በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

የስብሰባ አዳራሾቻችንን መንከባከብ

የስብሰባ አዳራሾቻችንን መንከባከብ

ሚያዝያ 1, 2024

 በኮሎምቢያ የምትኖር ኒኮል የተባለች ወጣት እህት እንዲህ ብላለች፦ “የስብሰባ አዳራሻችንን በጣም እወደዋለሁ! ከመንፈሳዊ ቤተሰቤ ጋር የምገናኝበት ቦታ ነው።” አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል?

 በዓለም ዙሪያ የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰበሰቡባቸው 63,000 ገደማ የስብሰባ አዳራሾች አሉ። እነዚህ ሕንፃዎች አምላክን ማምለክ የምንችልባቸው ምቹ ቦታዎች ናቸው። ግን ይህ ብቻ አይደለም። በኮሎምቢያ የሚኖር ዴቪድ የተባለ የዘወትር አቅኚ እንዲህ ብሏል፦ “የስብሰባ አዳራሻችን ትምህርታችንን ያስውበዋል። የስብሰባ አዳራሻችንን የሚያዩ ብዙ ሰዎች ሕንፃውን እንዲህ ባለ ጥሩ መንገድ መያዛችን ይገርማቸዋል።” ይህ የሆነው በአጋጣሚ አይደለም። የስብሰባ አዳራሾቻችንን ለማጽዳትና ለመጠገን ተግተን እንሠራለን። ይህ ሥራ የሚካሄደው እንዴት ነው?

አዳራሾችን የመንከባከቡ ሥራ የተደራጀው እንዴት ነው?

 የስብሰባ አዳራሹን የመንከባከብ ኃላፊነት በዋነኝነት የሚወድቀው አዳራሹን በሚጠቀሙት ጉባኤዎች ላይ ነው። ለዚህም ሲባል ወንድሞችና እህቶች የስብሰባ አዳራሻቸውን አዘውትረው ያጸዳሉ። በተጨማሪም ብልሽት እንዳይፈጠር የስብሰባ አዳራሹን ይከታተላሉ፤ እንዲሁም አነስተኛ የጥገና ሥራዎችን ይሠራሉ።

 የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ክፍል ጉባኤዎች የስብሰባ አዳራሻቸውን እንዲንከባከቡ ለመርዳት የጥገና አሠልጣኝ የሚሆኑ ወንድሞችን ይመድባል። እያንዳንዱ የጥገና አሠልጣኝ ከስድስት እስከ አሥር የስብሰባ አዳራሾችን ይከታተላል። አዳራሾቹን ሄዶ ይቃኛል፤ እንዲሁም አዳራሹን መንከባከብ ስለሚቻልበት መንገድ ለጉባኤዎቹ አስፋፊዎች ሥልጠና ይሰጣል። በየሦስት ዓመቱ እያንዳንዱን አዳራሽ በመቃኘት ከደህንነት ወይም ከጥገና ጋር የተያያዘ ችግር መኖሩን ይገመግማል።

የጥገና አሠልጣኞች የስብሰባ አዳራሾቻችንን ጥሩ አድርገን ለመያዝ ይረዱናል

 ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የጥገና አሠልጣኞች ለሚሰጧቸው ሥልጠና አድናቆት አላቸው። በሕንድ የምትኖር ኢንዱማቲ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ሥልጠናው ግሩም ነበር። አዳራሻችንን ጥሩ አድርገን መያዝ ስለምንችልበት መንገድ በመማራችን ደስ ብሎኛል።” በኬንያ የሚኖር ኤቫንስ የተባለ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ትናንሽ ችግሮችን ከመባባሳቸው በፊት በመፍታት ከከባድ ወጪዎች መዳን የምንችልበትን መንገድ ተምረናል።”

ወጪውን መሸፈን

 አንድን የስብሰባ አዳራሽ ለመከታተልና ለመጠገን በየዓመቱ በመቶዎች ብሎም በሺዎች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ሊያስፈልግ ይችላል፤ ወጪው የተመካው አዳራሹ በሚገኝበት ቦታ፣ በአዳራሹ የአገልግሎት ዘመን እንዲሁም አዳራሹን በሚጠቀሙት ጉባኤዎች ብዛት ላይ ነው። ይህ ወጪ የሚሸፈነው እንዴት ነው?

 አዳራሾችን ለመንከባከብ የሚያስፈልገው ወጪ የሚሸፈነው በመዋጮ ነው። በካዛክስታን የሚኖረው ወንድም አሌክሳንደር ጉዳዩን ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “የተወሰነው ገንዘብ የሚውለው ለኢንተርኔት፣ ለውኃና ለኤሌክትሪክ ክፍያ ነው። በተጨማሪም እንደ ሶፍት፣ ጓንት፣ የጽዳት ቁሳቁስና ቀለም ያሉትን ነገሮች ለመግዛት ይውላል።” ከዚህ የተረፈ ገንዘብ ካለ ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ተደርጎ በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ ገንዘብ የሚያስወጡ ትላልቅ የጥገና ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ ይውላል።

ትላልቅ የጥገና ፕሮጀክቶች

 አንድ የስብሰባ አዳራሽ ጉባኤው ለሁለት ወይም ለሦስት ወር ከመደበው የአዳራሽ ክትትል ወጪ የሚበልጥ ገንዘብ የሚጠይቅ ጥገና ካስፈለገው ሽማግሌዎች የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ክፍል የመደበውን የጥገና አሠልጣኝ ያማክራሉ። የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ክፍል ለፕሮጀክቱ ፈቃድ ከሰጠ ብዙውን ጊዜ የጥገና ወጪው ለዓለም አቀፉ ሥራ በተደረገው መዋጮ ይሸፈናል። በ2023 የአገልግሎት ዓመት 8,793 ፕሮጀክቶች የተካሄዱ ሲሆን ለዚህም 76.6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጥቷል። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ሁለቱን እንመልከት።

 አንጎላ ውስጥ ከተገነባ 15 ዓመት የሆነው አንድ የስብሰባ አዳራሽ የተለያዩ ችግሮች ነበሩበት። የኤሌክትሪክ መስመሩ መቀየር ነበረበት፤ ግድግዳው ተሰንጥቆ ነበር፤ እንዲሁም በአዳራሹ ጎረቤት የሚኖሩ ሰዎች ውኃ ከአዳራሹ ወደ ቤታቸው እየፈሰሰ እንደሆነ አቤቱታ ያቀርቡ ነበር። የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ክፍል እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አንድ ፕሮጀክት አደራጀ። ለፕሮጀክቱ 9,285 የአሜሪካ ዶላር ወጥቷል። የአዳራሹ ጎረቤቶች ለፕሮጀክቱ ምስጋናቸውን የገለጹ ሲሆን ሥራው በተከናወነበት መንገድም በእጅጉ ተደንቀዋል።

አንጎላ ውስጥ የታደሰው የስብሰባ አዳራሽ

 ፖላንድ ውስጥ አንድ የስብሰባ አዳራሽ ጣሪያው ውኃ ያፈስ ነበር፤ ምንጣፉ ደግሞ መቀየር ነበረበት። የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ክፍል ጣሪያውን ለመጠገንና ምንጣፉን ለመቀየር የሚያስችል ፕሮጀክት እንዲካሄድ ፈቃድ ሰጠ። ፕሮጀክቱ 9,757 የአሜሪካ ዶላር ፈጅቷል። ይህ ፕሮጀክት በመከናወኑ፣ ከዚህ በኋላ ላሉት በርካታ ዓመታት አዳራሹ መሠረታዊ እድሳት አያስፈልገውም።

ፖላንድ ውስጥ እየተካሄደ ያለ የስብሰባ አዳራሽ እድሳት

የጥገና ሥራ ይሖዋን ያስከብራል

 የጥገና ሥራ በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ ለመቆጠብ ብቻ ሳይሆን ይሖዋን ለማስከበርም ያስችላል። በቶንጋ የሚኖረው ወንድም ሾን እንዲህ ብሏል፦ “አዳራሻችንን መንከባከባችን ይሖዋን ንጹሕና ሥርዓታማ በሆነ፣ የተሟላ አገልግሎት በሚሰጥ እንዲሁም ስሙን በሚያስከብር የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ለማምለክ ያስችለናል። ሰዎችን ወደ ስብሰባ አዳራሻችን የምንጋብዘው ኩራት እየተሰማን ነው።”

እርዳታ ማበርከት የምትችሉት እንዴት ነው?

 ሁላችንም አዳራሻችንን ለማጽዳትና ለመጠገን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። በአውስትራሊያ የሚኖር ማሪኖ የተባለ የጥገና አሠልጣኝ እንዲህ ብሏል፦ “ሁላችንም ልዩ መብት በሆነው አዳራሻችንን የመንከባከብ ሥራ መካፈል እንችላለን። እንዲህ ስናደርግ በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ እንዲቆጠብና ይበልጥ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ እንዲውል አስተዋጽኦ እናደርጋለን።”

 በሕንድ የሚኖረው ወንድም ጆኤል የስብሰባ አዳራሹን መንከባከብ ያስደስተዋል። እንዲህ ብሏል፦ “ከወንድሞቼ ጋር አብሬ ስሠራ በገነት ውስጥ የሚኖረን ሕይወት ምን እንደሚመስል በትንሹ እንዳየሁ ይሰማኛል።” ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኒኮል ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ከተወሰነ ጊዜ በፊት ወንድሞች በመጸዳጃ ቤቱ ውስጥ ያለውን የሚያፈስ ቧንቧ ሲጠግኑ መሬቱን በመወልወል ሳግዛቸው ነበር። ለችግሩ በቀጥታ መፍትሔ ባልሰጥም አደጋ እንዳይከሰት መርዳት ችያለሁ።”

 የስብሰባ አዳራሻችሁን በመንከባከቡ ሥራ ለመካፈል ራሳችሁን ማቅረብ የምትፈልጉ ከሆነ የጉባኤያችሁን ሽማግሌዎች አነጋግሩ። በተጨማሪም የምታደርጉት መዋጮ እናንተ የምትሰበሰቡበትን አዳራሽ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች የስብሰባ አዳራሾችንም ለመጠገን ይውላል። በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ባለው የመዋጮ ሣጥን ወይም በ​donate.pr418.com አማካኝነት መዋጮ ማድረግ ይቻላል። የምታሳዩትን የልግስና መንፈስ ከልባችን እናደንቃለን።

ሁላችንም የስብሰባ አዳራሻችንን ለመንከባከብ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን