በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

አደጋ ለደረሰባቸው እርዳታ ማበርከት

አደጋ ለደረሰባቸው እርዳታ ማበርከት

የካቲት 1, 2021

 በ2020 በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች ከመድረሳቸውም በተጨማሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመላው ዓለም ተከስቶ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች አደጋ ለደረሰባቸው ሰዎች እርዳታ ያበረከቱት እንዴት ነው?

 የበላይ አካሉ የአስተባባሪዎች ኮሚቴ በ2020 የአገልግሎት ዓመት a አደጋ የደረሰባቸውን ለመርዳት 28 ሚሊዮን ዶላር b እንዲውል ፈቅዷል። ይህ ገንዘብ ከ200 በሚበልጡ አደጋዎች ለተጎዱ ወንድሞቻችን እርዳታ ለማበርከት አስችሏል፤ ከደረሱት አደጋዎች መካከል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በርካታ አውሎ ነፋሶች፣ በአፍሪካ የተከሰቱ ጎርፎች፣ በቬኔዙዌላ ያጋጠመው የምግብ እጥረት እና በዚምባብዌ የተከሰተው ድርቅ ይገኙበታል። በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ ምግብ፣ ውኃ፣ መጠለያ፣ ልብስ፣ የሕክምና ቁሳቁስ እንዲሁም ለጽዳት፣ ለጥገና እና ለመልሶ ግንባታ የሚያገለግሉ መሠረታዊ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ውሏል። የእርዳታ ሥራው ምን እንደሚመስል የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

 ኮቪድ-19፦ ወረርሽኙ በዓለም ዙሪያ በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ አካላዊ፣ ስሜታዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። እነዚህን ወንድሞች ለመርዳት በዓለም ዙሪያ ከ800 የሚበልጡ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል። እነዚህ ኮሚቴዎች ወንድሞቻችን የሚያስፈልጋቸውን ነገር በመከታተል ወዲያውኑ ሪፖርት ያቀርባሉ፤ ይህም የአስተባባሪዎች ኮሚቴው ምን ዓይነት እርዳታ ቢቀርብ የተሻለ እንደሆነ ለመወሰን ይረዳዋል።

 በዚህ ዓመት የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች፣ ብዙ ሰዎች ምግብ፣ ውኃ፣ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ እና ሕክምና እንዲያገኙ ረድተዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ኮሚቴዎቹ ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር ወንድሞች መንግሥት የሚያቀርበውን እርዳታ እንዲያገኙ ረድተዋቸዋል።

 የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችም የምናከናውነውን የእርዳታ ሥራ አስተውለዋል። ለምሳሌ በናኮንዴ፣ ዛምቢያ የአውራጃ አስተዳዳሪ የሆኑት ፊልድ ሲምዊንጋ “እርዳታ በእጅጉ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ፈጥናችሁ ስለደረሳችሁላቸው ውለታችሁን አንረሳውም” በማለት ለወንድሞቻችን ተናግረዋል።

 በአንጎላ የተከሰተ የምግብ እጥረት፦ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአንጎላ በምግብ አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ከመሆኑም ሌላ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር አድርጓል። በመሆኑም በርካታ ወንድሞችና እህቶች ምግብ ለመግዛት ተቸግረው ነበር።

ከብራዚል ወደ አንጎላ የተላኩት የታሸጉ ምግቦች

 የብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ በአንጎላ ለሚኖሩ ወንድሞቻችን ምግብ አሽጎ እንዲልክ ተጠይቆ ነበር። ለእርዳታ የሚውለውን ገንዘብ በአግባቡ ለመጠቀም ሲባል ምግቡ የሚገዛበትና የሚላክበት መንገድ በጥንቃቄ ተጠንቷል፤ ከዚያም ምግቡ በጅምላ ተገዛ። በመሆኑም በእያንዳንዱ እሽግ ውስጥ ያለውን ምግብ ለመግዛትና እሽጉን ለመላክ የወጣው ገንዘብ 22 ዶላር ብቻ ነው፤ እሽጎቹ ሩዝ፣ ቦሎቄና ዘይትን ጨምሮ 20 ኪሎ ግራም ገደማ የሚሆን ምግብ ይይዛሉ። እስካሁን ድረስ በድምሩ 654 ቶን የሚመዝኑ 33,544 እሽጎች ተልከዋል። የተላከው ምግብ በአካባቢው ከተገኘው ምግብ ጋር ተደምሮ ከ50,000 የሚበልጡ ሰዎችን መግቧል!

 ወንድሞቻችን የደረሳቸውን እርዳታ በተመለከተ ምን ይሰማቸዋል? አንጎላ ውስጥ በገለልተኛ አካባቢ የሚኖር አሌክሳንድሪ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የተደረገልኝ እርዳታ ይሖዋ እንደሚወደኝና ብቻዬን እንዳልሆንኩ አረጋግጦልኛል። የይሖዋ ድርጅት ከፍ አድርጎ ይመለከተኛል!” ማሪዛ የተባለች ነጠላ እናት እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ልመናዬን ሰምቷል። እሱንም ሆነ ድርጅቱን ከልብ አመሰግናለሁ!”

በአንጎላ የሚኖሩት ወንድሞች ለተላከላቸው እርዳታ አመስጋኞች ናቸው

 በዚምባብዌ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የተደረገ እርዳታ፦ በ2020 የአገልግሎት ዓመት ዚምባብዌ በከባድ ድርቅ ተጠቅታ ነበር፤ በዚህም ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ ተዳርገዋል። በዚምባብዌ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በቂ ምግብ አልነበራቸውም።

 ለወንድሞቻችን ምግብ ለማቅረብ አምስት የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ አስፋፊዎች ምግብ በማሸግ፣ በመጫን ወይም መኪናቸውን ለዚህ አገልግሎት በማዋል በእርዳታ ሥራው ተካፍለዋል። c በ2020 የአገልግሎት ዓመት ከ22,700 የሚበልጡ ሰዎችን ለመመገብ 691,561 ዶላር ወጪ ተደርጓል።

በዚምባብዌ የሚኖሩት ወንድሞች የተላከላቸውን የምግብ እርዳታ ሲቀበሉ (ከወረርሽኙ በፊት)

 አንዳንዶቹ ወንድሞች እርዳታ የደረሳቸው፣ በቤታቸው የነበረው ምግብ በተሟጠጠበት ወቅት ነው። ወንድሞቻችን ምግቡ ሲደርሳቸው ይሖዋን አወደሱ። እንዲያውም አንዳንዶቹ የመንግሥቱን መዝሙሮች መዘመር ጀመሩ።

 በአንድ አካባቢ፣ መበለት የሆኑ ሁለት እህቶች አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ በተደረገ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ነበር። ሆኖም ስብሰባው ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ስላስተዋሉ እህቶቻችን እርዳታውን ለማግኘት የሚያስፈልገውን ቅድመ ሁኔታ መቀበል እንደሌለባቸው ወሰኑ። ስብሰባውን ለቀው ሲወጡ ሰዎቹ “በኋላ ምግብ ፍለጋ እኛ ጋ እንዳትመጡ!” ብለው አሾፉባቸው። ሆኖም ከሁለት ሳምንት በኋላ፣ ወንድሞች ያዘጋጁት እርዳታ እዚያ አካባቢ ደርሶ እህቶቻችን የሚያስፈልጋቸውን ምግብ አገኙ፤ ይህ የሆነው የእርዳታ ድርጅቱ የሚያቀርበው የምግብ እርዳታ ከመድረሱ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው።

ፕሪስካ “ይሖዋ አገልጋዮቹን አሳፍሯቸው አያውቅም” ብላለች

 በዚምባብዌ የተካሄደው የእርዳታ ሥራ ለአካባቢው ነዋሪዎችም ጥሩ ምሥክርነት ሰጥቷል። በአነስተኛ መንደር ውስጥ የምትኖረውን የፕሪስካን ምሳሌ እንመልከት። ድርቁ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ቢፈጥርም ፕሪስካ ረቡዕንና ዓርብን ለአገልግሎት መድባ ነበር፤ እርሻ በሚታረስበት ጊዜም እንኳ በእነዚህ ቀናት ታገለግላለች። በመንደሩ የሚኖሩ ሰዎች “ስብከት፣ ስብከት ስትይ ቤተሰብሽን በረሃብ ልትጨርሺ ነው” እያሉ ያሾፉባት ነበር። እሷም “ይሖዋ አገልጋዮቹን አሳፍሯቸው አያውቅም” ብላ ትመልስላቸዋለች። ብዙም ሳይቆይ ፕሪስካ ድርጅታችን የላከው የእርዳታ ቁሳቁስ ደረሳት። አንዳንዶቹ ጎረቤቶቿ በዚህ በጣም ስለተደነቁ ፕሪስካን “አምላክ አሳፍሮሽ አያውቅም፤ ስለዚህ ስለ እሱ መማር እንፈልጋለን” አሏት። በአሁኑ ወቅት ሰባት ጎረቤቶቿ በሬዲዮ የሚተላለፈውን የጉባኤ ስብሰባ ይከታተላሉ።

 ወደ መጨረሻው ይበልጥ በተቃረብን መጠን ብዙ የተፈጥሮ አደጋዎች እንደሚከሰቱ እንጠብቃለን። (ማቴዎስ 24:3, 7) በ​donate.pr418.com ላይ በተዘረዘሩት የተለያዩ መንገዶች አማካኝነት በልግስና ላደረጋችሁት መዋጮ እናመሰግናለን። የምታደርጉት መዋጮ አፋጣኝ እና ውጤታማ እርዳታ ለማበርከት ያገለግላል።

a የ2020 የአገልግሎት ዓመት ከመስከረም 2019 እስከ ነሐሴ 2020 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል።

b በዚህ ርዕስ ውስጥ ሁሉም ገንዘቦች የተጠቀሱት በአሜሪካ ዶላር ነው።

c ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በወጡት ገደቦች የተነሳ ወንድሞቻችን ምግብ ለማድረስ ፈቃድ መጠየቅ አስፈልጓቸዋል። በተጨማሪም በቫይረሱ የመያዝ አጋጣሚያቸውን ለመቀነስ ሲሉ ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገዋል።