በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

ታላቁን አስተማሪያችንን የሚያስከብሩ ሕንፃዎች

ታላቁን አስተማሪያችንን የሚያስከብሩ ሕንፃዎች

ሐምሌ 1, 2023

 ይሖዋ ሕዝቡን ማስተማር ይወዳል። በዚህም የተነሳ ድርጅቱ ተማሪዎች የአገልግሎት ምድባቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲወጡ የሚረዱ የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን አቋቁሟል። ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች አንዱ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት (SKE) ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአምላክ ድርጅት ለትምህርት ሥርዓቱ ብቻ ሳይሆን ትምህርቱ ለሚሰጥባቸው ሕንፃዎችም ትኩረት መስጠት ጀምሯል። የዚህ ዋነኛ ዓላማ ለተማሪዎችም ሆነ ለአስተማሪዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው። የምታደርጉት መዋጮ ይህን ዓላማ ለማሳካት እየረዳ ያለው እንዴት ነው?

ተጨማሪ ተማሪዎችና ምቹ የትምህርት ቦታዎች

 ለበርካታ ዓመታት ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች የሚካሄዱት በጉባኤ ስብሰባ አዳራሾችና በትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች ነበር። ታዲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች ብቻ የሚውሉ ተጨማሪ ሕንፃዎችን እየገነባን ወይም እያደስን ያለነው ለምንድን ነው? ሦስት ምክንያቶችን እንመልከት።

 ተጨማሪ የሰው ኃይል ማስፈለጉ። የበላይ አካሉ የአገልግሎት ኮሚቴ ረዳት የሆነው ክሪስቶፈር ሜቨር “ቅርንጫፍ ቢሮዎች በመስክ ላይ የሚያገለግሉ ተጨማሪ ወንድሞችና እህቶች እንደሚያስፈልጓቸው ሪፖርት እያደረጉ ነው” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ለምሳሌ የብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ በ2019 ሪፖርት እንዳደረገው፣ በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ የሚያገለግሉ 7,600 ገደማ የሚሆኑ ተጨማሪ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተመራቂዎች ያስፈልጋሉ።” የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮም በልዩ የአደባባይ ምሥክርነት፣ በወደብ ምሥክርነትና በእስር ቤት በሚሰጠው ምሥክርነት ሌሎችን ሊያሠለጥኑ የሚችሉ ብቃት ያላቸው አቅኚዎች በእጅጉ እንደሚያስፈልጉ ሪፖርት አድርጓል። በተጨማሪም በአካባቢ ንድፍና ግንባታ እንዲሁም በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞች ያስፈልጋሉ። የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተመራቂዎች፣ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት ያግዛሉ።

 የአመልካቾች ቁጥር መጨመሩ። በብዙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የአመልካቾቹ ቁጥር ትምህርት ቤቶቹ መቀበል ከሚችሉት በላይ ነው። ለምሳሌ በብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 2,500 ገደማ የሚሆኑ አመልካቾች ነበሩ። ሆኖም ትምህርት ቤቶቹ በቂ ቦታ ስላልነበራቸው መቀበል የቻሉት 950 ተማሪዎችን ብቻ ነው።

 ምቹ ማረፊያ ማስፈለጉ። ትምህርት ቤቱ በጉባኤ ስብሰባ አዳራሾች ወይም በትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች ሲካሄድ በአብዛኛው ተማሪዎቹ የሚያርፉት በአካባቢው ባሉ ወንድሞችና እህቶች ቤት ነው። በየዓመቱ ጥቂት ትምህርት ቤቶች ብቻ በሚካሄዱባቸው አገሮች ይህ ዝግጅት ችግር ላይኖረው ይችላል። ትምህርት ቤቶቹ በዓመት ውስጥ በተደጋጋሚ የሚካሄዱ ከሆነ ግን የአካባቢው አስፋፊዎች ተማሪዎቹን በእንግድነት መቀበል ይከብዳቸዋል። ስለዚህ ትምህርቱ ለሚሰጥበት ቦታ ቅርብ የሆኑና ተማሪዎችን ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጁ ሕንፃዎችን መገንባት አስፈልጓል።

 የመማሪያ ክፍሉን፣ የአስተማሪዎችንና 30 ገደማ የሚሆኑ ተማሪዎችን መኖሪያ ክፍሎች እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች የያዘ አንድ ሕንፃ ለመገንባት እንደየአካባቢው ሁኔታ ሊለያይ ቢችልም በአማካይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል።

የትምህርት ቤት ሕንፃዎቹ ምን ዓይነት ናቸው?

 ትምህርት ቤቶቹ በአብዛኛው የሚገነቡት ከትላልቅ ከተሞች ወጣ ብለው ባሉ ሆኖም ለትራንስፖርት አመቺ በሆኑ ጸጥ ያሉ አካባቢዎች ነው። ለትምህርት ቤቱ የተለያዩ አገግሎቶችን በመስጠት እንዲሁም ሕንፃዎችንና መሣሪያዎችን በመጠገን ሊያግዙ የሚችሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አስፋፊዎች ያሉባቸው አካባቢዎች ተመራጭ ናቸው።

 በሕንፃዎቹ ውስጥ ቤተ መጻሕፍቶች፣ የማጥኛ ቦታዎች፣ ኮምፒውተሮች፣ ፕሪንተሮችና ሌሎች መሣሪያዎች እንዲኖሩ ይደረጋል። በአብዛኛው ተማሪዎችና አስተማሪዎች አብረው ሊመገቡ የሚችሉባቸው የመመገቢያ አዳራሾች ይኖራሉ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግና ዘና ለማለት የሚያመች በቂ ቦታ እንዲኖርም ይደረጋል።

 የመማሪያ ክፍሉም ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል። በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ ባለው ዓለም አቀፍ ንድፍና ግንባታ ዲፓርትመንት የሚሠራ ትሮይ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የመማር ማስተማር ሂደቱን ምቹ የሚያደርግ የመማሪያ ክፍል ንድፍ ለማውጣት እንድንችል የቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶችን የሚከታተለውን ክፍል አማክረናል።” አክሎም “በዚያ የሚሠሩት ወንድሞች ከመማሪያ ክፍሎቹ ስፋት፣ አቀማመጥና ብርሃን እንዲሁም ከሚያስፈልጓቸው የኦዲዮ/ቪዲዮ መሣሪያዎች ጋር የተያያዙ መመሪያዎችን ሰጡን” ብሏል። በሃንጋሪ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆነው ዞልታን የድምፅ መሣሪያዎች እንዲቀርቡ መደረጉ ስላስገኘው ጥቅም ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ላይ የድምፅ ማጉያ መሣሪያዎች ስላልነበሩን ተማሪዎቹ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲመልሱ ደጋግመን ማስታወስ ያስፈልገን ነበር። አሁን ግን በእያንዳንዱ ጠረጴዛ ላይ የድምፅ ማጉያ መሣሪያ ስላለ ችግሩ ተፈቷል!”

“የይሖዋ ልዩ እንግዶች”

 የሕንፃዎቹ ንድፍ መሻሻሉ በተማሪዎችና በአስተማሪዎች ላይ ምን ውጤት አስገኝቷል? በፓልም ኮስት፣ ፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት የተካፈለችው አንጄላ “በጣም ሰላማዊ ቦታ ነው” በማለት ተናግራለች። አክላም “የምንማርበትንና የምኖርበትን ክፍል ጨምሮ እያንዳንዱ ነገር፣ ትኩረታችን ሳይከፋፈል ማጥናትና መማር እንድንችል ለመርዳት ታስቦ በጥንቃቄ የተዘጋጀ ነው” ብላለች። በሃንጋሪ የትምህርት ቤቱ አስተማሪ ሆኖ የሚያገለግል ቻባ የተባለ ወንድምም ከተማሪዎች ጋር አብሮ መመገብ በመቻሉ በጣም ደስተኛ ነው። እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ስለሚያስገኙት ጥቅም ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ጊዜ ተማሪዎቹ ስላጋጠማቸው ነገር በነፃነት ይነግሩናል። ይህም በደንብ እንድናውቃቸው ረድቶናል። በመሆኑም ትምህርቱን የእነሱን ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ ማቅረብ ችለናል።”

 ተማሪዎቹና አስተማሪዎቹ የትምህርት ሕንፃዎቹ በተሻለ ሁኔታ መገንባታቸው ‘የታላቁ አስተማሪ’ የይሖዋ በረከት እንደሆነ ይሰማቸዋል። (ኢሳይያስ 30:20, 21) ወደ ትምህርት ቤት በተቀየረ ሕንፃ ውስጥ በተካሄደ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት የተካፈለች በፊሊፒንስ የምትኖር አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ትምህርት ቤቱ የተካሄደበት ቦታ እንዲሁ ተማሪዎች ብቻ ሳንሆን የይሖዋ ልዩ እንግዶች እንደሆንን አስታውሶናል። እሱ ደስተኛ ሆነን ቃሉን በሚገባ እንድናጠና ይፈልጋል።”

 እንዲህ ያሉ የትምህርት ቤት ሕንፃዎች ሊገነቡ፣ ሊታደሱና ጥገና ሊደረግላቸው የቻሉት እናንተ በምታደርጉት መዋጮ የተነሳ ነው። ከእነዚህ መዋጮዎች መካከል አብዛኞቹ የሚደረጉት በ​donate.pr418.com አማካኝነት ነው። ለልግስናችሁ ከልብ እናመሰግናለን።

በፓልም ኮስት፣ ፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ያለው የትምህርት ቤት ሕንፃ መግቢያ

በኢየሱስ ዘመን የነበረው ቤተ መቅደስ ሞዴል፣ የትምህርት ቤቱ የእንግዳ መቀበያ፣ ፓልም ኮስት፣ ፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት የሚካፈሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቱ ሲገቡ፣ ብራዚል

ተማሪዎች እየተማሩ፣ ብራዚል

በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት የሚካፈሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቱ ሲገቡ፣ ፊሊፒንስ

በትምህርት ቤቱ የመመገቢያ አዳራሽ አብረው ሲመገቡ፣ ፊሊፒንስ