የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
በአገሬው ተወላጅ ጎሳዎች ውስጥ ሃይማኖታዊ ነፃነትን ማስከበር
ግንቦት 1, 2021
ላቲን አሜሪካ ውስጥ ከሚኖሩት በመቶ ሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት፣ የራሳቸው ቋንቋና ባሕል ያላቸው ጎሳዎች ናቸው። የእነዚህ ጎሳዎች አባላት የሆኑ ብዙ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች አሉን፤ እነዚህ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ባሕላቸውን ይወዱታል። የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር ሲሉ፣ ከ130 በሚበልጡ የላቲን አሜሪካ አገር በቀል ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እየተረጎሙና እያሰራጩ ነው። a ይሁንና የእነዚህ ጎሳዎች አባላት የሆኑ አንዳንድ ወንድሞቻችን፣ ይሖዋን ለማገልገል በመምረጣቸውና መጽሐፍ ቅዱስ በማይደግፋቸው የአካባቢው ልማዶች ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተነሳ ተቃውሞ አጋጥሟቸዋል። እናንተ የምታደርጉት መዋጮ እነዚህን ወንድሞች ለመርዳት የሚውለው እንዴት ነው?
ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የተደረገ እርዳታ
ሜክሲኮ ውስጥ በሃሊስኮ ግዛት ተራራማ አካባቢ የሚኖሩ የዊቾል ማኅበረሰብ አባላት የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አሉ፤ እነዚህ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚጋጩ ሃይማኖታዊ ልማዶች ላይ ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በአክብሮት ገልጸው ነበር። b ሆኖም ይህ አቋማቸው አንዳንድ የማኅበረሰቡን አባላት አስቆጣ። ታኅሣሥ 4, 2017 በቁጣ የተሞሉ ሰዎች በተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮችና አብረዋቸው ባሉ ሰዎች ላይ ጥቃት ሰነዘሩ። ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ ያስገደዷቸው ከመሆኑም ሌላ ንብረታቸውን አወደሙባቸው፤ እንመለሳለን ብለው ካሰቡም እንደሚገድሏቸው ዛቱባቸው።
በአቅራቢያው ባሉ ከተሞች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ለእነዚህ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለጊዜው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በማሟላት ወዲያውኑ ደረሱላቸው። ሆኖም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለመርዳት ማድረግ የሚቻል ነገር ይኖር ይሆን? አጉስቲን የተባለ ወንድም በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፦ “ጠበቃ ለመቅጠር ገንዘብ አልነበረንም፤ የሕግ ምክር ለመጠየቅም የት መሄድ እንዳለብን የምናውቀው ነገር አልነበረም።”
ጉዳዩ የወንድሞቻችንን የአምልኮ ነፃነት የሚነካ ስለሆነ የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ አፋጣኝ እርምጃ ወሰደ። በመጀመሪያ፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት የተፈጸመውን ወንጀል እንዲያጣሩ ጥያቄ አቀረበ። ቀጥሎም፣ ወንድሞች ከይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አስተባባሪዎች ኮሚቴ ፈቃድ ካገኙ በኋላ በዋናው መሥሪያ ቤት ከሚገኘው የሕግ ክፍል ጋር በመተባበር የዊቾል ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ጉዳይ የሚመለከት የክስ ፋይል ከፈቱ። በኋላም ጉዳዩ ወደ አገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረሰ፤ ይህ ፍርድ ቤት የሜክሲኮ የመጨረሻው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው።
ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ጠበቃዎችን ያቀፈው የሕግ ቡድን፣ ግልጽ የሆነ አንድ የመከራከሪያ ነጥብ አዘጋጀ፤ ይህም ‘የአገሬው ተወላጅ የሆኑ ጎሳዎች፣ ሌሎች ባሕላቸውን እንዲያከብሩላቸው እንደሚጠብቁ ሁሉ እነሱም የራሳቸውን ጎሳ አባላት ነፃነት ሊያከብሩ ይገባል’ የሚል ነው። ሰብዓዊ መብት በየትኛውም ቦታ ሊከበር ይገባል።
ሐምሌ 8, 2020 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በአንድ ድምፅ ለይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ። ከቀያቸው የተባረሩት ወንድሞች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ሊፈቀድላቸው እንደሚገባ ትእዛዝ አስተላለፈ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው አጉስቲን፣ እሱም ሆነ ሌሎች ምን እንደተሰማቸው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ነው የተደሰትነው፤ ወንድሞች ላደረጉልን ነገር በጣም አመስጋኝ ነን። እነሱ ባይረዱን ኖሮ በራሳችን ምንም ነገር ማድረግ አንችልም ነበር።”
‘ጥቂት ለሆኑት ብዙ ማድረግ’
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሳን ሁዋን ዴ ኢሉማን የሚኖሩ ወንድሞቻችን ተመሳሳይ ተቃውሞ አጋጥሟቸው ነበር፤ በኢኳዶር የምትገኘው ይህች መንደር በኦታቫሎ ቫሊ ያሉ በርካታ የአገሬው ተወላጅ ጎሳዎች የሚኖሩባት መንደር ነች። በዚያ ያሉ ወንድሞች፣ አስፈላጊውን የግንባታ ፈቃድ ካገኙ በኋላ በ2014 የስብሰባ አዳራሽ መገንባት ጀመሩ። ይሁንና አንድ ቄስ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን አሰባስቦ በኃይል ግንባታውን እንዲያስቆሙ አደረገ። ከዚያም የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ለአምልኮ እንዳይሰበሰቡ ከለከለ።
በኢኳዶር ቅርንጫፍ ቢሮ ያለው የሕግ ክፍል ከዋናው መሥሪያ ቤት የሕግ ክፍል ጋር በመተባበር፣ የወንድሞችን የአምልኮ ነፃነት ለማስከበር እርምጃ ወሰደ። ወንድሞቻችን፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰዱት። በዚህም የተነሳ የአካባቢው ማኅበረሰብ በወንድሞች ላይ ያለውን ተቃውሞ ለማንሳት እንዲሁም ወንድሞች ስብሰባ ማድረጋቸውንና የጀመሩትን የስብሰባ አዳራሽ መገንባታቸውን እንዲቀጥሉ ለመፍቀድ ተገደደ። ሆኖም ለወደፊትም የወንድሞቻችንን መብት ለማስከበር ሲባል የሕግ ቡድናችን፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ሊያደርጉበት የሚገባ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ አነሳ፤ ይህም ‘የአገሬው ተወላጅ ጎሳዎች፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ማክበር ይጠበቅባቸዋል?’ የሚል ነው።
ሐምሌ 16, 2020 ጉዳዩ ለኢኳዶር ሕገ መንግሥት አጣሪ ፍርድ ቤት ቀረበ፤ ይህ ፍርድ ቤት የአገሪቱ የመጨረሻ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው። በኢኳዶር ያሉ ጠበቃ ወንድሞች ጉባኤውን ወክለው ቀረቡ። ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ፣ ልምድ ያላቸው አራት ጠበቃ ወንድሞቻችንም በችሎቱ ላይ ሐሳብ ሰጥተዋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እገዳ የተነሳ እነዚህ ወንድሞች ሐሳብ የሰጡት ከያሉበት አገር ሆነው በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ነው። በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚወክል የሕግ ቡድን፣ ችሎት ላይ በዚህ መንገድ የመከራከሪያ ሐሳብ እንዲያቀርብ ሲፈቀድለት ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው። c አንድ ሰው የአገሬው ተወላጅ ጎሳ አባል ስለሆነ ብቻ እንደ ማንኛውም ሰው ያሉትን ሰብዓዊ መብቶች ሊነፈግ እንደማይገባ የሕግ ቡድኑ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ጠቅሶ አስረዳ።
በኦታቫሎ ቫሊ ያሉ ወንድሞቻችን የሕገ መንግሥት አጣሪ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። በተደረገላቸው እርዳታ ግን ልባቸው ተነክቷል። በኢሉማን ኪችዋ ጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ሲሳር እንዲህ ብሏል፦ “ጥቂት ለሆኑት ይህን ያህል ብዙ ነገር የሚያደርገው ይሖዋና እሱ የሚጠቀምበት ድርጅት ብቻ ነው።”
በክሱ ሂደት ላይ የተሳተፉት ጠበቆች በሙሉ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው፤ በሙያቸው ወንድሞቻቸውን ያለምንም ክፍያ በማገልገላቸው ደስተኞች ናቸው። በእርግጥ የክስ መዝገብ መክፈት፣ ለክሱ መዘጋጀትና ፍርድ ቤት ቀርቦ መከራከር ጊዜና ገንዘብ እንደሚጠይቅ አይካድም። በሜክሲኮ ከተካሄደው ችሎት ጋር በተያያዘ ጠበቆቻችንና ሌሎች ወንድሞች የመከራከሪያ ሐሳቦቹን ለመዘጋጀት ከ380 የሚበልጡ ሰዓታት አሳልፈዋል፤ ለችሎቱ የሚሆኑ ሰነዶችን ተርጉሞ ማቅረብም ተጨማሪ 240 ሰዓታት ጠይቋል። በኢኳዶር ከተካሄደው ችሎት ጋር በተያያዘ ደግሞ 40 ገደማ የሚሆኑ ጠበቆች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዓታት አሳልፈዋል። ታዲያ የወንድሞቻችንን መብት ለማስከበር ያደረግነው ጥረት የጠየቀውን ወጪ መሸፈን የተቻለው እንዴት ነው? እናንተ donate.pr418.com ላይ ያሉትን የተለያዩ ዘዴዎች ተጠቅማችሁ ባደረጋችሁት መዋጮ ነው። ለልግስናችሁ በጣም እናመሰግናችኋለን!