በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

ለየት ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠኛ

ለየት ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠኛ

ሚያዝያ 1, 2022

 ጥር 2021 የበላይ አካሉ ለዘላለም በደስታ ኑር! a የተባለ አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠኛ መሣሪያ መውጣቱን ገለጸ። ይህን ማስታወቂያ ስትሰማ ምን ተሰማህ? በካናዳ የሚኖረው ማቲው እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ተደስቼ ነበር፤ ጽሑፉ የተዘጋጀበትን ዓላማ እንዲሁም መስክ ላይ እንዴት ሙከራ እንደተደረገበት የሚገልጹትን ንግግሮችና ቪዲዮዎች ስሰማና ስመለከት ደግሞ ጉጉቴ ይበልጥ ጨመረ። ጽሑፉን አግኝቼ እስክጠቀምበት በጣም ጓጉቼ ነበር።”

 ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው ጽሑፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናበት አዲስ ዘዴ አስተዋውቆናል። ሆኖም በአዲሱ መጽሐፍና ቀደም ሲል በነበሩት ማስጠኛ መሣሪያዎች መካከል ያለው ልዩነት ይህ ብቻ አይደለም። ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ የታተመ ቅጂ የምትጠቀም ከሆነ መጽሐፉን ስትይዘው እጅህ ላይ ለየት ያለ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ይህ የሆነበትን ምክንያት ለማወቅ ከመጽሐፉ ሕትመት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ነገሮችን እስቲ እንመልከት።

ለየት ያለ ስሜት የሚፈጥር አዲስ መጽሐፍ

 ወፍራም ወረቀት። እንዲህ ያለ ወረቀት መጠቀማችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ ከ600 የሚበልጡ ባለ ቀለም ሥዕሎችን ይዟል፤ ይህም ምን ያስተምረናል? ከተባለው መጽሐፍ በአሥር እጥፍ ገደማ የሚበልጥ ነው! ከዚህም ሌላ አዲሱ መጽሐፍ፣ ጽሑፍም ሆነ ሥዕል የሌለባቸው ብዙ ክፍት ቦታዎች አሉት። እነዚህ ሁለት ነገሮች የሚፈጥሩት ችግር አለ፦ ወረቀቱ ስስ ከሆነ በቀጣዩ ገጽ ላይ ያለው ሥዕል ከታች ተደርቦ ይታያል። በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ፣ ዩ ኤስ ኤ ባለው ዓለም አቀፍ የሕትመት ክፍል የሚሠሩት ወንድሞች ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል መፍትሔ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀመሩ፤ ለዚህም ሲሉ አሁን ለሕትመት በምንጠቀምባቸው አራት የተለያዩ ዓይነት ወረቀቶች ላይ ሙከራ አደረጉ። የበላይ አካሉ የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ አራቱንም የሕትመት ናሙናዎች ከተመለከተ በኋላ ከበስተ ጀርባ ያለውን ጽሑፍ ብዙም የማያሳየውን ወረቀት መረጠ። በእርግጥ ይህ ወረቀት አብዛኞቹን ጽሑፎቻችንን ለማተም ከምንጠቀምበት ወረቀት በ16 በመቶ ዋጋው ከፍ ያለ ነው፤ ሆኖም ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ በዚህ ዓይነት ወረቀት መታተሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መጽሐፉን በሚያነቡበት ወቅት በቀጣዩ ገጽ ላይ ያለው ጽሑፍና ሥዕል ተደርቦ እየታየ ትኩረታቸውን እንዳይሰርቀው ያደርጋል።

በስተ ቀኝ ያለው፣ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ለማተም የተጠቀምንበትን ወረቀት የሚያሳይ ነው

 ለየት ያለ የሽፋን ማሸጊያ። የአዲሱ መጽሐፍ ሽፋን ከሌሎች መጽሐፎቻችን ሽፋን ይለያል፤ ሽፋኑ ላይ የተለጠፈው ማሸጊያ ወይም እርጥበት መከላከያ ለየት ያለ ነው። የአዲሱ መጽሐፍ ማሸጊያ በሌሎቹ መጻሕፍት ላይ እንዳለው የሚያንጸባርቅ አይደለም፤ ይህም የሽፋኑን ሥዕል ጎላ ብሎ እንዲታይ አድርጎታል። እንዲህ ያለው ማሸጊያ መጽሐፉ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ በመዋሉ ምክንያት ቶሎ እንዳያረጅም ይከላከላል። ሆኖም እንዲህ ያለው ማሸጊያ ከሚያንጸባርቀው ማሸጊያ በአምስት እጥፍ ገደማ ይወደዳል። በመሆኑም የተለያዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንዲህ ያለውን ማሸጊያ በጣም ውድ ባልሆነ ዋጋ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀመሩ።

ሽፋኖቹ ሲታሸጉ

 ዋጋቸው ወደድ የሚል የሕትመት ቁሳቁሶች የተመረጡት ለምንድን ነው? በዓለም አቀፍ የሕትመት ክፍል ውስጥ የሚሠራ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ይህ መጽሐፍ በደንብ ጥቅም ላይ እንደሚውል እንጠብቃለን፤ በመሆኑም ዓላማችን በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ቢውልም ቶሎ የማይበላሽ መጽሐፍ ማተም ነው።” በብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ባለው የሕትመት ክፍል የሚሠራው ኤድዋርዶ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ድርጅት ይህ መጽሐፍ የሚያምር፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆይና ለአጠቃቀም ምቹ እንዲሆን ለማድረግ ጥራት ያላቸው የሕትመት ቁሳቁሶችን በመጠቀሙ በጣም ደስ ብሎናል፤ ደግሞም ይህ የተደረገው በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ ሳይባክን ነው።”

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ማተም

 ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ ሕትመት የጀመረው መጋቢት 2021 ነው። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ይህን ማድረግ ተፈታታኝ ነበር። በቤቴል የእንቅስቃሴ ገደብ ስለተጣለ ተመላላሽ ቤቴላውያን በሕትመቱ ሥራ ሊያግዙን አልቻሉም፤ በዚህ ወቅት አዳዲስ ቤቴላውያንን ማስገባትም የሚቻል አልነበረም። በመሆኑም አንዳንድ ማተሚያዎቻችን በቂ የሰው ኃይል አልነበራቸውም፤ ሌሎቹ ደግሞ መንግሥት በጣለው እገዳ የተነሳ በጊዜያዊነት ተዘግተው ነበር።

 ታዲያ ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ የተወጣነው እንዴት ነው? ማተሚያዎቹ ሥራ ሲጀምሩ በቤቴል በሌሎች ዲፓርትመንቶች ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች ለጊዜው በማተሚያ ክፍሉ ውስጥ እንዲያገለግሉ ተመደቡ። በዓለም አቀፍ የሕትመት ክፍል ውስጥ የሚሠራው ጆኤል እንዲህ ብሏል፦ “እነዚህ ወንድሞችና እህቶች የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ማሳየታቸውና አዲስ ምድብ ለመልመድ ፈቃደኛ መሆናቸው ይህን ሥራ ለማከናወን ትልቅ እገዛ አበርክቷል።”

 ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ እስካሁን ድረስ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ቅጂዎች ማተም ችለናል። ሕትመቱን ለማከናወን ማተሚያ ፕሌቶችን፣ ማሸጊያዎችን፣ ወረቀቶችን፣ ቀለሞችንና ማጣበቂያዎችን ጨምሮ በርካታ ቁሳቁሶች ያስፈልጋሉ። ይህን ጽሑፍ ባተምንባቸው የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ውስጥ ከ2.3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ አውጥተናል። ወጪ ለመቀነስ ስንል ያተምነው፣ ጉባኤዎች ያዘዙትን መጻሕፍት ያህል ብቻ ነው።

“ድንቅ የሥነ ጥበብ ሥራ ነው”

 የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎችና ጥናቶቻቸው ስለዚህ አዲስ መጽሐፍ ምን ተሰምቷቸዋል? በአውስትራሊያ የሚኖር ፖል የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ በጣም ደስ የሚል ስለሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የማስጠናው በጉጉት ነው። መጽሐፉ የተዘጋጀበት መንገድ ማራኪ ከመሆኑም ሌላ አሳታፊ ነው። ቅልብጭ ያለ መረጃ፣ የልብን አውጥቶ ለመናገር የሚያነሳሱ ጥያቄዎች፣ ቪዲዮዎች፣ ሥዕሎች፣ ሰንጠረዦችና ተማሪው የሚያወጣቸውን ግቦች አንድ ላይ አጣምሮ የያዘ ግሩም መጽሐፍ ነው። የማስተማር ችሎታዬን እንዳሻሽል የሚያነሳሳ ድንቅ የሥነ ጥበብ ሥራ ነው።”

 በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲህ ብሏል፦ “አዲሱን መጽሐፍ በጣም ወድጄዋለሁ። ሥዕሎቹ ዋና ዋና ነጥቦቹን ለመረዳት አግዘውኛል። ቪዲዮዎቹ ልቤን ስለነኩት ለተግባር አነሳስተውኛል።” ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በሳምንት ሁለት ጊዜ እያጠና ሲሆን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይም አዘውትሮ ይገኛል።

 ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ በበርካታ ቋንቋዎች በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ቅጂዎች ገና መታተም አለበት። እስከ ዛሬ ድረስ፣ የበላይ አካሉ ይህ መጽሐፍ በ710 ቋንቋዎች እንዲታተም ፈቃድ ሰጥቷል፤ ይህም ምን ያስተምረናል? የተባለው መጽሐፍ ከታተመባቸው ቋንቋዎች በ340 ይበልጣል!

 የሕትመት ወጪው የሚሸፈነው እንዴት ነው? ለዓለም አቀፉ ሥራ ከሚደረጉ መዋጮዎች ነው፤ ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ የሚደረጉት በ​donate.pr418.com አማካኝነት ነው። የምታደርጉት መዋጮ ስለ ይሖዋ መማርና ‘ለዘላለም በደስታ መኖር’ የሚፈልጉ ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መሣሪያዎች ለማዘጋጀት ይረዳናል፤ በልግስና የምታደርጉትን መዋጮ እናደንቃለን።—መዝሙር 22:26

a የመጽሐፉ መውጣት የተገለጸው ከዓመታዊው ስብሰባ ጋር ተያይዞ በተካሄደ መንፈሳዊ ፕሮግራም ላይ ነው፤ ፕሮግራሙ በ​JW ብሮድካስቲንግ ላይ ተላልፎ ነበር።