጉም አልነበረውም፤ ስለ አምላክ መንግሥት መስበክ በጀመርኩበት ጊዜ ግን ሕይወቴ ትርጉም ያለው ሆኗል። ደግሞም ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም ማምጣት የሚችለው ይህ መንግሥት ብቻ ነው።”

“በእምነት አጋሮቼ ፊት ያልሆንኩትን መስዬ መታየት አልፈለግኩም።”—ዳንኤል

ዳንኤል በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ጥሩ እድገት በማድረጉ አንዳንድ መንፈሳዊ ኃላፊነቶች ተሰጥተውት ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን አንድ ስህተት በመፈጸሙ ሕሊናውን ይወቅሰው ጀመር። ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “ከዓመታት በፊት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያየሁት ግብዝነት ከአእምሮዬ ስላልጠፋ የአገልግሎት መብቶቼን ከመተው ውጪ ሌላ ምርጫ እንደሌለኝ ተሰማኝ። በእምነት አጋሮቼ ፊት ያልሆንኩትን መስዬ መታየት አልፈለግኩም።”

ደስ የሚለው ነገር ዳንኤል ማስተካከያዎችን ካደረገ በኋላ ጥሩ ሕሊና ይዞ በአገልግሎት መብቶቹ መቀጠል እንደሚችል ተሰማው፤ በመሆኑም በጉባኤ ውስጥ በድጋሚ የተሰጡትን መብቶች በደስታ ተቀብሏል። እንዲህ ዓይነቱ አስደሳች የሐቀኝነት ባሕርይ አምላክን ያለ ግብዝነት የሚያገለግሉ ሰዎች የሚታወቁበት መለያ ነው። እነዚህ ሰዎች በወንድማቸው ዓይን ውስጥ ያለውን ‘ጉድፍ ከማውጣታቸው’ በፊት በራሳቸው ዓይን ውስጥ ያለውን ‘ግንድ ማውጣት’ እንዳለባቸው ተገንዝበዋል።

“በብልጣ ብልጥነት የሆነ ያልሆነውን የሚናገር የሽያጭ ሠራተኛ ሆኜ መቀጠል እንደማልችል ተገነዘብኩ። . . . የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጥሩ ሕሊና እንዲኖረኝ ረድተውኛል።”—ጄፍሪ

በንግዱ ዓለም ረጅም ዓመታት ያሳለፈው ጄፍሪ እንዲህ ብሏል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቴ እያደገ ሲመጣ አንድ ኮንትራት ለማሸነፍ ስል በብልጣ ብልጥነት የሆነ ያልሆነውን የሚናገር የሽያጭ ሠራተኛ ሆኜ መቀጠል እንደማልችል ተገነዘብኩ። እንደ ምሳሌ 11:1 ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጥሩ ሕሊና እንዲኖረኝ ረድተውኛል፤ ጥቅሱ ‘አባይ ሚዛን በይሖዋ ዘንድ አስጸያፊ ነው’ ይላል።” ለኢየሱስ ስለ ግብር ጥያቄ ካቀረቡለት ሰዎች በተቃራኒ ጄፍሪ ከእምነት ባልንጀሮቹም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት በቅንነት መመላለስ እንዳለበት ተገንዝቧል።

በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማሩትን ነገር በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ያደርጋሉ። “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና” ለመልበስ ብርቱ ጥረት እያደረጉ ነው። (ኤፌሶን 4:24) የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ፣ ምን ብለው እንደሚያምኑ እንዲሁም አምላክ ቃል ስለገባው አዲስ ዓለም እውቀት እንድታገኝ እንዴት ሊረዱህ እንደሚችሉ ለማወቅ ጥረት እንድታደርግ እናበረታታሃለን። በአዲሱ ዓለም ውስጥ “ጽድቅ ይሰፍናል”፤ ግብዝነት የሚባል ነገር ደግሞ አይኖርም።—2 ጴጥሮስ 3:13