የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የአራቱ ፈረሰኞች ግልቢያ—በሕይወትህ ላይ ለውጥ ያመጣል?
አራቱ ፈረሰኞች—እነማን ናቸው?
ስለ አራቱ ፈረሰኞች የሚናገረው ራእይ ሚስጥራዊና አስፈሪ ሊመስል ይችላል፤ እውነታው ግን እንደዚያ አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስና በዘመናችን የተፈጸሙ ክንውኖች እያንዳንዱ ፈረሰኛ ምን እንደሚያመለክት በግልጽ እንድንረዳ ያስችሉናል። በተጨማሪም የፈረሰኞቹ ግልቢያ በምድር ላይ መከራ እንደሚመጣ የሚጠቁም ቢሆንም ይህ ለአንተና ለቤተሰብህ ምሥራች ሊሆን ይችላል። እንዴት? በመጀመሪያ እያንዳንዱ ፈረሰኛ ምንን እንደሚወክል እንመልከት።
የነጩ ፈረስ ጋላቢ
ራእዩ እንዲህ በማለት ይጀምራል፦ “እኔም አየሁ፣ እነሆ ነጭ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደ ፊት ገሰገሰ።”—ራእይ 6:2
የነጩ ፈረስ ጋላቢ ማን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ከዚሁ ከራእይ መጽሐፍ ላይ ማግኘት እንችላለን፤ የራእይ መጽሐፍ በሌላ ጥቅስ ላይ ይህ ጋላቢ “የአምላክ ቃል” እንደሆነ ይናገራል። (ራእይ 19:11-13) ቃል የሚለው ማዕረግ የተሰጠው የአምላክ ቃል አቀባይ ሆኖ ለሚያገለግለው ለኢየሱስ ነው። (ዮሐንስ 1:1, 14) በተጨማሪም “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” እንዲሁም “ታማኝና እውነተኛ” ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 19:11, 16) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ተዋጊ ንጉሥ ነው፤ የተሰጠውን ሥልጣን ደግሞ ተገቢ ባልሆነ ወይም ጨቋኝ በሆነ መንገድ አይጠቀምበትም። ሆኖም ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
ኢየሱስ ድል እንዲያደርግ ሥልጣን የሰጠው ማን ነው? (ራእይ 6:2) ነቢዩ ዳንኤል “የሰው ልጅ የሚመስል” ተብሎ የተገለጸው መሲሕ ‘ከዘመናት በፊት የነበረው’ ከተባለው ከይሖዋ አምላክ * “የገዢነት ሥልጣን፣ ክብርና መንግሥት” ሲቀበል በራእይ ተመልክቷል። (ዳንኤል 7:13, 14) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው የመግዛትና ፍርድ የማስፈጸም ሥልጣንም ሆነ መብት ለኢየሱስ የሰጠው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አብዛኛውን ጊዜ ነጭ ቀለምን ጽድቅን ለማመልከት ይጠቀምበታል፤ በመሆኑም ነጩ ፈረስ የአምላክ ልጅ በጽድቅ የሚያከናውነውን ጦርነት የሚያመለክት ተስማሚ ምሳሌ ነው።—ራእይ 3:4፤ 7:9, 13, 14
ፈረሰኞቹ መጋለብ የጀመሩት መቼ ነው? የመጀመሪያው ጋላቢ ማለትም ኢየሱስ መጋለብ የጀመረው አክሊል ሲሰጠው መሆኑን ልብ በል። (ራእይ 6:2) ታዲያ ኢየሱስ በሰማይ ላይ ንጉሥ ሆኖ አክሊሉን የተቀበለው መቼ ነው? ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ባረገበት ወቅት ነው? አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ ሥልጣን እስኪሰጠው ድረስ የተወሰነ ጊዜ መጠበቅ አስፈልጎታል። (ዕብራውያን 10:12, 13) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ይህ ጊዜ ተጠናቆ በሰማይ ላይ መግዛት የሚጀምረው መቼ እንደሆነ የሚጠቁም ምልክት ሰጥቷቸዋል። መግዛት በሚጀምርበት ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ ሁኔታዎች መባባስ እንደሚጀምሩ ይኸውም ጦርነት፣ የምግብ እጥረት እንዲሁም ቸነፈር እንደሚከሰት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3, 7፤ ሉቃስ 21:10, 11) በ1914 አንደኛው የዓለም ጦርነት ከፈነዳ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ በማለት የሚጠራው በመከራ የተሞላ ጊዜ እንደጀመረ ግልጽ ሆነ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ታዲያ ኢየሱስ በ1914 አክሊል ከተሰጠው በኋላ ሁኔታዎች ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሱ የሄዱት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ በወቅቱ መግዛት የጀመረው በምድር ሳይሆን በሰማይ ላይ ነው። በዚያን ጊዜ በሰማይ ላይ ጦርነት ተነሳ፤ ሚካኤል ተብሎ የተጠራው አዲሱ ንጉሥ ኢየሱስ፣ ሰይጣንንና አጋንንቱን ወደ ምድር ወረወራቸው። (ራእይ 12:7-9, 12) ወደ ምድር የተጣለው ሰይጣን የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን ስላወቀ ከዚያ ጊዜ አንስቶ በታላቅ ቁጣ ተሞልቷል። አምላክ በቅርቡ በሰይጣን ላይ እርምጃ በመውሰድ በምድር ላይ ፈቃዱን ያስፈጽማል። (ማቴዎስ 6:10) አሁን ደግሞ ቀሪዎቹ ሦስት ፈረሰኞች፣ የምንኖረው በመከራ በተሞሉት ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ውስጥ እንደሆነ የሚያረጋግጡት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ኢየሱስን ከሚያመለክተው ከመጀመሪያው ፈረሰኛ በተለየ መልኩ ቀሪዎቹ ሦስት ፈረሰኞች በመላው የሰው ልጅ ማኅበረሰብ ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ሁኔታዎችን ያመለክታሉ።
የቀዩ ፈረስ ጋላቢ
“ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ሌላ ፈረስ ወጣ፤ በእሱም ላይ ለተቀመጠው ሰዎች እርስ በርሳቸው ይተራረዱ ዘንድ ሰላምን ከምድር እንዲወስድ ተፈቀደለት፤ እንዲሁም ትልቅ ሰይፍ ተሰጠው።”—ራእይ 6:4
ይህ ጋላቢ ጦርነትን ይወክላል። ጋላቢው ሰላምን የሚወስደው ከጥቂት አገሮች ላይ ብቻ ሳይሆን ከመላው ምድር እንደሆነ ልብ በል። በ1914 በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፋዊ ጦርነት ተከሰተ። ከዚያ በኋላ ደግሞ የከፋ ጥፋት ያስከተለ ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ተቀሰቀሰ። ከ1914 አንስቶ በተከሰቱ ጦርነቶችና ግጭቶች የተነሳ ከ100 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች እንደሞቱ ይገመታል! ሌሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በእርግጥም የምንኖርበት ዘመን ጦርነት የነገሠበት ነው። በታሪክ ውስጥ ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መልኩ የሰው ልጅ በምድር ላይ ያሉትን ሰብዓዊ ፍጡራን በሙሉ የማጥፋት አቅም አለው ሊባል ይችላል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የመሰሉ ሰላም አስከባሪ ነን የሚሉ ተቋማት እንኳ የቀዩን ፈረስ ጋላቢ ማስቆም አልቻሉም።
የጥቁሩ ፈረስ ጋላቢ
“እኔም አየሁ፣ እነሆ ጥቁር ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር። ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል እንደ ድምፅ ያለ ነገር ‘አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር፣ ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፤ ደግሞም የወይራ ዘይቱንና ወይኑን አትጉዳ’ ሲል ሰማሁ።”—ራእይ 6:5, 6
ይህ ጋላቢ ረሃብን ይወክላል። እዚህ ጥቅስ ላይ፣ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ከመከሰቱ የተነሳ አንድ እርቦ (0.7 ኪሎ) ስንዴ በአንድ ዲናር እንደሚሸጥ የተገለጸ ሲሆን በዚያ ዘመን ደግሞ አንድ ዲናር የአንድ ሰው የሙሉ ቀን ደሞዝ ነበር። (ማቴዎስ 20:2) ጥቅሱ ሦስት እርቦ (2.1 ኪሎ) ገብስም በአንድ ዲናር እንደሚሸጥ ይናገራል፤ በወቅቱ ገብስ ከስንዴ ዝቅ ተደርጎ ይታይ ነበር። ትልቅ ቤተሰብ ያለው ሰው በዚህ እህል ቤተሰቡን እንዴት መመገብ ይችላል? በመሆኑም ሰዎች የወይራ ዘይትና የወይን ጠጅን ጭምር መቆጠብ እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል፤ በወቅቱ በነበረው ባህል የወይራ ዘይትና የወይን ጠጅ ለዕለታዊ ቀለብነት የሚያገለግሉ መሠረታዊ ነገሮች ነበሩ።
ከ1914 አንስቶ የጥቁሩ ፈረስ ጋላቢ እየጋለበ እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ አለ? አዎ! በ20ኛው መቶ ዘመን 70 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ሞተዋል። አንድ ድርጅት እንደተናገረው “ከ2012 እስከ 2014 ባሉት ዓመታት ከዓለም ሕዝብ አንድ ዘጠነኛው ማለትም 805 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በቂ ምግብ አላገኙም።” አንድ ሌላ ሪፖርት ደግሞ “በየዓመቱ በረሃብ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር በኤድስ፣ በወባ በሽታና በሳንባ ነቀርሳ ከሚሞቱት ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር ይበልጣል” ሲል ገልጿል። የተራቡ ሰዎችን ለመመገብ ከፍተኛ ጥረት የሚደረግ ቢሆንም እንኳ የጥቁሩ ፈረስ ጋላቢ ግልቢያውን እንደቀጠለ ነው።
የግራጫው ፈረስ ጋላቢ
“እኔም አየሁ፣ እነሆ ግራጫ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበር። መቃብርም በቅርብ ይከተለው ነበር። ሞትና መቃብርም በረጅም ሰይፍ፣ በምግብ እጥረት፣ በገዳይ መቅሰፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።”—ራእይ 6:8
አራተኛው ጋላቢ በወረርሽኝና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ የሚከሰት ሞትን ይወክላል። ከ1914 በኋላ ብዙም ሳይቆይ የኅዳር በሽታ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድሏል። በወቅቱ በዓለም ላይ ከሚኖሩት ሰዎች አንድ ሦስተኛው ማለትም ወደ 500 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በኅዳር በሽታ ተይዘው እንደነበር ይገመታል።
ሆኖም ወረርሽኙ በኅዳር በሽታ ብቻ አላበቃም። አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት በ20ኛው መቶ ዘመን ከ300 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በፈንጣጣ ምክንያት ሞተዋል። በሕክምናው መስክ ሰፊ ምርምር ቢደረግም እንኳ አሁንም ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኤድስ፣ በሳንባ ነቀርሳና በወባ በሽታ ምክንያት ሕይወታቸው በአጭሩ ይቀጫል።
ጦርነት፣ ረሃብም ሆነ ወረርሽኝ መጨረሻ ላይ ለሞት መዳረጋቸው አይቀርም። በቃኝን የማያውቀው መቃብር የሞቱ ሰዎችን ያለማቋረጥ እየሰበሰበ ነው።
በቅርቡ የተሻለ ጊዜ ይመጣል!
በመከራ የተሞላው ዘመን የሚያበቃበት ጊዜ ቀርቧል። ኢየሱስ በ1914 ‘ድል እያደረገ እንደወጣና’ ሰይጣንን ወደ ምድር እንዳባረረው ተመልክተናል፤ ይሁንና ድሉን ገና እንዳላጠናቀቀ ልብ በል። (ራእይ 6:2፤ 12:9, 12) በቅርቡ ኢየሱስ በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት የሰይጣንን ተጽዕኖም ሆነ ዲያብሎስን የሚደግፉ ሰዎችን ያስወግዳል። (ራእይ 20:1-3) ኢየሱስ የሦስቱን ፈረሰኞች ግልቢያ ከማስቆምም ባለፈ በእነሱ ግልቢያ ምክንያት የተከሰቱትን መጥፎ ሁኔታዎች ያስተካክላል። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተስፋ ተመልከት።
ጦርነት ተወግዶ ሰላም ይሰፍናል። ይሖዋ “ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል። ቀስትን ይሰባብራል፤ ጦርንም ያነክታል።” (መዝሙር 46:9) ሰላም ወዳድ የሆኑ ሰዎች ‘በብዙ ሰላም እጅግ ደስ ይላቸዋል።’—መዝሙር 37:11
ረሃብ ተወግዶ የተትረፈረፈ ምግብ ይኖራል። “በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል።”—መዝሙር 72:16
ወረርሽኝና ሞት ተወግደው ሁሉም ሰዎች ፍጹም ጤንነትና የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። አምላክ “እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”—ራእይ 21:4
ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ወደፊት ምድርን ሲገዛ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር የሚያሳይ ፍንጭ ሰጥቷል። ሰዎች ሰላማዊ እንዲሆኑ አስተምሯል፤ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር መግቧል፤ የታመሙትን ፈውሷል፤ የሞቱትን ጭምር አስነስቷል።—ማቴዎስ 12:15፤ 14:19-21፤ 26:52፤ ዮሐንስ 11:43, 44
የይሖዋ ምሥክሮች የእነዚህ ፈረሰኞች ግልቢያ ካበቃ በኋላ ለሚመጣው በረከት ዝግጁ መሆን የምትችለው እንዴት እንደሆነ ከራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሊያሳዩህ ፈቃደኞች ናቸው። ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ?