የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
በኮቪድ-19 ወቅት የስብሰባ አዳራሾችን ማዘጋጀት
ጥቅምት 1, 2022
“የበላይ አካሉ፣ መንግሥት ገደብ ካልጣለ በስተቀር ከሚያዝያ 1 ጀምሮ ሁሉም ጉባኤዎች በአካል ስብሰባ ማድረግ እንዲጀምሩ ለማበረታታት መወሰኑን ስንገልጽላችሁ ደስ ይለናል።” መጋቢት 2022 መጀመሪያ አካባቢ jw.org ላይ የወጣው ይህ ማስታወቂያ በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን እጅግ አስደስቷቸው ነበር። ሆኖም በወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ገና አላበቃም። a ታዲያ ተሰብሳቢዎቹን ከቫይረሱ ለመጠበቅ ምን ዓይነት ማስተካከያዎችና ቁሳቁሶች አስፈልገዋል? ለሁለት ዓመት ያህል በአካል ስብሰባዎችን ካለማድረጋችን አንጻር የስብሰባ አዳራሾቻችን ተሰብሳቢዎችን ለማስተናገድ ብቁ ይሆናሉ?
ወንድሞቻችን በስብሰባ አዳራሾች ውስጥ ስብሰባዎችን በድጋሚ ለማስጀመር ለበርካታ ወራት ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የተለያዩ ችግሮች፣ የተለያዩ መፍትሔዎች
በ2020 በአካል ስብሰባ ማድረግ ካቆምን ከአንድ ወር በኋላ በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው ዓለም አቀፍ ንድፍና ግንባታ ዲፓርትመንት ኮቪድ-19 የስብሰባ አዳራሾቻችንን በምንጠቀምበት መንገድ ላይ ምን ለውጥ እንደሚያመጣ እንዲሁም የስብሰባ አዳራሾቻችን ኮቪድ-19ን ለመከላከል አመቺ እንዲሆኑ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ማጤን ጀመረ።
ብዙውን ጊዜ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚያስፈልጉት ነገሮች ከሌላው አካባቢ የተለዩ ናቸው። በዓለም አቀፍ ንድፍና ግንባታ ዲፓርትመንት የሚያገለግለው ማቲው ደ ሳንክቲስ እንዲህ ብሏል፦ “በአንዳንድ አገሮች ያለው ችግር የእጅ መታጠቢያ ቁሳቁሶች እጥረት ነው። የስብሰባ አዳራሾች የቧንቧ ውኃ ከሌላቸው ውኃ መግዛት ወይም በአካባቢው ከሚገኝ ወንዝ ወይም ጉድጓድ ቀድቶ ማምጣት ያስፈልጋል። በሌሎች አገሮች ደግሞ አንዳንድ መንግሥታት ከአየር ማቀዝቀዣ መሣሪያዎች፣ አዳራሾችን ከማናፈስ እንዲሁም ስለ ጤናና ስለ ንጽሕና የሚገልጹ ምልክቶችን ከመስቀል ጋር በተያያዘ አዲስ መመሪያ አውጥተዋል።”
ወንድሞቻችን እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች የተወጡት እንዴት ነው? ማቲው ለበርካታ የስብሰባ አዳራሾች “ቀላልና ብዙ ወጪ የማያስወጡ ውጤታማ መፍትሔዎችን” ማግኘት እንደተቻለ ገልጿል። ለምሳሌ በፓፑዋ ኒው ጊኒ 20 ሊትር በሚይዙ የፕላስቲክ ባልዲዎች ላይ ቧንቧ በመግጠም የእጅ መታጠቢያ ቦታዎችን ማዘጋጀት ተችሏል። በዚህ መንገድ በገጠራማ አካባቢዎች በሚገኙ የስብሰባ አዳራሾች የእጅ መታጠቢያ ቦታዎችን ለማዘጋጀት የሚያስፈልገው 40 የአሜሪካ ዶላር ብቻ ነው። በአፍሪካ ለሚገኙ የስብሰባ አዳራሾች በእስያ ከሚገኝ አንድ ድርጅት ከ6,000 የሚበልጡ ጥራት ያላቸው የእጅ መታጠቢያዎችን ገዝተናል።
ከተደረጉት ሌሎች ዝግጅቶች መካከል የስብሰባ አዳራሾች በደንብ እንዲናፈሱ ሲባል ፋኖችንና የአየር ማስተላለፊያ መሣሪያዎችን መግጠምና ማስተካከል ይገኙበታል። ብዙ ጉባኤዎች የማይክሮፎን መቀባበልን ለማስቀረት ሲሉ ረጃጅም የማይክሮፎን ዘንጎችን ገዝተዋል። ቫይረሱን ሊያስተላልፉ በሚችሉ እንደ በር እጀታና የቧንቧ መክፈቻ ባሉ ቦታዎች ላይ ንክኪን ለመቀነስ እንዲሁም እነዚህን ቦታዎች አዘውትሮ በኬሚካል ለማጽዳት ጥረት ተደርጓል። አንዳንድ ጉባኤዎች በመጸዳጃ ቤቶቻቸው ውስጥ በእጅ ሳይነኩ የሚከፈቱ ቧንቧዎችን ገጥመዋል። ቺሊ ውስጥ ለእያንዳንዱ የስብሰባ አዳራሽ አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ በአማካይ 1,400 የአሜሪካ ዶላር ፈጅቷል።
ወንድሞቻችን በዋነኝነት ትኩረት ያደረጉት አዳራሾቹ ኮቪድ-19ን ለመከላከል አመቺ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ቢሆንም በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ ለመቆጠብም ጥረት አድርገዋል። ለምሳሌ በአንዳንድ አገሮች መንግሥት የእጅ መታጠቢያዎችና የማይክሮፎን ዘንጎች ከቀረጥ ነፃ እንዲሆኑ ባደረገው ዝግጅት ተጠቅመዋል። ቅርንጫፍ ቢሮዎች እርስ በርስ በመተባበር ቁሳቁሶችን በጅምላ በመግዛት ወጪ ለመቆጠብ ጥረት አድርገዋል። ቅርንጫፍ ቢሮዎችና ዓለም አቀፉ የዕቃ ግዢ ዲፓርትመንት ብዙውን ጊዜ ቁሳቁሶችን ከአምራቾች በቀጥታ ለመግዛት ጥረት ያደርግ ነበር፤ ይህም ወጪ ለመቆጠብ ብቻ ሳይሆን ቁሳቁሶቹን ለማድረስ የሚያስፈልገውን ጊዜ ለመቀነስም አስችሏል።
“ከስጋት ነፃ እንድሆን ረድቶኛል”
የስብሰባ አዳራሾች ኮቪድ-19ን ለመከላከል አመቺ እንዲሆኑ የተደረገው ጥረት በስብሰባዎች ላይ በአካል የሚገኙትን ሰዎች ከጉዳት ለመጠበቅና ስጋት እንዳይሰማቸው ለማድረግ አስችሏል። በፔሩ የምትኖር ዱልሲኔ የተባለች እህት ወደ ስብሰባ አዳራሽ እንደምንመለስ ስትሰማ ‘ስጋት አድሮባት’ እንደነበር በሐቀኝነት ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ “ወረርሽኙ ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ ኮቪድ-19 ይዞኝ ነበር። ስለዚህ ለቫይረሱ ድጋሚ ልጋለጥ እንደምችል ስለተሰማኝ ወደ ስብሰባ አዳራሽ መሄድ አስፈርቶኝ ነበር። ወደ ስብሰባ አዳራሹ ስደርስ ግን ሽማግሌዎች በርካታ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንደወሰዱ ተመለከትኩ፤ ለምሳሌ የእጅ ማጽጃ መሣሪያዎችንና የማይክሮፎን ዘንጎችን አዘጋጅተው እንዲሁም ከእያንዳንዱ ስብሰባ በፊትና በኋላ አዳራሹን በኬሚካል ለማጽዳት ዝግጅት አድርገው ነበር። ይህን ሁሉ ማየቴ ከስጋት ነፃ እንድሆን ረድቶኛል።” b
ሣራ የተባለች በዛምቢያ የምትኖር እህት ደግሞ ለየት ያለ ፈተና አጋጥሟታል። እንዲህ ብላለች፦ “ከተወሰኑ ወራት በፊት ባለቤቴ በኮቪድ-19 ሞተ። ስለዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለቤቴ በሌለበት በአካል በስብሰባ ላይ ስገኝ ምን ይሰማኝ ይሆን የሚለው አሳስቦኝ ነበር።” ታዲያ በስብሰባ ላይ ከተገኘች በኋላ ምን ተሰማት? እንዲህ ብላለች፦ “በስብሰባዎች ላይ በአካል መገኘት መቻላችን በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ይሖዋ አብሮን እንዳለ አረጋግጦልኛል። አሁን ከበፊቱ ይበልጥ የሽማግሌዎችን እንዲሁም የወንድሞችንና የእህቶችን ማበረታቻ፣ ፍቅርና ድጋፍ ማጣጣም ችያለሁ።”
በዓለም ዙሪያ ያሉ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ወደ ስብሰባ አዳራሽ መመለስ በመቻላቸው አመስጋኝ ናቸው። በልግስና ለምታደርጉት መዋጮ እናመሰግናለን። ብዙዎቻችሁ መዋጮ ያደረጋችሁት በdonate.pr418.com አማካኝነት ነው። ያደረጋችሁት መዋጮ የንጹሕ አምልኮ ማዕከሎቻችን አመቺና አንድ ላይ ለመሰብሰብ ስጋት የማይፈጥሩ ቦታዎች እንዲሆኑ ለማድረግ አስችሎናል።