የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
የስብከቱን ሥራ የሚያግዝ የግንባታ ሥራ
ጥቅምት 20, 2023
የበላይ አካሉ በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ ተጠቅሞ የመንግሥቱን ምሥራች ለማስፋፋት የሚረዱ ሕንፃዎችን ማዘጋጀት ይፈልጋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2023 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች የሚጠቀሙባቸው ሕጋዊ ማኅበራት የጉባኤና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችን በዓለም ዙሪያ ለመግዛት፣ ለመገንባት፣ ለማደስና ለመጠገን ከ500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ አውጥተዋል። ይህ አኃዝ፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጉባኤዎች የስብሰባ አዳራሾቻቸውን ለመንከባከብ ያወጡትን ገንዘብ አይጨምርም።
ከዚህም ሌላ በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎችን ለመገንባትና ለመንከባከብ ይውላል፤ ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ በዓለም ዙሪያ የሚከናወነውን የስብከት ሥራ ለማደራጀትና ለመደገፍ ያገለግላሉ። የጉባኤና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችን ለመገንባትና ለማደስ የሚውል ተጨማሪ ገንዘብ እንዲገኝ በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚከናወነው ሥራ ቀለል እንዲል ተደርጓል። ያም ቢሆን፣ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎችን ለመጠገን፣ ለማደስ ወይም ቦታ ለመቀየር ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ያስፈልጋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው? ቅርንጫፍ ቢሮዎች በመስኩ የሚከናወነውን አስፈላጊ ሥራ የሚደግፉት እንዴት ነው? መልሱን እስቲ እንመልከት።
“ዕድሜውን ያራዝመዋል”
ብዙዎቹ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ዕድሜያቸው ከ30 ወይም ከ40 ዓመት በላይ ነው! በዓለም አቀፉ የንድፍና ግንባታ ዲፓርትመንት ውስጥ የሚያገለግለው ኒኮላስ እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩ እንክብካቤ የሚደረግለት ሕንፃ እንኳ በጊዜ ሂደት ማርጀቱ አይቀርም። የእድሳት ሥራ፣ ሕንፃው አገልግሎት መስጠቱን እንዲቀጥል ዕድሜውን ያራዝመዋል።”
የቤቴል ሕንፃዎች ድርጅታዊ ለውጦችንም ማስተናገድ ይኖርባቸዋል። አብዛኞቹ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ከተገነቡ ወዲህ በዓለም ዙሪያ ያለው የአስፋፊዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ይህን እድገት ለማስተናገድ በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ተጨማሪ ፈቃደኛ ሠራተኞች አስፈልገዋል። በዚህም የተነሳ፣ ቀደም ሲል በቂ የነበሩ ሕንፃዎች በአሁኑ ጊዜ በሰው ተጨናንቀዋል!
የደህንነት ጉዳይም ከግምት መግባት ይኖርበታል። ወደ መጨረሻዎቹ ቀናት ይበልጥ ዘልቀን ስንገባ ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ብዙ የተፈጥሮ አደጋዎች ያጋጥሙናል። (ሉቃስ 21:11) በእድሳት ወቅት አዳዲስ የግንባታ ዘዴዎችን በመጠቀም ሕንፃዎቹ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን እናደርጋለን። እነዚህ ማሻሻያዎች፣ ሕንፃዎቹ የተፈጥሮ አደጋ ከደረሰ በኋላ የእርዳታ ሥራውን ለማስተባበርና በመስኩ የሚከናወነውን ሥራ ለመደገፍ የሚያስችሉ ማዕከላት እንዲሆኑ ሊያደርጉ ይችላሉ።
“ይሖዋ ይህን ውሳኔ ባርኮታል”
በበላይ አካሉ አመራር ሥር፣ በ2023 የአገልግሎት ዓመት በ43 ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ በሚገኙ ሕንፃዎች ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ የግንባታ ሥራ ተከናውኗል። ይህም ሲባል በዓለም ዙሪያ ካሉት ቤቴሎች ውስጥ ግማሽ ገደማ የሚሆኑት የሆነ ዓይነት የግንባታ ሥራ እየተሠራባቸው ነበር ማለት ነው። የዚህን ሥራ አስፈላጊነት የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።
አንጎላ። በአንጎላ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግለው ማት እንዲህ ብሏል፦ “በሐጌ 2:7 ላይ የሚገኘው ትንቢት ልዩ በሆነ መንገድ ሲፈጸም የማየት መብት አግኝተናል። በአሥር ዓመት ውስጥ ብቻ የአስፋፊዎች ቁጥር 60 በመቶ አድጓል። በዚህም የተነሳ የቤቴል ቤተሰብ በሦስት እጥፍ ማደግ ነበረበት። ያም ቢሆን የሕንፃዎቻችን አቅም የምንፈልገውን ያህል ሠራተኞችን እንዳንጠራ እንቅፋት ሆኖብናል። ይህም ብዙ ቤቴላውያን ከባድ ኃላፊነት እንዲሸከሙና ተጨማሪ ሰዓት እንዲሠሩ አስገድዷል።”
እድገቱን ማስተናገድ ስለሚቻልበት መንገድ ጥናት የሚያደርጉ ወንድሞች ተመደቡ። መጀመሪያ ላይ፣ ፈጣኑና የተሻለው አማራጭ አሁን ያለውን የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃ ማደስ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ሆኖም ሁኔታውን በደንብ ካጠኑ በኋላ፣ የአሁኑን ሕንፃ ማደስ በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም እንደማያስችል ተገነዘቡ። ከዚህ ይልቅ፣ በአቅራቢያው ያለ ሕንፃ ተገዝቶ እንዲታደስ ሐሳብ አቀረቡ። ማት እንዲህ ብሏል፦ “ሌላ ሕንፃ ገዝተን እናድስ የሚለው አማራጭ ለቅርንጫፍ ኮሚቴው በቀረበበት ወቅት ራሳችን የገነባነውን ሕንፃ ያህል ምቹ እንደማይሆን ተሰምቶን ነበር። አሁን ግን ሕንፃው ለሥራችን ተስማሚ እንደሆነ ተገንዝበናል። ይሖዋ ይህን ውሳኔ ባርኮታል።”
የአንጎላ ቅርንጫፍ ቢሮ ወደፊት ተጨማሪ የሥራ ቦታ መፈለጉ አይቀርም። ሆኖም አዲሱ ሕንፃ፣ በቤቴል ግቢ ውስጥ የተሠሩት ጊዜያዊ ቤቶች እንዲሁም ከቤቴል ግቢ ውጭ የተከራዩአቸው አፓርታማዎች ቅርንጫፍ ቢሮው በመስኩ ላይ የሚታየውን ከፍተኛ እድገት መደገፉን እንዲቀጥል አስችለውታል።
ጃፓን። ዋናዎቹ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች የተገነቡት ከ40 ዓመት በፊት ነው፤ እንዲሁም አብዛኞቹ ሕንፃዎች መሠረታዊ እድሳት ተደርጎላቸው አያውቅም። ሕንፃዎቹን ለመንከባከብ ብዙ ሥራ ተሠርቷል፤ ይሁንና እንዲህ ያለ የታሰበበት ጥረት ቢደረግም ሕንፃዎቹ ማርጀታቸው አልቀረም። በዚህም የተነሳ ሰፊ የእድሳት ፕሮጀክት ተጀምሯል።
ባለፉት ዓመታት የቤቴል ሕይወትም ተቀይሯል። ከ2015 በፊት ለቤቴል ቤተሰብ ቁርስ፣ ምሳና ራት ይቀርብ ነበር። በመሆኑም አብዛኞቹ የጃፓን ቤቴል የመኖሪያ ክፍሎች ኩሽናቸው በጣም ጠባብ ነው። በአሁኑ ወቅት ቤቴላውያን አብዛኛውን ምግባቸውን ራሳቸው ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። እድሳቱ የቤቴል ክፍሎች ሰፋ ያለ ኩሽና እንዲኖራቸው ስላስቻለ ቤቴላውያን በቀላሉ ምግባቸውን ማብሰል ይችላሉ። በጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ የምታገለግል ኩሚኮ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ኩሽናው በጣም ተመችቶኛል፤ አዳዲሶቹን የቤቴል ዝግጅቶች በተሟላ ሁኔታ እንድደግፍ ረድቶኛል።”
በጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር የሚከናወነው ሥራ ለዓለም አቀፉ ሥራ በጣም አስፈላጊ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ከሚታተምባቸው ሁለት ቅርንጫፍ ቢሮዎች አንዱ ነው። በመሆኑም የእድሳት ሥራው የቁርጥራጭ ወረቀትና የብናኝ መሰብሰቢያ ማሽን መግጠምን ያካትታል፤ ይህም በማተሚያው ውስጥ የሚሠሩትን ቤቴላውያን ደህንነት ለመጠበቅ ያስችላል። ይህን ማሽን ገዝቶ ለመግጠም አንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አካባቢ ፈጅቷል፤ ሆኖም ማሽኑ፣ ቅርንጫፍ ቢሮው መንፈሳዊ ምግብ ማተሙንና መላኩን እንዲቀጥል ያስችላል።
የግንባታ ሥራው በሚከናወንበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕትመት እንዳይቋረጥ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። በጃፓን ቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግለው ትሬይ እንዲህ ብሏል፦ “በግንባታ ሥራው ወቅት ድርጅታችን አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ያወጣ ነበር፤ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዞች ጨምረው ነበር። የሕትመት ሥራው ሳይቋረጥ አዳዲስ ማሽኖችን ለመግጠም በተለያዩ የቤቴል የሥራ ክፍሎችና በሕንፃ ተቋራጩ መካከል ከፍተኛ ቅንጅት አስፈልጓል።” እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ የማተሚያ ቤቱ የግንባታ ሥራ በተፋፋመበት ወቅት ማለትም ከመጋቢት እስከ ነሐሴ 2023 ድረስ በየወሩ ወደ 220,000 የሚጠጉ መጽሐፍ ቅዱሶች ታትመዋል። ይህ ሁሉ ሥራ የተከናወነው ያለተጨማሪ ወጪ ነው።
የእድሳት ሥራው ሌላ ጉልህ ገጽታ ኃይል ቁጠባ ነው። አዳዲስ የሶላር ፓነሎች ይተከላሉ፤ ይህም በየዓመቱ ለኤሌክትሪክ ከሚወጣው ገንዘብ 120,000 የአሜሪካ ዶላር ለመቆጠብ ያስችላል። የተነባበሩ ሦስት መስታወቶች ያሏቸው መስኮቶችም ይገጠማሉ፤ ይህም ለኤሌክትሪክ የሚወጣውን ወጪ በዓመት በ10,000 ዶላር ገደማ ይቀንሳል። ኃይል ለመቆጠብ የሚያስችሉት እነዚህ መሣሪያዎች ለእድሳት ፕሮጀክቱ የሚወጣውን ወጪ ቢጨምሩትም ፓነሎቹና መስኮቶቹ በሚያገለግሉበት ዘመን በድምሩ ከ3.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለመቆጠብ ያስችላሉ። ሕንፃዎቹ በሥነ ምኅዳሩ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖም ይቀንሳሉ።
“አሁንም ገና ብዙ ሥራ ይቀራል”
እነዚህ ሁለት የቅርንጫፍ ቢሮ ፕሮጀክቶች፣ የቤቴል ሕንፃዎች በመስኩ ያለውን ሥራ ለመደገፍ እንዲችሉ ምን ያህል ሥራ መሠራት እንዳለበት ያሳያሉ። ሆኖም ሥራው ገና አልተጠናቀቀም። በዓለም አቀፉ የንድፍና ግንባታ ዲፓርትመንት የሚያገለግለው አሮን እንዲህ ብሏል፦ “እስካሁን ብዙ ነገር ተሠርቷል፤ ግን አሁንም ገና ብዙ ሥራ ይቀራል።” ይህ ሥራ የሚከናወነው እንዴት ነው? አሮን እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች እነዚህን አስፈላጊ ፕሮጀክቶች ለመደገፍ ሲሉ በልግስና ከሚያደርጉት መዋጮ በተጨማሪ ቀደም ሲል በሥራው ለመካፈል ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀረቡትን እንዲሁም ወደፊትም ራሳቸውን ለማቅረብ በሕይወታቸው ላይ ማስተካከያ እያደረጉ ያሉትን ወንድሞቻችንን በጣም እናደንቃቸዋለን። ወንድሞቻችን የሚያደርጉት የገንዘብና የጉልበት ድጋፍ ይሖዋ እየባረከን እንደሆነ የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ነው።”—መዝሙር 110:3
የምናከናውናቸው የግንባታና የእድሳት ሥራዎች በሙሉ የሚደገፉት በፈቃደኝነት በሚደረጉ መዋጮዎች ነው፤ አብዛኛው መዋጮ የሚደረገው በdonate.pr418.com አማካኝነት ነው። ሁልጊዜም ለምታሳዩት ልግስና ከልብ እናመሰግናችኋለን።