በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

ለሚሊዮኖች ጥቅም ያስገኙ የርቀት የትርጉም ቢሮዎች

ለሚሊዮኖች ጥቅም ያስገኙ የርቀት የትርጉም ቢሮዎች

መጋቢት 1, 2021

 ቋሚ ከሆኑ የትርጉም ቡድኖቻችን መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሥራቸውን የሚያከናውኑት በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ሳይሆን በርቀት የትርጉም ቢሮዎች (RTO) ውስጥ ነው። ይህ ዝግጅት ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ተርጓሚዎች በርቀት የትርጉም ቢሮ ውስጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ መሥራት እንዲችሉ ምን መሣሪያ ያስፈልጋቸዋል? የትርጉም ቡድኑ የሚገኝበት ቦታ በትርጉም ሥራው ጥራት ላይ ለውጥ የሚያመጣውስ እንዴት ነው?

 የርቀት የትርጉም ቢሮ መቋቋሙ ተርጓሚዎች ቋንቋቸው በስፋት በሚነገርበት አካባቢ እንዲኖሩ ያስችላቸዋል። የሎው ጀርመንኛ ተርጓሚ የሆነችው ካረን እንዲህ ብላለች፦ “በኳውቴሞክ፣ ቺዋዋ፣ ሜክሲኮ ወደሚገኘው የርቀት የትርጉም ቢሮ ከተዛወርን ወዲህ ሁልጊዜ ሎው ጀርመንኛ እንጠቀማለን፤ አብረውን ከሚሠሩት ተርጓሚዎች ጋር ስንነጋገር፣ ስናገለግል እንዲሁም ገበያ ስንወጣ ቋንቋውን እንጠቀማለን። በቋንቋው ተናጋሪዎች ነው የተከበብነው። ለረጅም ጊዜ ያልሰማናቸውን ፈሊጣዊ አነጋገሮች እንሰማለን፤ እንዲሁም የቋንቋውን ለውጥ መከታተል እንችላለን።”

 ጋና ውስጥ የፍራፍራ ቋንቋ ተርጓሚ የሆነው ጄምስ፣ በቅርንጫፍ ቢሮው ያለው የቤቴል ቤተሰብ አልፎ አልፎ እንደሚናፍቀው በሐቀኝነት ተናግሯል። አክሎ ግን እንዲህ ብሏል፦ “በርቀት የትርጉም ቢሮው ውስጥ መሥራት ያስደስተኛል። በአካባቢው ቋንቋ ስሰብክና ሰዎቹ ለምሥራቹ የሚሰጡትን ምላሽ ስመለከት ልቤ ይነካል።”

 ወንድሞች የርቀት የትርጉም ቢሮ የት መቋቋም እንዳለበት የሚወስኑት እንዴት ነው? በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ዓለም አቀፍ ንድፍና ግንባታ ክፍል የሚያገለግለው ጆሴፍ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ አካባቢዎች አስተማማኝ የሆነ የኤሌክትሪክና የውኃ አቅርቦት ወይም የሚተረጎመውን ጽሑፍ ለመላላክ የሚያስችል የኢንተርኔት አገልግሎት የላቸውም፤ አንዱ እንቅፋት ይህ ነው። በዚህም የተነሳ የርቀት የትርጉም ቢሮ ለማቋቋም ስናስብ ቋንቋው የሚነገርባቸውን የተለያዩ አካባቢዎች እንደ ምርጫ እንይዛለን።”

 በጥቅሉ ሲታይ የርቀት የትርጉም ቢሮ ለማቋቋም ፈጣኑና ረከስ ያለው አማራጭ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ፣ የስብሰባ አዳራሽ ወይም የሚስዮናውያን ቤት መጠቀም ነው፤ ከዚያም ተርጓሚዎቹ ከሌላ ቦታ እየተመላለሱ መተርጎም ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት አማራጭ ካልተገኘ፣ ለተርጓሚዎች መኖሪያና የሥራ ቦታ የሚሆን ሕንፃ ለመግዛት ፈቃድ ሊሰጥ ይችላል። የትርጉም ቡድኑ ሁኔታ ከጊዜ በኋላ ከተቀየረ እነዚህ ሕንፃዎች በቀላሉ ተሸጠው ገንዘቡ ለሌላ አስፈላጊ ዓላማ ሊውል ይችላል።

ሥራውን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት

 በ2020 የአገልግሎት ዓመት የርቀት የትርጉም ቢሮዎችን ሥራ ለመደገፍ 13 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አውጥተናል። በርቀት የትርጉም ቢሮዎች ውስጥ ያሉት የትርጉም ቡድኖች ኮምፒውተሮች፣ ሶፍትዌሮች፣ የድምፅ መቅጃ መሣሪያዎች፣ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲሁም የውኃና የኃይል አቅርቦት ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ለአንድ ተርጓሚ የሚያስፈልገውን ኮምፒውተር ለማዘጋጀት እስከ 750 የአሜሪካ ዶላር ሊፈጅ ይችላል። ኮምፒውተሩ ላይ፣ የተገዙ ሶፍትዌሮችና ዎችታወር ትራንስሌሽን ሲስተም የተባለው ፕሮግራም ይጫንበታል፤ ይህ ፕሮግራም ተርጓሚዎች ሥራቸውን እንዲያደራጁና ማመሣከሪያዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

 ከዚህም በተጨማሪ ተርጓሚዎች በቢሯቸው ውስጥ ቅጂ ለማከናወን የሚያስፈልጉት የድምፅ መቅጃ መሣሪያዎች ይሟሉላቸዋል። በተለይ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት እነዚህ መሣሪያዎች በጣም ጠቃሚ ነበሩ፤ ምክንያቱም በርካታ ተርጓሚዎች እነዚህን መሣሪያዎች ቤታቸው ወስደው ጽሑፎችንና ቪዲዮዎችን መቅዳታቸውን መቀጠል ችለዋል።

 በአካባቢው የሚኖሩ ፈቃደኛ ሠራተኞችም የተተረጎሙትን ጽሑፎች በመገምገምና የርቀት የትርጉም ቢሮውን በመንከባከብ እገዛ ያበረክታሉ። በኬፕ ታውን፣ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው የአፍሪካንስ የርቀት የትርጉም ቢሮ የምታገለግለው ክርስቲን “ብዙ አስፋፊዎችና የዘወትር አቅኚዎች እዚህ የማገልገል አጋጣሚ አግኝተዋል” በማለት ተናግራለች።

 እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች በዚያ የማገልገል መብት በማግኘታቸው ደስተኞች ናቸው። በአንድ የርቀት የትርጉም ቢሮ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆና የምታገለግል አንዲት እህት እዚያ መሥራት “መንፈስን የሚያድስ” እንደሆነ ተናግራለች። በአካባቢው የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች ድምፃቸውን በመቀዳትም እገዛ ያበረክታሉ። በቬራክሩዝ፣ ሜክሲኮ የምትኖር ሑዋና የተባለች የቶተናክ ቋንቋ ተርጓሚ እንዲህ ብላለች፦ “አሁን የምንኖረው ቋንቋችን በሚነገርባቸው ከተሞች አቅራቢያ ስለሆነ ብዙ ወንድሞችና እህቶች በቀላሉ እዚህ መጥተው ቪዲዮዎችንና ኦዲዮዎችን መቀዳት ይችላሉ።”

 ይሁንና የርቀት የትርጉም ቢሮዎች መቋቋማቸው የትርጉም ሥራው ጥራት እንዲጨምር አድርጓል? በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩት አንባቢዎቻችን መካከል ብዙዎቹ “አዎ” የሚል መልስ ይሰጣሉ። በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የሚነገረው የኮንጎ ቋንቋ ተርጓሚ የሆነው ሴድሪክ እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ስንተረጉም የምንጠቀምበትን ቋንቋ ‘የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ኮንጎ’ ብለው ይጠሩት ነበር፤ ምክንያቱም በእኛ ጽሑፎች ላይ ያለው ቋንቋ ብዙዎቹ የኮንጎ ተናጋሪዎች ከሚጠቀሙበት ቋንቋ የተለየ ነበር። አሁን ግን ጽሑፎቻችን የሚተረጎሙት በዘመናዊ ኮንጎ፣ ማለትም ሰዎች በየዕለቱ ቋንቋውን በሚጠቀሙበት መንገድ እንደሆነ ይናገራሉ።”

 በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው አንዲሌ የተባለው የቆሳ ቋንቋ ተርጓሚም ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥቷል። እንዲህ ብሏል፦ “ብዙዎች ስንተረጉም የምንጠቀምበት ቋንቋ እንደተለወጠ ይነግሩናል። ቀደም ሲል እንግሊዝኛውን መጠበቂያ ግንብ ያነብቡ የነበሩ ልጆችም እንኳ አሁን በቆሳ የተዘጋጀውን ጽሑፍ ማንበብ ጀምረዋል። በተለይ ተሻሽሎ የወጣው አዲስ ዓለም ትርጉም ተፈጥሯዊ ለዛውን የጠበቀ በመሆኑ በጣም ተደስተዋል።”

 የርቀት የትርጉም ቢሮዎችን ለማቋቋም፣ ለመንከባከብና ሠራተኞችን ለማሟላት የሚያስፈልገው ወጪ በሙሉ የሚሸፈነው ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት በሚደረጉት መዋጮዎች ነው፤ እንዲህ ያለውን መዋጮ በ​donate.pr418.com አማካኝነትም ማድረግ ይቻላል።