በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

ትላልቅ ስብሰባዎችን ‘መስማትና ማየት’

ትላልቅ ስብሰባዎችን ‘መስማትና ማየት’

ሐምሌ 1, 2024

 በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ዓመታዊ ስብሰባዎችን ማድረግ ከጀመሩ 130 ዓመት አልፏቸዋል። እነዚህ ስብሰባዎች በአሁኑ ወቅት ከ40 በላይ ንግግሮችን፣ ሙዚቃ፣ ቃለ መጠየቆችንና ቪዲዮዎችን ያካተቱ ናቸው። ተሰብሳቢዎቹ ከፕሮግራሙ እንዲጠቀሙና ለተግባር እንዲነሳሱ ከተፈለገ ግን በጥራት ‘መሰማትና መታየት’ አለበት። (ሉቃስ 2:20) በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ከእነዚህ ትላልቅ ስብሰባዎች መጠቀም እንዲችሉ፣ የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

እያንዳንዱን የስብሰባ ቦታ ከግምት ያስገባ የኦዲዮ ቪዲዮ አገልግሎት

 በምዕራባውያን አገሮች ያሉት ብዙዎቹ ስታዲየሞችና መሰብሰቢያ ቦታዎች የራሳቸው የድምፅና የቪዲዮ መሣሪያዎች አሏቸው። ታዲያ እንዲህ ያሉ የስብሰባ ቦታዎችን ስንከራይ ብዙውን ጊዜ የራሳችንን መሣሪያዎች የምንጠቀመው ለምንድን ነው? በዋናው መሥሪያ ቤት ብሮድካስቲንግ ዲፓርትመንት የሚሠራው ዴቪድ እንዲህ ብሏል፦ “ከምንከራያቸው ቦታዎች አብዛኞቹ፣ ታዳሚዎች ከስድስት ሰዓት በላይ በንግግር የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን እንዲያዳምጡባቸው ታስበው የተዘጋጁ አይደሉም። ለምሳሌ ያህል፣ ስፖርታዊ ውድድር የሚካሄድባቸው ቦታዎች የድምፅ መሣሪያዎቻቸውን በዋነኝነት የሚጠቀሙት አጫጭር ማስታወቂያዎችን ለማስተላለፍና የተቀነጨቡ ሙዚቃዎችን ለማስደመጥ ነው። የቪዲዮ ስክሪኖቻቸው የሚያሳዩት የውድድር ውጤቶችን፣ ማስታወቂያዎችንና ድጋሚ የሚታዩ የጨዋታ ክሊፖችን ነው። በእኛ ስብሰባዎች ላይ ግን ረዘም ያሉ ቪዲዮዎችን ለተሰብሳቢዎች እናሳያለን፤ እንዲሁም ከመድረክ የሚተላለፈው እያንዳንዱ ቃል በጥራት እንዲሰማ እንፈልጋለን።”

 የኦዲዮ ቪዲዮ መሣሪያዎችን የምንገጥመው የስብሰባው ቦታውን ከግምት አስገብተን ነው፤ ምክንያቱም አንዱ መሰብሰቢያ ከሌላው ይለያል። ስብሰባዎቹ የሚካሄዱባቸው ቦታዎች እንደተመረጡ በየቅርንጫፍ ቢሮዎቹ ውስጥ የሚገኙት የብሮድካስቲንግ ዲፓርትመንቶች የተሰብሳቢዎቹን ብዛትና የቦታውን የመያዝ አቅም ከግምት በማስገባት ተሰብሳቢዎቹ የሚቀመጡበትን ቦታ ይወስናሉ። ከዚያም ወንድሞች የድምፅ መሣሪያዎቹንና የቪዲዮ ስክሪኖቹን የት የት እንደሚያስቀምጡ ያሰላሉ፤ መሣሪያዎቹን እንዴት እንደሚያስተሳስሩ ይወስናሉ፤ እንዲሁም የሚያስፈልጓቸውን መሣሪያዎች ዝርዝር ያዘጋጃሉ። ይህ የሚደረግበት ዓላማ በስብሰባው ላይ የሚገኝ ሁሉም ሰው ፕሮግራሙን በጥራት ማየትና መስማት እንዲችል ነው።

በአካባቢ ብሮድካስቲንግ ዲፓርትመንት የሚሠሩ ወንድሞች በጥንቃቄ የተነደፈ ፕላን ሲከተሉ

 ፕሮግራሙ በብዙ ቋንቋዎች በሚተላለፍባቸው ስብሰባዎች ላይ ይህ ሥራ ይበልጥ ውስብስብ ይሆናል። ፕሮግራሙ ወደ ሌላ ቋንቋ የሚተረጎም ከሆነ በመጀመሪያ ድምፅና ምስል ለተርጓሚዎቹ መተላለፍ አለበት፤ ከዚያ ደግሞ ትርጉማቸው፣ ቋንቋውን ለሚሰሙት ሰዎች በሌላ የሬዲዮ መስመር ይተላለፋል። ለየት ያሉ የሚዲያ ማጫወቻዎች ስላሉን ሁሉም ተሰብሳቢዎች ተመሳሳይ ቪዲዮ እየተመለከቱ ፕሮግራሙን በስምንት የተለያዩ ቋንቋዎች በድምፅ ማስተላለፍ እንችላለን። ዴቪድ እንደተናገረው “ይህ ሥራ በጣም ውስብስብ ነው፤ በሥራው የሚካፈሉ ፈቃደኛ ሠራተኞችም ብዙ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል።”

 አብዛኞቹ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በየዓመቱ የሚጠቀሙበት የድምፅና የቪዲዮ መሣሪያ አላቸው። ስለዚህ ወንድሞች መሣሪያዎቹ ከአንዱ የስብሰባ ቦታ ወደ ሌላው የሚጓጓዙበትን መንገድ ያመቻቻሉ። የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ብቻ እንኳ ለትላልቅ ስብሰባ ጥቅም ላይ የሚውሉ መሣሪያዎችን ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ በየዓመቱ ከ200,000 የአሜሪካ ዶላር በላይ ያወጣል። ሆኖም ይህ ተጨማሪ መሣሪያዎችን ለመግዛትና ለጥገና ከሚወጣው ወጪ በእጅጉ ያንሳል። በካናዳ በተካሄደ ትልቅ ስብሰባ ላይ የኦዲዮ ቪዲዮ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሠራው ስቲቨን እንዲህ ብሏል፦ “የእኛ የኦዲዮ ቪዲዮ ቡድን አንድም ብሎን፣ መፍቻ፣ ገመድና መሣሪያ ከቁጥር እንዳይጎድል፣ በጥንቃቄ እንዲያዝ በኋላም በተገቢው መንገድ ታሽጎ ወደ ቀጣዩ ስብሰባ እንዲላክ ጥረት አድርጓል።”

መሣሪያዎችን መግዛትና በአግባቡ መያዝ

 የድምፅና የቪዲዮ መሣሪያዎችን መከራየት በጣም ውድ ነው፤ ብዙውን ጊዜ ደግሞ መሣሪያዎቹ ጥራታቸውን የጠበቁና በአግባቡ የተያዙ አይደሉም። በዚህም ምክንያት በጥቅሉ የምንመርጠው የሚያስፈልገንን መሣሪያ መግዛት ነው። አምስት ሜትር በሦስት ሜትር የሆነ LED የቪዲዮ ማሳያ በአሁኑ ወቅት 24,000 ዶላር ነው፤ አንድ የአሥራ አምስት ሜትር የማይክሮፎን ገመድ እንኳ 20 ዶላር ያወጣል። በመሆኑም ብሮድካስቲንግ ዲፓርትመንት አንድም መሣሪያ ከመግዛቱ በፊት ከዕቃ ግዢ ክፍል ጋር በመነጋገር ‘ወጪውን ያሰላል።’ (ሉቃስ 14:28) ለምሳሌ ያህል፣ ይህ መሣሪያ ቢገዛ ምን ያህል ሰዎች ይጠቀማሉ? መሣሪያውን ከመግዛት የተሻለ አማራጭ ይኖር ይሆን? መሣሪያውን ለማስቀመጥ በቂ ቦታ አለን? ለመሣሪያው ክትትል ለማድረግ በቂ ዕቃዎችና የሠለጠኑ ፈቃደኛ ሠራተኞችስ አሉን?

 በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ ለመቆጠብ ስንል ለኦዲዮ ቪዲዮ መሣሪያዎቹ አዘውትረን ጥገና በማድረግ የአገልግሎት ዘመናቸውን ለማርዘም ጥረት እናደርጋለን። መሣሪያዎቹን የምናጓጉዘው ደግሞ እንግልት በሚችሉ ማስቀመጫዎች ነው፤ እነዚህ ማስቀመጫዎችም እንደ አስፈላጊነቱ ጥገና ይደረግላቸዋል።

የድምፅና የቪዲዮ መሣሪያዎችን መጠገን ዕድሜያቸው እንዲረዝም ይረዳል

ግሩም ምሥክርነት እና ጥራቱን የጠበቀ ፕሮግራም

 በስብሰባዎቻችን ላይ ያለው የድምፅና የቪዲዮ ጥራት የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችን ያስደንቃቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ከዓለማችን ትላልቅ የብሮድካስቲንግ ኩባንያዎች የአንዱ ተቀጣሪ የሆነ ሰው የፕሮግራሙ ይዘትና የሚተላለፍበት ጥራት እንዳስደነቀው ተናግሯል። በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የኦዲዮ ቪዲዮ መሣሪያዎችን በመግጠምና በማጫወት ሥራ የሚያግዘው ጆናታን የዚህን ሰው ስሜት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ ሥራ የምንካፈለው ሁሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች እንጂ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዳልሆንን ሲያውቅ በጣም ተገረመ። እኛ በአንድ ቀን ተኩል የገጣጠምነውን ነገር የእሱ ኩባንያ ሰዎች አምስት ቀን እንደሚፈጅባቸው ተናገረ።” በሌላ ትልቅ ስብሰባ ላይ ደግሞ የስብሰባ ቦታው የሥራ ኃላፊ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ የሙዚቃና የቪዲዮ ባለሙያዎች እዚህ ሠርተው ያውቃሉ፤ እንዲህ ያለ የሥራ ባሕልና የካበተ ልምድ ግን አላየሁም።”

ወንድሞችና እህቶች ፕሮግራሙን በጥሞና ሲከታተሉ

 አንተስ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ካለው ጥራቱን የጠበቀ የኦዲዮ ቪዲዮ አገልግሎት ተጠቅመሃል? በእንግሊዝ እንዳለው እንደ ዴቪድ ይሰማህ ይሆናል፤ እንዲህ ብሏል፦ “88 ዓመቴ ነው፤ ዕድሜዬን በሙሉ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ስገኝ ኖሬያለሁ። ትኩረቴን ሰብስቤ ፕሮግራሙን መከታተል ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቀላል ሆኖልኛል። ግሩም ለሆኑት ቪዲዮዎች ምስጋና ይግባቸውና ፕሮግራሙ ሳላስበው ነው የሚያልቀው፤ ትምህርቱም ይበልጥ ግልጽና ፍሰቱን የጠበቀ ነው።” በናይጄሪያ የሚኖረው ሚካኤል እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች አሁን እንደ በፊቱ ተናጋሪውን መስማት ወይም ቪዲዮዎቹን መመልከት ትግል ስለማይሆንባቸው ትምህርቱን በትኩረትና ሳይሰላቹ ይከታተላሉ።”

 በዚህ ዓመት ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ በሚል ጭብጥ በሚካሄደው የክልል ወይም ልዩ የክልል ስብሰባ ላይ ስትገኙ፣ ተሰብሳቢዎች ፕሮግራሙን መስማትና ማየት እንዲችሉ ምን ያህል እንደሚለፋ ለማሰብ ሞክሩ። ይህ እውን ሊሆን የቻለው በ​donate.pr418.com እና በሌሎች መንገዶች በምታደርጉት መዋጮ ነው። ከልብ እናመሰግናለን!