በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

መስማት የተሳናቸው አልተረሱም

መስማት የተሳናቸው አልተረሱም

ሐምሌ 1, 2022

 ይሖዋ አምላክ ሁሉም ዓይነት ሰዎች፣ ሁኔታቸው ሳይገድባቸው ስለ እሱና በሰማይ ስለተቋቋመው መንግሥቱ እንዲማሩ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ዓላማ ለማሳካት ሲሉ በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች የሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱሶችንና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥኛ ጽሑፎችን ያዘጋጃሉ፤ ይህም መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የሚዘጋጁትንም ይጨምራል። እንዲያውም ድርጅታችን በሺዎች የሚቆጠሩ ጽሑፎች በምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎች እንዲዘጋጁ አድርጓል፤ a እነዚህን ቪዲዮዎች ከ100 በሚበልጡ የምልክት ቋንቋዎች ማግኘት ይቻላል። ለመሆኑ እነዚህን ቪዲዮዎች የምናዘጋጀውና የምናሰራጨው እንዴት ነው? ከዚህ ሥራ ጋር በተያያዘ ባለፉት ዓመታት ምን ማሻሻያዎችንስ አድርገናል?

የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎች የሚዘጋጁት እንዴት ነው?

 የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎችን የሚያዘጋጁት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የትርጉም ቡድኖች ናቸው። የትርጉም ቡድኑ አባላት የሚተረጉሙትን ጽሑፍ በቅድሚያ በደንብ አድርገው ይዘጋጁታል። ከዚያም መልእክቱን በምልክት ቋንቋ ጥሩ አድርገው ማስተላለፍ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይወስናሉ። ቀጥሎ ደግሞ ጽሑፉን በቪዲዮ ይቀዱታል። በአሁኑ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎችን ወደ ምልክት ቋንቋ በቋሚነት የሚተረጉሙ 60 ቡድኖች አሉ፤ 40 የትርጉም ቡድኖች ደግሞ ጽሑፎችን አልፎ አልፎ ይተረጉማሉ።

 ቀደም ባሉት ጊዜያት የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎችን ማዘጋጀት በጣም ብዙ ወጪ ይጠይቅ ነበር። በወቅቱ የቪዲዮ ካሜራዎችና ሌሎች መሣሪያዎች ውድ ነበሩ። ከዚህም ሌላ ቪዲዮዎችን የምንቀዳው ራሳችን በምናዘጋጃቸው ስቱዲዮዎች ውስጥ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ ለስቱዲዮ የሚሆኑንን ሕንፃዎች መጀመሪያ ማደስ ሊያስፈልገን ይችላል። በአጠቃላይ አንድ የምልክት ቋንቋ ትርጉም ቡድን የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሙሉ ለማሟላት ከ30,000 የአሜሪካ ዶላር በላይ ማውጣት ያስፈልገን ነበር።

 ድርጅታችን በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ሲል የትርጉም ሥራውን ለማሻሻልና ለማቅለል የሚያስችሉ መንገዶችን ሲፈልግ ቆይቷል። ለዚህም ሲባል ብዙ ወጪ ሳያስወጣ አስፈላጊውን ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ዘመናዊ መሣሪያ መጠቀም ጀምረናል። የትርጉም ቡድኖች ስቱዲዮዎችን ከመጠቀም ይልቅ ቪዲዮዎችን እዚያው ቢሯቸው ውስጥ መቅዳት ጀመሩ፤ ቪዲዮውን ሲቀዱ ከኋላቸው አረንጓዴ ሸራ ወይም ተመሳሳይ ነገር እንዲኖር ያደርጋሉ። አንድ ቪዲዮ ላይ በርከት ያሉ ሰዎች የሚያስፈልጉ ከሆነ ወንድሞችና እህቶች የየራሳቸውን ድርሻ ቢሯቸው ወይም ቤታቸው ሆነው ይቀዳሉ፤ እንደ ቀድሞው ስቱዲዮ መሄድ አያስፈልጋቸውም።

 የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎችን የሚቀዱ ወንድሞችና እህቶችን የሚያግዝ ሶፍትዌርም አዘጋጅተናል። እነዚህ ማሻሻያዎች የትርጉም ቡድኖች አንድን የምልክት ቋንቋ ቪዲዮ ለማዘጋጀት የሚወስድባቸውን ጊዜ በግማሽ ቀንሰውታል። ወንድሞቻችን እነዚህ ማሻሻያዎች በመደረጋቸው ተደስተዋል። አሌክሳንደር የተባለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎች ከበፊቱ ይበልጥ ቶሎ ቶሎ ይወጣሉ። ይህም በጣም አስደስቶኛል። ቪዲዮዎቹን በየቀኑ እመለከታቸዋለሁ።”

 በአሁኑ ወቅት አንድ የትርጉም ቡድን የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት የሚወጣው ወጪ ከ5,000 የአሜሪካ ዶላር ያነሰ ነው። ይህም በብዙ የምልክት ቋንቋዎች ቪዲዮዎችን ለማዘጋጀት አስችሎናል።

የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎች የሚሰራጩት እንዴት ነው?

 የትርጉም ቡድኑ አንድ የምልክት ቋንቋ ቪዲዮ ካዘጋጀ በኋላ ቪዲዮው ለተጠቃሚዎቹ መድረስ አለበት። ቀደም ባሉት ዓመታት የቪዲዮ ካሴቶችንና ዲቪዲዎችን እናዘጋጅ ነበር። ሆኖም ይህ ውድ ከመሆኑም ሌላ ጊዜና ብዙ ሥራ ይጠይቃል። ቪዲዮው ከተቀረጸ በኋላ ለአሳታሚ ድርጅት መላክ ያስፈልገዋል። በመጨረሻም የቪዲዮ ካሴቶቹና ዲቪዲዎቹ ወደየጉባኤዎቹ ይላካሉ። በ2013 ብቻ የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎችን ለማዘጋጀት ከ2,000,000 በላይ የአሜሪካ ዶላር አውጥተናል።

 መስማት የተሳናቸው ሰዎች ቪዲዮዎቹን ሲያገኙ በጣም ይደሰታሉ። ሆኖም ቪዲዮዎቹ ለአጠቃቀም አመቺ አልነበሩም፤ በተለይ ደግሞ የካሴቶቹና የዲቪዲዎቹ ብዛት እየጨመረ ሲሄድ ለመጠቀም አስቸጋሪ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ለመቅዳት በርከት ያሉ ዲቪዲዎች ያስፈልጋሉ። በብራዚል የሚኖረው ዢለኒ እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “አንድ ጥቅስ ማውጣት ከፈለግን መጀመሪያ ጥቅሱ የሚገኝበትን የቪዲዮ ካሴት ማግኘት ይኖርብናል፤ ከዚያ ደግሞ ጥቅሱን እንፈልጋለን። ይህ በጣም አስቸጋሪ ነበር።” ሃፋይኒ የተባለች የምልክት ቋንቋ ዲቪዲዎችን የምትጠቀም እህት እንዲህ ብላለች፦ “የግል ጥናት ማድረግ አድካሚ ነበር። ጥቅሶችን ወይም ማመሣከሪያ ጽሑፎችን መፈለጉ ብቻ ረጅም ሰዓት ይወስድብን ነበር።” ወንድሞችና እህቶች አገልግሎት ሲወጡ ዲቪዲዎችን ወይም የቪዲዮ ካሴቶችን ይዘው ይሄዱ ነበር፤ ፍላጎት ያለው ሰው ሲያገኙ ቪዲዮውን በራሱ ቴሌቪዥን ላይ ያሳዩታል። እንዲያውም አንዳንድ ወንድሞች የራሳቸውን የዲቪዲ ማጫወቻ ይዘው ይሄዱ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን በእጅ ለመያዝ አመቺ የሆኑና ስክሪን ያላቸው የዲቪዲ ማጫወቻዎች መጡ፤ ብዙ ወንድሞችና እህቶች በእነዚህ ይጠቀሙ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ቦቢ እንዲህ ብሏል፦ ለሰዎች አንድ ጥቅስ ካሳየህ በኋላ ሌላ ጥቅስ ለመድገም ከፈለግክ ዲቪዲውን አውጥተህ መቀየር ይኖርብሃል። ይህ ጊዜ የሚወስድ ነገር ነው፤ በውይይታችን ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ለመጠቀምም አያነሳሳም።”

 በ2013 የይሖዋ ድርጅት JW Library Sign Language የተባለውን አፕሊኬሽን አወጣ፤ ይህ አፕሊኬሽን ወንድሞችና እህቶች በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ ቪዲዮዎችን በራሳቸው ስልክ ወይም ታብሌት ላይ አውርደው ለማጫወት የሚያስችላቸው ነው። አፕሊኬሽኑ መጀመሪያ የወጣው በአሜሪካ የምልክት ቋንቋ ነበር። ከዚያም በ2017 ሁሉንም የምልክት ቋንቋዎች ማጫወት እንዲችል ተደረገ። በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞችና እህቶች በዚህ በጣም ተደስተዋል። በብራዚል የሚኖር ዡዜሊኖ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “እውነት አልመሰለኝም ነበር! የበላይ አካሉ መስማት ለተሳነን ሰዎች ምን ያህል ፍቅር እንዳለው እንዳስብ አድርጎኛል። መስማት እንደሚችሉ ሰዎች ሁሉ እኛም በእውነት ውስጥ እድገት እንድናደርግ እንደሚፈልጉ ተረድቻለሁ። ደስታዬ ወሰን አልነበረውም። ይህ አፕሊኬሽን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ይበልጥ አነሳስቶኛል።”

አንዲት እህት JW Library Sign Language አፕሊኬሽን ስትጠቀም

 በአሁኑ ወቅት ሁሉንም የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎች የምናወጣው ኢንተርኔት ላይ ነው፤ ቪዲዮዎቹን ድረ ገጻችን ላይ አሊያም JW Library Sign Language የተባለው አፕሊኬሽን ላይ ማግኘት ይቻላል። ይህም የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎችን መተርጎም፣ መቅዳትና ማሰራጨት ቀላል እንዲሆን አድርጓል፤ እንደ በፊቱ ወራት ወይም ዓመታት የሚፈጅ ሳይሆን በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሥራ ሆኗል። እንዲያውም ብዙ የምልክት ቋንቋዎች በአፍ ከሚነገሩ ቋንቋዎች ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ጽሑፎችን ማውጣት ችለዋል።

 መስማት የተሳናቸው አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሰጡትን አስተያየት እስቲ እንመልከት። ክሊዝዬ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ይህን ያህል የሚጨነቅ ድርጅት የት ይገኛል? መንፈሳዊ ምግብ ቀላልና አመቺ በሆነ መንገድ እየቀረበልን ነው። የይሖዋ ድርጅት ያደረገልን ነገር ዓለም ሊያቀርብልን ከሚችል ከማንኛውም ነገር ጋር አይወዳደርም።” ቭላዲሚር ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ቪዲዮዎቹ ይሖዋ መስማት ለሚችሉ ሰዎች የሚያስበውን ያህል መስማት ለተሳናቸው ሰዎችም እንደሚያስብ እንድገነዘብ አድርጎኛል።”

 በምልክት ቋንቋ በሚዘጋጁ ቪዲዮዎቻችን ላይ ብዙውን ጊዜ የሚከተለው ሐሳብ ይገኛል፦ “ይህ ጽሑፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ከሚታተሙት ጽሑፎች መካከል አንዱ ሲሆን ይህ የማስተማር ሥራ የሚደገፈው ደግሞ ሰዎች በፈቃደኝነት በሚያደርጉት መዋጮ ነው።” ብዙዎቹ መዋጮዎች የሚደረጉት donate.pr418.com​ን በመጠቀም ነው፤ ለምታደርጉት መዋጮ በጣም እናመሰግናለን። በመዋጮ የሚገኘው ገንዘብ የምልክት ቋንቋ የሚጠቀሙትን ጨምሮ ለሁሉም ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሶችንና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥኛ ጽሑፎችን ለማዘጋጀት ያስችለናል።

a የምልክት ቋንቋ የሚጠቀሙ ሰዎች ሐሳባቸውን የሚያስተላልፉት እጃቸውንና የፊታቸውን መግለጫ በመጠቀም ነው። በመሆኑም የምልክት ቋንቋ ጽሑፎች የሚዘጋጁት በቪዲዮ ነው።