የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
መንፈሳዊ ምግብ የሚያደርስ ትንሽ መሣሪያ
መስከረም 1, 2020
የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ዘመን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ መንፈሳዊ ምግብ በዲጂታል ፎርማት ይቀርብላቸዋል። ሆኖም በበርካታ አገሮች ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችን ኢንተርኔት ለመጠቀም የሚያስችል ገንዘብ የላቸውም። ሌሎቹ ደግሞ የሚኖሩት ኢንተርኔት በሚቆራረጥበት፣ ቀርፋፋ በሆነበት ወይም ከናካቴው በሌለበት አካባቢ ነው።
ያም ቢሆን የኢንተርኔት አገልግሎት የሌላቸው ብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጽሑፎችንና ቪዲዮዎችን ማውረድ ችለዋል! ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
JW ቦክስ ኢንተርኔት እንደልብ ማግኘት ለማይችሉ ጉባኤዎች የተዘጋጀ አነስተኛ መሣሪያ ነው። መሣሪያው ከአንድ የንግድ ድርጅት የተገዛ ሲሆን በቤቴል የሚገኘው የኮምፒውተር ዲፓርትመንት ያዘጋጀው ሶፍትዌር እንዲሁም በjw.org ላይ የሚገኙ ዲጂታል ጽሑፎችና ቪዲዮዎች ተጭነውበታል። እያንዳንዱ መሣሪያ 75 የአሜሪካ ዶላር አካባቢ ያወጣል።
በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ወንድሞችና እህቶች ስልካቸውን ወይም ታብሌታቸውን በዋይፋይ አማካኝነት ከJW ቦክስ ጋር አገናኝተው ጽሑፎችንና ቪዲዮዎችን ማውረድ ይችላሉ። ጊዜ ያለፈባቸው ወይም ዋጋቸው ውድ ያልሆነ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ያሏቸው ወንድሞችም ጭምር በዚህ ዝግጅት መጠቀም ይችላሉ። ይሁንና አንድ ጉባኤ የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት ካልቻለ JW ቦክስ ላይ አዳዲስ ጽሑፎችንና ቪዲዮዎችን መጫን የሚቻለው እንዴት ነው? ቅርንጫፍ ቢሮው jw.org ላይ የወጡትን አዳዲስ ነገሮች በJW ቦክስ ላይ መጫን የሚያስችል ፍላሽ ዲስክ በየተወሰነ ጊዜው ለጉባኤዎች ይልካል፤ እያንዳንዱ ፍላሽ ዲስክ 4 የአሜሪካ ዶላር ገደማ ያወጣል።
JW ቦክስ ለወንድሞቻችን ምን ጥቅም አስገኝቶላቸዋል? በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የሚኖር ናታን አድሩዋንድራ የተባለ አባት እንዲህ ብሏል፦ “‘ይሖዋ ሆይ፣ . . . በአንተ እታመናለሁ’ እና የሎጥን ሚስት አስታውሱ የተባሉትን ድራማዎች ለማውረድ ለረጅም ጊዜ ስሞክር ነበር። ግን ተሳክቶልኝ አያውቅም፤ ስለዚህ ተስፋ ቆርጬ ነበር። አሁን ግን እነዚህን ቪዲዮዎች ስልኬ ላይ ማውረድ ችያለሁ፤ ይህ ደግሞ ልጆቻችንን በተሻለ መንገድ ለማስተማር ይረዳናል።”
በናይጄርያ በሚገኙ ጉባኤዎች JW ቦክስን ለማስተካከል የሚያግዝ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች JW ቦክስን ከይሖዋ እንዳገኙት ልዩ ስጦታ አድርገው ነው የሚመለከቱት። በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን ውስጥ የሚገኙትን ጽሑፎችና ቪዲዮዎች በቀላሉ ማውረድ በመቻላቸው በጣም ተደስተዋል።”
እስካሁን ድረስ በአፍሪካ፣ በኦሺያንያና በደቡብ አሜሪካ ለሚገኙ ወንድሞች ከ1,700 የሚበልጡ JW ቦክሶች ተልከዋል፤ ከዚህ በኋላም ለሌሎች ጉባኤዎች ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ለዚህ ዝግጅት የሚውለው ወጪ የሚገኘው ከየት ነው? ለዓለም አቀፉ ሥራ ከተደረገው መዋጮ ነው፤ ከእነዚህ መዋጮዎች መካከል አብዛኞቹ የሚደረጉት በdonate.pr418.com አማካኝነት ነው። በልግስና ለምታደርጉት መዋጮ እናመሰግናለን።