የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
የኢየሱስ ወንጌል—ከካሜራ በስተ ጀርባ
ጥቅምት 1, 2024
በዚህ ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች በጉጉት ሲጠባበቋቸው ከነበሩ ክንውኖች መካከል አንዱ የኢየሱስ ወንጌል ክፍል 1 መውጣት ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ድራማውን ተመልክተውታል። ቀጣዮቹ 17 ክፍሎች ደግሞ ገና ይወጣሉ! ይህን ተከታታይ ድራማ ለማዘጋጀት ከካሜራ በስተ ጀርባ ምን ነገሮች እየተከናወኑ ነው? እናንተስ ይህን ሥራ የደገፋችሁት እንዴት ነው?
ተዋናዮችንና ባለሙያዎችን መንከባከብ
የኢየሱስ ወንጌል ቪዲዮ አብዛኛው ክፍል እየተቀረጸ ባለበት በአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እያንዳንዱ ትእይንት ሲቀረጽ ከ50 እስከ 80 ሰዎች ይሳተፋሉ። a ለሁሉም ተዋናዮችና ባለሙያዎች ምሳ፣ መክሰስና ራት ይቀርባል። የሚቀርበው ምግብ የሚወሰነው ቀደም ብሎ ነው። በምግብ አገልግሎት ክፍል የምትሠራው ኤስተር እንዲህ ብላለች፦ “ጥራት ያለውን ሸቀጥ በጥሩ ዋጋ ለማግኘት ስንል አስቤዛዎችን ከተለያዩ አቅራቢዎች እንገዛለን። በተጨማሪም ምግብ ተርፎ እንዳይጣል በምግቡ ዓይነት ላይ ዘወትር ማስተካከያ እናደርጋለን።” በየዕለቱ ለአንድ ሰው የምግብ ወጪ አራት የአሜሪካ ዶላር ገደማ እናወጣለን።
ተዋናዮቻችንና ባለሙያዎቻችን ምግብ ብቻ ሳይሆን ጥበቃም ያስፈልጋቸዋል። ከምን? አውስትራሊያ ፀሐያማ እንደመሆኗ መጠን አብዛኞቹ ቀናት ጥርት ያለ ሰማይ ያለባቸውና አየሩ ሞቃታማ የሆነባቸው ናቸው፤ ይህም የአልትራቫዮሌት ጨረር ተጋላጭነት ከፍ እንዲል ያደርጋል። በቦታው ያሉ ሁሉ በጨረሩና በኃይለኛው ሙቀት እንዳይጎዱ ሲባል ትጉ የሆኑ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ድንኳኖችንና ጥላማ ቦታዎችን ያዘጋጃሉ፤ እንዲሁም ሰንስክሪን፣ ጃንጥላና ውኃ ያቀርባሉ። በኦዲዮ/ቪዲዮ አገልግሎት ውስጥ የሚሠራው ኬቨን እንዲህ ብሏል፦ “አብዛኞቹ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ተመላላሽ ቤቴላውያን ናቸው። ይህን ጨምሮ ሌሎች ብዙ ሥራዎችን በትሕትናና በደስታ ያከናውናሉ። ያለእነሱ እርዳታ ይህን ፕሮጀክት ማሳካት አንችልም ነበር።”
ከቅርንጫፍ ቢሮው ውጭ ቀረጻ ማካሄድ
አንዳንድ ትእይንቶችን ስቱዲዮ ውስጥም ሆነ ቅርንጫፍ ቢሮው ጀርባ ባለው መስክ መቅረጽ አመቺ አይደለም። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም ቀረጻው ከቅርንጫፍ ቢሮው ውጭ ይካሄዳል። በጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ትእይንቶች ላይ የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ የአስፋልት መንገዶችና ዘመናዊ ቤቶች መኖር የለባቸውም፤ በመሆኑም ተዋንያንና ባለሙያዎች ለዚህ ቀረጻ ራቅ ወዳሉ ቦታዎች በተደጋጋሚ መጓዝ ያስፈልጋቸዋል። አልባሳት፣ ትእይንቱ ላይ የሚገቡ ቁሳቁሶችና መሣሪያዎች ተሸክፈው ወደ ቀረጻ ቦታው መወሰድና ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ መቀመጥ አለባቸው። ቀረጻ ከመጀመሩ በፊት የቀረጻው አስተባባሪዎች ጀነሬተር፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃና መጸዳጃ ቤት መኖሩን ያረጋግጣሉ። ተዋንያንና ባለሙያዎች እንግዳ ተቀባይ በሆኑ ወንድሞቻችን ቤቶች፣ በተጎታች ቤቶች ወይም በሆቴሎች ውስጥ ያርፋሉ።
ከቅርንጫፍ ቢሮው ውጭ ቀረጻ ማካሄድ ብዙ ገንዘብ የሚያስወጣ፣ ጊዜ የሚያባክንና አድካሚ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በ2023 የበላይ አካሉ 2.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የቪዲዮ ግድግዳ እንዲገዛ ፈቃድ ሰጠ፤ ይህ ቴክኖሎጂ ትእይንቱ በስፍራው የተቀረጸ እንዲመስል ያደርጋል። ቴክኖሎጂው መስክ ላይ ያለውን ትእይንት ለማምጣት፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው ምስልና ብርሃንን አቀናጅቶ ይጠቀማል። በመሆኑም ወደ ስፍራው ሄዶ መቅረጽ የሚያስከትለውን ከፍተኛ ወጪ ለማስቀረት ያስችላል። የአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ዳረን እንዲህ ብሏል፦ “የቪዲዮ ግድግዳ ተጠቅሞ መቅረጽ የተዋንያንን ድካም ይቀንሳል፤ ባለሙያዎችም አንዳንድ ትእይንቶችን ደጋግመው እንዲቀርጹ ያስችላል። ለምሳሌ ውጭ ወጥተን ቀረጻ ብናካሂድ ኖሮ ፀሐይ ስትጠልቅ ለመቅረጽ ያለን ጊዜ ጥቂት ደቂቃ ብቻ ይሆን ነበር። የቪዲዮ ግድግዳ ስንጠቀም ግን የምንፈልገውን ምስል እስክናገኝ ድረስ ፀሐይ ስትጠልቅ የሚያሳየውን ትእይንት ደጋግመን ማጫወት እንችላለን።”
“መሥዋዕትነት እንደከፈልኩ አልተሰማኝም”
የኢየሱስ ወንጌል የተባለው ተከታታይ ድራማ አንድ ክፍል እንኳ ሲቀረጽ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዋንያንና ከዚያ በጣም የሚበልጡ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ። እነዚህ ወንድሞቻችን እነሱን ለመንከባከብ ስለሚደረገው ጥረት ምን ይሰማቸዋል?
በፕሮጀክቱ ለመካፈል ስትል ከሜልበርን ከ700 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዛ የመጣችው አምበር እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “አውሮፕላን ማረፊያው ከደረስኩበት ጊዜ አንስቶ በቤቴል ያሉ ወንድሞች በጣም ተንከባክበውኛል። ብዙ ቤቴላውያን ምግብ ወይም ሻይ ቡና ጋብዘውኛል። በቀረጻ ቦታው ሁሉም እንዳይጨንቀኝና ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠኝ እንዲሰማኝ አድርገዋል። ጉዞዬ በበረከት የተሞላ ነበር። ምንም መሥዋዕትነት እንደከፈልኩ አልተሰማኝም!”
ዴሪክ የሚሠራው በቪዲዮ ዝግጅት ቡድኑ ውስጥ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “ከመጀመሪያው አንስቶ በርካታ ዲፓርትመንቶች ድጋፍ አድርገውልናል። ለዚህ ፕሮጀክት ጊዜያቸውን፣ ጥሪታቸውንና ጉልበታቸውን መሥዋዕት ባደረጉ ወንድሞችና እህቶች በመከበቤ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ተባባሪ፣ ፈቃደኛና ደግ ናቸው። ይሖዋ እነሱንም ሆነ እኛን እንደባረከን በግልጽ ይታያል። ይሖዋ፣ የሥራችን ውጤት ብቻ ሳይሆን ሥራውን የምናከናውንበትም መንገድ እንደሚያሳስበው እርግጠኛ ሆኛለሁ።”
በdonate.pr418.com አማካኝነትም ሆነ በሌሎች መንገዶች መዋጮ በማድረግ ይህን የቪዲዮ ፕሮጀክት ስለደገፋችሁ ከልብ እናመሰግናችኋለን።
a የአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ቢሮ አውስትራሊያንና በደቡብ ፓስፊክ የሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎችን ጨምሮ በብዙ አገሮች የምናከናውነውን ሥራ በበላይነት ይከታተላል። ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኘው ሲድኒ፣ አውስትራሊያ ውስጥ ነው።