በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

መዳፋችን ውስጥ ያለ ቤተ መጻሕፍት

መዳፋችን ውስጥ ያለ ቤተ መጻሕፍት

መስከረም 1, 2021

 “ከተወሰኑ ዓመታት በፊት መንፈሳዊ ምግቦች በዲጂታል ፎርማት ይቀርባሉ ብሎ ማሰብ በጣም ከባድ ነበር።” አንተም በዚህ ሐሳብ ትስማማለህ? ሐሳቡ የተወሰደው ጄፍሪ ጃክሰን በ2020 የበላይ አካሉ ሪፖርት ቁጥር 6 ላይ ከሰጠው የማበረታቻ ንግግር ላይ ነው። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “አሁን ግን እንደ JW ላይብረሪ ያሉት መሣሪያዎች ባይኖሩ ኖሮ በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ምን እናደርግ እንደነበር ግራ ይገባናል። ይሖዋ ላለፉት ዓመታት በሙሉ እንዲህ ላለው ሁኔታ ሲያዘጋጀን ቆይቷል።”

 ይሖዋ ሲያዘጋጀን የቆየው እንዴት ነው? JW ላይብረሪ አፕሊኬሽንን ለመሥራት ምን ሥራ ጠይቋል? አፕሊኬሽኑን ለማሻሻል እና አገልግሎት መስጠቱን እንዲቀጥል ለማድረግስ ምን ያስፈልጋል?

በዓይነቱ የመጀመሪያ

 ግንቦት 2013 በዋናው መሥሪያ ቤት የሚገኘው የሜፕስ ፕሮግራሚንግ ክፍል ተሻሽሎ የወጣውን አዲስ ዓለም ትርጉም የያዘ አፕሊኬሽን እንዲሠራ ከበላይ አካሉ ጥያቄ ቀረበለት። በሜፕስ ፕሮግራሚንግ ክፍል ውስጥ የሚሠራው ፖል ዊሊስ እንዲህ ብሏል፦ “እስከዚያ ጊዜ ድረስ በየትኛውም የአፕሊኬሽን ስቶር ውስጥ የራሳችን የሞባይል አፕሊኬሽን አልነበረንም። ግን ወዲያውኑ ሥራውን የሚያከናውን አንድ ቡድን አቋቋምን፣ አንዳንድ ፕሮጀክቶችን ለጊዜው አቆምን፤ ከዚያም ከሌሎች ዲፓርትመንቶች ጋር በመተባበር አፕሊኬሽኑን ዲዛይን ማድረግና መሥራት ጀመርን። ብዙ ጊዜ እንጸልይ ነበር፤ ደግሞም በይሖዋ እርዳታ፣ ከአምስት ወር በኋላ ለተካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ አፕሊኬሽኑን ማድረስ ቻልን!”

 ቀጣዩ ከባድ ሥራ፣ አፕሊኬሽኑ ተጨማሪ ጽሑፎችን እና ቋንቋዎችን ያካተተ እውነተኛ ቤተ መጻሕፍት እንዲሆን ማድረግ ነበር። ጥር 2015 አፕሊኬሽኑ ላይ አብዛኞቹን ወቅታዊ ጽሑፎቻችንን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማካተት ተቻለ፤ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ደግሞ ተጠቃሚዎች በመቶዎች በሚቆጠሩ ሌሎች ቋንቋዎች ጽሑፎችን ማውረድ ቻሉ።

 ከዚያ ጊዜ አንስቶ ወንድሞቻችን አፕሊኬሽኑን ለማዘመን ብዙ ሥራዎች አከናውነዋል። ለምሳሌ ቪዲዮዎች እንዲካተቱ ተደርጓል፤ ለጉባኤ ስብሰባ የሚያስፈልጉት ሁሉም ጽሑፎችና ሚዲያዎች በአንድ ዓምድ ሥር ተካትተዋል፤ እንዲሁም ተጠቃሚዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ በቀጥታ የምርምር መርጃ መሣሪያን ማጣቀስ እንዲችሉ ዝግጅት ተደርጓል።

ላይብረሪው አገልግሎት መስጠቱን እንዲቀጥል ማድረግ

 JW ላይብረሪ በየቀኑ 8 ሚሊዮን፣ በየወሩ ደግሞ ከ15 ሚሊዮን የሚበልጡ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ላይ ይከፈታል! አፕሊኬሽኑ በእነዚህ መሣሪያዎች ላይ ያለምንም መስተጓጎል መሥራቱን እንዲቀጥል ምን ያስፈልጋል? ወንድም ዊሊስ እንዲህ ብሏል፦ “የሞባይል አፕሊኬሽን ሥራ፣ አበቃ የሚባል ነገር የለውም። አዳዲስ ገጽታዎችን ለመጨመርና ለተጠቃሚዎች ምቹ እንዲሆን ለማድረግ ሁልጊዜ መሥራት ይኖርብናል። ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቹን የሚያሠራቸው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ሁልጊዜ ስለሚታደስ አፕሊኬሽኑ ከለውጦቹ ጋር ተስማምቶ እንዲሄድ በየጊዜው ማስተካከያ ማድረግ አለብን። የውስጥ ሶፍትዌራችንንም (የኮምፒውተር ፕሮግራማችንን) በየጊዜው መከታተልና ማዘመን ያስፈልገናል። ምክንያቱም JW ላይብረሪ ላይ የሚወጡት ጽሑፎችና ቅጂዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው።” በሁሉም ቋንቋዎች የተዘጋጁትን ከቆጠርን በአሁኑ ወቅት JW ላይብረሪ ላይ 200,000 ገደማ ጽሑፎችና ከ600,000 የሚበልጡ የኦዲዮ ቅጂዎችና ቪዲዮዎች ይገኛሉ!

 አፕሊኬሽኑ አገልግሎት መስጠቱን እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስፈልገው ኮምፒውተር ብቻ አይደለም። የተለያዩ ሶፍትዌሮችንም (የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን) መግዛት ያስፈልጋል። አንዱ ፕሮግራም ብቻውን በየዓመቱ 1,500 የአሜሪካ ዶላር ያስወጣል። በተጨማሪም የሜፕስ ፕሮግራሚንግ ዲፓርትመንት፣ የተለያዩ አምራቾች የሠሯቸውን ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ለመግዛት በየዓመቱ 10,000 የአሜሪካ ዶላር ገደማ ያወጣል፤ ይህን የሚያደርጉት አፕሊኬሽኑ በአዳዲስ ኮምፒውተሮች፣ ታብሌቶችና ስልኮች ላይ በትክክል መሥራቱን ለማረጋገጥ ነው።

በመዋጮ የሚገኘው ገንዘብ እንዲቆጠብ አድርጓል

 JW ላይብረሪ ጽሑፎችን ለማተም፣ ለመጠረዝና ለመላክ የሚወጣው ወጪ በእጅጉ እንዲቀንስ አድርጓል። ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር የተባለውን ቡክሌት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የዚህን ቡክሌት የ2013 እትም ወደ 12 ሚሊዮን ገደማ ቅጂዎች አትመን ነበር። በ2020 የታተሙት የዚህ ቡክሌት ቅጂዎች ግን አምስት ሚሊዮን ብቻ ናቸው፤ ይህ የሆነው በዓለም ዙሪያ 700,000 ያህል የአስፋፊዎች ጭማሪ ኖሮም ነው። ለውጡን ያመጣው ምንድን ነው? በአሁኑ ጊዜ ብዙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የዕለት ጥቅስ የሚያነብቡት JW ላይብረሪን ተጠቅመው ስለሆነ ነው። a

“በጣም ምርጥ አፕሊኬሽን”

 JW ላይብረሪ ለተጠቃሚዎቹም ብዙ ጥቅሞች አስገኝቷል። በካናዳ የምትኖረው ዠነቪቭ፣ አፕሊኬሽኑ የጥናት ፕሮግራሟ ይበልጥ ቋሚ እንዲሆን እንደረዳት ይሰማታል። እንዲህ ስትል በሐቀኝነት ተናግራለች፦ “እውነቱን ለመናገር ከመደርደሪያ ላይ መጽሐፍ ማሰባሰብ ቢጠበቅብኝ ኖሮ በየቀኑ የማጠና አይመስለኝም። አሁን ግን ታብሌቴን ከፍቼ የፈለግኩትን ነገር ከአፕሊኬሽኑ ላይ ማንበብ እችላለሁ። የጥናት ፕሮግራሜ ቋሚ መሆኑ እምነቴ እንዲጠናከርና መንፈሳዊነቴ እንዲያድግ ረድቶኛል።”

ዠነቪቭ

 ይህ አፕሊኬሽን በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባለበት በዚህ ወቅት ይበልጥ ጠቃሚ መሆኑ ታይቷል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ሻርሊን እንዲህ ብላለች፦ “ኮቪድ-19 ዓለምን ማተራመስ ከጀመረ ወዲህ አዳዲስ የታተሙ ጽሑፎቻችንን ካየሁ ከአንድ ዓመት የሚበልጥ ጊዜ ሆኖኛል። ሆኖም JW ላይብረሪ በዚህ ሁሉ ጊዜ ተገቢውን መንፈሳዊ ምግብ እንድናገኝ አስችሎናል፤ ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ እንዲህ የመሰለ ዝግጅት ስላደረገልን በጣም አመሰግነዋለሁ።”

 በፊሊፒንስ የምትኖረው ፌይ የተናገረችው ሐሳብ የብዙዎቻችንን ስሜት የሚገልጽ ነው። እንዲህ ብላለች፦ “አጠቃላይ መንፈሳዊ ሕይወቴና ልማዶቼ ከዚህ አፕሊኬሽን ጋር የተሳሰረ ነው ማለት እችላለሁ። ከእንቅልፌ እንደነቃሁ የማነበው እሱን ነው። ቤት ውስጥ ጉድ ጉድ ስል የማዳምጠው እሱን ነው። ለስብሰባ የምዘጋጀው እሱን ተጠቅሜ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ስዘጋጅ የምጠቀመውም እሱን ነው። ፋታ ሳገኝ ቪዲዮዎች አይበታለሁ። ወረፋ እየጠበቅኩ ደግሞ ጽሑፎች ወይም መጽሐፍ ቅዱስ አነብበታለሁ። በጣም ምርጥ አፕሊኬሽን ነው።”

 ይህ አፕሊኬሽን በአገልግሎት ላይም በጣም ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ በካሜሩን ያለች አንዲት እህት አገልግሎት ላይ ሳለች ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት ሌላ እህት የተጠቀመችበትን አንድ ጥቅስ መጠቀም ፈለገች። ሆኖም ጥቅሱ የቱ ጋ እንዳለ ማስታወስ አልቻለችም። እንዲህ ብላለች፦ “ደግነቱ፣ ጥቅሱ ላይ ያሉ የተወሰኑ ቃላት ትዝ አሉኝ። አፕሊኬሽኑን ከፈትኩና መጽሐፍ ቅዱስ አወጣሁ፤ ከዚያም ቃላቱን አስገብቼ ፈለግኩ። ወዲያውኑ ጥቅሱን አገኘሁት። አሁን ይህ አፕሊኬሽን ስላለ፣ የረሳኋቸውን ጥቅሶች በቀላሉ ማግኘት እችላለሁ።”

 በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን የሚጠቅመውን JW ላይብረሪ አፕሊኬሽንን መፍጠር፣ አገልግሎት መስጠቱን እንዲቀጥል ማድረግና ማሻሻል የቻልነው እናንተ donate.pr418.com ላይ የተጠቀሱትን ዘዴዎች ተጠቅማችሁ በምታደርጉት መዋጮ ነው። ለምታሳዩት ልግስና እናመሰግናለን።

JW ላይብረሪ—እመርታዎች

  1. ጥቅምት 2013—የተሻሻለውን አዲስ ዓለም ትርጉም የያዘው አፕሊኬሽን ተለቀቀ

  2. ጥር 2015—ሌሎች ጽሑፎች በእንግሊዝኛ ወጡ፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሌሎች ቋንቋዎች ወጡ

  3. ኅዳር 2015—የጽሑፍ ማቅለሚያ ተካተተ

  4. ግንቦት 2016—ስብሰባዎች የሚለው ዓምድ ተጨመረ

  5. ግንቦት 2017—ማስታወሻ መያዝ የሚቻልበት ገጽታ ተጨመረ

  6. ታኅሣሥ 2017—ለጥናት የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ተካተተ

  7. መጋቢት 2019—የድምፅ ቅጂዎችን ማውረድ፣ ቪዲዮዎችን በቀጥታ ማጫወት እንዲሁም የምርምር መርጃ መሣሪያን ማጣቀስ ተቻለ

  8. ጥር 2021—ለዘላለም በደስታ ኑር! ለተባለው ጽሑፍ የሚያስፈልጉ ገጽታዎች ተካተቱ

a ከ​JW ላይብረሪ ላይ አንድ ነገር ሲወርድ የሚጠይቀው አነስተኛ ወጪ አለ። ለምሳሌ ያህል ባለፈው ዓመት ከ​jw.org እና ከ​JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ቪዲዮዎችን በቀጥታ ለሚያጫውቱ እንዲሁም የተለያዩ ነገሮችን ለሚያወርዱ ተጠቃሚዎቻችን አገልግሎት ለመስጠት ስንል ከ1.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ አድርገናል። እንደዚያም ሆኖ ይህ ወጪ የታተሙ ጽሑፎችን፣ ሲዲዎችን እና ዲቪዲዎችን ማዘጋጀትና ከቦታ ቦታ ማጓጓዝ ከሚጠይቀው ወጪ በጣም ያነሰ ነው።