የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
ተአማኒነት ያለውና እምነት የሚያጠናክር ዜና
ታኅሣሥ 1, 2021
የይሖዋ ምሥክሮች የእምነት አጋሮቻቸው ያሉበት ሁኔታ በጣም ያሳስባቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:17) ብዙዎቻችን በኬንያ የምትኖረውን ታኒስ የተባለችውን እህት ስሜት እንጋራለን። “በዓለም ዙሪያ ያሉት ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እፈልጋለሁ” ብላለች። ታዲያ ታኒስን ጨምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ወቅታዊ መረጃ የሚያገኙት ከየት ነው? ከ2013 አንስቶ jw.org በተባለው ድረ ገጻችን ላይ ባለው የዜና ዓምዳችን አማካኝነት መረጃ ስናስተላልፍ ቆይተናል።
የዜና ዓምዳችን፣ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚመለከቱ ተአማኒነት ያላቸው ዘገባዎችን ይዞ ይወጣል፤ ለምሳሌ፣ አዲስ ስለወጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ የአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራዎች፣ የግንባታ ፕሮጀክቶችና ሌሎች ወሳኝ ክንውኖች ይዘግባል። በእምነታቸው ምክንያት ስለታሰሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም መረጃ ይሰጠናል። በተጨማሪም በዜና ዓምዳችን ላይ ከስብከት ዘመቻዎችና ከመታሰቢያው በዓል ጋር የተያያዙ አበረታች ሪፖርቶች ይወጣሉ። ታዲያ እነዚህን የዜና ዘገባዎች የሚያዘጋጃቸው ማን ነው? የሚዘጋጁትስ እንዴት ነው?
ለዜና የሚሆኑ ክንውኖችን መለየትና መዘገብ
የዜና ዓምዳችንን በበላይነት የሚከታተለው በዋናው መሥሪያ ቤት የሚገኘው የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ነው። ይህ ዲፓርትመንት የሚሠራው በበላይ አካሉ የአስተባባሪዎች ኮሚቴ አመራር ሥር ሆኖ ነው። የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ፣ ከ100 በላይ ወንድሞችንና እህቶችን ያቀፈ ነው፤ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ የርቀት ፈቃደኛ ሠራተኞች ናቸው። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ጸሐፊዎች፣ መረጃ አጣሪዎች፣ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎችና ተርጓሚዎች ሆነው ያገለግላሉ። የአንዳንዶቹ ሥራ ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ ምሁራንን እና የሚዲያ ሰዎችን ማነጋገር ነው። በዓለም ዙሪያ ባሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚገኙ ከ80 የሚበልጡ የሕዝብ ግንኙነት ዴስኮች ለዚህ ዲፓርትመንት እገዛ ያበረክታሉ።
የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ፣ አንድ ዜና ከማዘጋጀቱ በፊት በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ካሉት የሕዝብ ግንኙነት ዴስኮች ጋር ይነጋገራል። ወንድሞቻችን፣ ዜና ሊሆን የሚችል አንድ ክንውን ከለዩ በኋላ ስለ ጉዳዩ ምርምር ያደርጋሉ እንዲሁም ተአማኒነት ያላቸው መረጃዎችን ያጠናቅራሉ። ይህም ቃለ መጠይቆችን ማድረግንና ባለሙያዎችን ማነጋገርን ሊጨምር ይችላል። መረጃዎቹ ከተጠናቀሩ በኋላ የዜና ዘገባው ይጻፋል፤ የአርትኦት ሥራና ማጣሪያ ንባብ ይደረግለታል፤ ፎቶዎች ይካተቱበታል፤ ከዚያም ፈቃድ እንዲያገኝ ወደ አስተባባሪዎች ኮሚቴ ይላካል።
የአድናቆት መልእክቶች
የእምነት አጋሮቻችን ስለ ዜና ዓምዱ ምን ይሰማቸዋል? በፊሊፒንስ የምትኖር ሼረል የተባለች እህት “ቀኔን ስለ ይሖዋ ድርጅትና ስለ ሕዝቦቹ የሚገልጽ ዜና በማንበብ ስጀምር ደስ ይለኛል” ብላለች።
ብዙ አንባቢዎች በjw.org ላይ የሚገኘው የዜና ዓምድ ከሌሎች የዜና ሚዲያዎች በጣም እንደሚለይ አስተውለዋል። በካዛክስታን የምትኖረው ታቲያና እንዲህ ብላለች፦ “jw.org ላይ የሚወጣው ዜና ልተማመንበት የምችል መሆኑ ያስደስተኛል። የዜና ዘገባዎቹ እምነት የሚጣልባቸውና ትክክለኛ ናቸው።” በሜክሲኮ የምትኖር አልማ የተባለች እህት “በሌሎች የዜና ሚዲያዎች ላይ ከሚገኘው የሚያሸብር ዜና በተቃራኒ jw.org ላይ የሚወጡ ዜናዎችን ማንበብ በጣም ያበረታታኛል” ብላለች።
የዜና ዓምዳችን እምነት የሚጣልበት ብቻ ሳይሆን እምነት የሚያጠናክርም ነው። በኬንያ የሚኖረው በርናርድ እንዲህ ብሏል፦ “የዜና ዓምዱ በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞቼንና እህቶቼን እንደ ቤተሰቤ እንዳያቸው ረድቶኛል፤ የሚኖሩት የትም ይሁን የት። አሁን በጸሎቴ ላይ ስማቸውንና ያሉበትን ሁኔታ ለይቼ መጥቀስ እችላለሁ።” በኬንያ የምትኖር ባይብሮን የተባለች እህትም እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስ በአዲስ ቋንቋ እንደወጣ የሚገልጽ ዜና ሳነብ ሁሌም በጣም ደስ ይለኛል! እነዚህን የዜና ዘገባዎች ሳነብ ‘ይሖዋ እንዴት ያለ የማያዳላ አምላክ ነው!’ ብዬ አስባለሁ።”
ስደት እየደረሰባቸው ስላሉ ወንድሞች የሚገልጹ ዜናዎችን ማንበብም እንኳ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። በኬንያ የምትኖረው ጃክሊን እንዲህ ብላለች፦ “ስለ ድፍረታቸው ሳስብ እኔ ራሴ እምነቴ ይጠናከራል። ታሪካቸውን ሳነብ ‘እንዲጸኑ የረዳቸው ምንድን ነው?’ ብዬ አስባለሁ። ቀላል ብለን የምናስባቸው ነገሮች፣ ለምሳሌ ጸሎት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፣ ሌላው ቀርቶ መዘመር እንኳ ምን ያህል እንዳጠናከራቸው አስተውያለሁ።”
በኮስታ ሪካ የምትኖረው ቢያትሪስ ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር በተያያዘ የሚወጡት ዜናዎች ያስደንቋታል። እንዲህ ብላለች፦ “የዜና ዓምዱ፣ ድርጅታችን ችግር ላይ ለወደቁ ወንድሞቻችን እርዳታ የሚያደርግበት መንገድ ፈጣን፣ ውጤታማና ፍቅር የሚንጸባረቅበት እንደሆነ እንድገነዘብ ረድቶኛል። ‘ይህ በእርግጥም ይሖዋ የሚመራው ድርጅት ነው’ እንድል አድርጎኛል።”
በዓለም ዙሪያ ስላሉ ወንድሞቻችን ወቅታዊ መረጃ ማግኘት በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነን! ይህ ሊሳካ የቻለው እናንተ ለዓለም አቀፉ ሥራ በምታደርጉት መዋጮ ነው፤ ብዙዎች መዋጮ የሚያደርጉት donate.pr418.comን ተጠቅመው ነው። ለምታደርጉት መዋጮ ከልብ እናመሰግናችኋለን!