የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
“እስከ ምድር ዳር ድረስ” የሚሰብኩ ሚስዮናውያን
ሰኔ 1, 2021
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ተልእኮ በቅንዓት እየተወጡ ነው። ይሁንና ብዙ ሰዎች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች ጨምሮ በአንዳንድ የምድራችን ክፍሎች ምሥራቹ በደንብ አልተዳረሰም። በአንዳንድ አገሮች ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ አነስተኛ ነው። (ማቴዎስ 9:37, 38) ታዲያ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ምሥራቹን የሚሰሙበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ለመርዳት ምን ጥረት እየተደረገ ነው?
የበላይ አካሉ የአገልግሎት ኮሚቴ፣ የኢየሱስን ትእዛዝ ለመፈጸም ሲል በዓለም ዙሪያ ሰባኪዎች በሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች የመስክ ሚስዮናውያንን መድቧል። በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም 3,090 የመስክ ሚስዮናውያን አሉ። a ከእነዚህ ሚስዮናውያን መካከል አብዛኞቹ እንደ መንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች ሠልጥነዋል። ሚስዮናዊ ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች መኖሪያቸውን ትተው ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ፈቃደኞች ናቸው። በመንፈሳዊ የጎለመሱትና ብዙ ተሞክሮ ያላቸው እነዚህ ታማኝ ሚስዮናውያን ምሥራቹ እንዲስፋፋ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ከመሆኑም ሌላ ለአዳዲስ ደቀ መዛሙርት ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ።
ሌሎችን የሚረዱትን ሚስዮናውያን መርዳት
በእያንዳንዱ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በሚገኘው የአገልግሎት ዘርፍ ሥር ያለው የመስክ አገልጋዮች ዴስክ ከቅርንጫፍ ኮሚቴው ጋር በመተባበር ሚስዮናውያን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ጥረት ያደርጋል፤ ከእነዚህ መካከል ተስማሚ መኖሪያ፣ ሕክምናና አነስተኛ የሆነ የወጪ መሸፈኛ ይገኙበታል። በ2020 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሚስዮናውያኑ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት ወደ 27 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አውጥተዋል። ይህ ዝግጅት ሚስዮናውያኑ ሙሉ ትኩረታቸውንና ጉልበታቸውን በአገልግሎታቸው እንዲሁም ያሉበትን ጉባኤ በማጠናከሩ ሥራ ላይ እንዲያውሉ ያስችላል።
የመስክ ሚስዮናውያን የስብከቱን ሥራ እየደገፉ ያሉት እንዴት ነው? የማላዊ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ፍራንክ ሜሰን እንዲህ ብሏል፦ “በስብከቱ ሥራ ጥሩ ችሎታ ያላቸውና ደፋር የሆኑት ሚስዮናውያን ጉባኤዎች በአጥር የተከለሉ መንደሮችንና የውጭ አገር ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች የሚገኙባቸውን አካባቢዎች ጨምሮ አስቸጋሪ ክልሎችን መሸፈን እንዲችሉ ረድተዋል። በተጨማሪም የአካባቢውን ቋንቋና ባሕል ለመማር የሚያደርጉት ትጋት የተሞላበት ጥረት ለሌሎች ግሩም ምሳሌ ሆኗል፤ እንዲሁም የእነሱ በጎ ተጽዕኖ ወጣቶች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ግብ እንዲያወጡ ያነሳሳል። ይሖዋ እነዚህን የመስክ ሚስዮናውያን ስለሰጠን እናመሰግነዋለን።”
በሌላ አገር የሚያገለግል የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ሚስዮናውያን የይሖዋ ሕዝቦች በዓለም ዙሪያ አንድ እንደሆኑ የሚያሳዩ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችም እንኳ በባሕል የተከፋፈልን ሰዎች እንዳልሆንን፣ ከዚህ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንድ ቤተሰብ እንዳደረገን በግልጽ ማየት ይችላሉ።”
የመስክ ሚስዮናውያን፣ በተመደቡባቸው ጉባኤዎች ያሉ አስፋፊዎችን የሚረዱት እንዴት ነው? በቲሞር ሌስተ የሚኖረው ፓውሎ በጉባኤው ለተመደቡት ሚስዮናውያን ከፍተኛ አድናቆት አለው። እንዲህ ብሏል፦ “አካባቢያችን በጣም ሞቃት ነው። ሚስዮናውያኑ የመጡት ከቀዝቃዛ አገር ቢሆንም እዚህ ያለው የአየር ሁኔታ ከመስበክ እንዲያግዳቸው አልፈቀዱም። ጠዋት ላይ በሚደረጉት የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ላይ ሁሌም ይገኛሉ። አየሩ በጣም ሞቃት በሚሆንበት የቀትር ሰዓት እንዲሁም ምሽት ላይ ተመላልሶ መጠየቅ ሲያደርጉ በተደጋጋሚ አያቸዋለሁ። እኔን ጨምሮ ብዙ ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ ረድተዋል። መላ ሕይወታቸውን ይሖዋን በቅንዓት ለማገልገል ይጠቀሙበታል፤ የጉባኤው ወንድሞችና እህቶች የእነሱን ምሳሌ በማየታቸው ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል ተነሳስተዋል።”
በማላዊ የምትኖር ኬቲ የተባለች የዘወትር አቅኚ፣ ሚስዮናዊ ሆነው የሚያገለግሉ አንድ ባልና ሚስት እሷንና ቤተሰቧን እንዴት እንደረዷቸው ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ሚስዮናውያኑ ወደ ጉባኤያችን ሲመደቡ ከቤተሰባችን ውስጥ የይሖዋ ምሥክር የሆንኩት እኔ ብቻ ነበርኩ። ሆኖም እነዚህ ባልና ሚስት በብዙ መንገዶች ድጋፍ አድርገውልኛል፤ ደግሞም ከቤተሰባችን ጋር በጣም ተቀራርበዋል። እነሱ በተዉት ግሩም ምሳሌ የተነሳ ልጆቼ ይሖዋን ማገልገል አስደሳችና አርኪ ሕይወት ለመምራት እንደሚረዳ ማስተዋል ችለዋል። አሁን ሦስቱ ሴቶች ልጆቼ በዘወትር አቅኚነት እያገለገሉ ሲሆን ባለቤቴ ደግሞ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምሯል፤ ይህ ውጤት የተገኘው በእነሱ በጎ ተጽዕኖ ምክንያት ነው።”
የመስክ ሚስዮናውያን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት የሚውለው ገንዘብ የሚገኘው ከየት ነው? ለዓለም አቀፉ ሥራ ከተደረገው መዋጮ ነው፤ ከእነዚህ መዋጮዎች መካከል አብዛኞቹ የሚደረጉት donate.pr418.com ላይ የሚገኙትን ዘዴዎች በመጠቀም ነው። በልግስና የምታደርጉትን መዋጮ እጅግ እናደንቃለን።
a እነዚህ ሚስዮናውያን በስብከቱ ሥራ እርዳታ ወደሚያስፈልግባቸው አካባቢዎች ይመደባሉ። ሌሎች 1,001 የሚሆኑ የመስክ ሚስዮናውያን ደግሞ በወረዳ ሥራ ላይ ያገለግላሉ።