የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
የጊልያድ ትምህርት ቤት ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነት
ታኅሣሥ 1, 2020
በየዓመቱ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ በርካታ የልዩ ሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ውስጥ በሚካሄደው የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንዲካፈሉ ይጋበዛሉ። a ተማሪዎቹ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ባሏቸው የተለያዩ ኃላፊነቶች ይበልጥ ውጤታማ መሆን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይማራሉ። ይህ ሥልጠና፣ ተመራቂዎቹ በመላው ዓለም የሚገኙ ጉባኤዎችንና ቅርንጫፍ ቢሮዎችን እንዲያጠናክሩና እንዲደግፉ ይረዳቸዋል።
በእርግጥም ጊልያድ ዓለም አቀፋዊ ትምህርት ቤት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በ2019 በተካሄደው 147ኛው ክፍል ላይ ከ29 አገሮች የመጡ 56 ተማሪዎች ተካፍለዋል። በጊልያድ ትምህርት ቤት እንዲሠለጥኑ የሚጋበዙት፣ የልዩ ሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ማለትም ቤቴላውያን፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ ሚስዮናውያንና ልዩ አቅኚዎች ናቸው።
ለትምህርት ቤቱ ዝግጅት ማድረግ የሚጀመረው ተማሪዎቹ ክፍል ከመግባታቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የዋናው መሥሪያ ቤት የጉዞ ዲፓርትመንት ወደ ጊልያድ ትምህርት ቤት ለተጋበዙ ተማሪዎች የአውሮፕላን ቲኬት ይገዛል። ለ147ኛው የጊልያድ ክፍል፣ የውጭ አገር ተማሪዎችን ወደ ፓተርሰን ለማምጣትና ወደ አገራቸው ለመመለስ ለእያንዳንዱ ተማሪ በአማካይ 1,075 የአሜሪካ ዶላር ወጥቷል። ከሰለሞን ደሴቶች የመጡ ተማሪዎች ወደ ፓተርሰን ለመምጣት አራት ጊዜ፣ ወደ አገራቸው ለመመለስ ደግሞ ሦስት ጊዜ አውሮፕላን መሳፈር አስፈልጓቸዋል፤ በድምሩ ከ35,400 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘዋል! የእነዚህ ተማሪዎች የአውሮፕላን ቲኬት ለእያንዳንዳቸው 2,300 የአሜሪካ ዶላር ፈጅቷል። ወጪ ለመቀነስ ሲባል፣ የዋናው መሥሪያ ቤት የጉዞ ዲፓርትመንት ረከስ ያለ ዋጋ ያላቸው ቲኬቶች ለማግኘት የሚረዳ የኮምፒውተር ሶፍትዌር ይጠቀማል። የኮምፒውተር ሶፍትዌሩ፣ ቲኬቱ ከተያዘ በኋላም እንኳ ይበልጥ የሚረክስ ቲኬት ለማግኘት ለሳምንታት ወይም ለወራት መፈለጉን ይቀጥላል። የዋናው መሥሪያ ቤት የጉዞ ዲፓርትመንት ቲኬት ለመግዛት በመዋጮ የተገኙ ማይሌጆችንና የአየር መንገድ ክሬዲቶችንም ይጠቀማል።
ብዙዎቹ ተማሪዎች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመግባት ቪዛ ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም የዋናው መሥሪያ ቤት የሕግ ክፍል የተማሪ ቪዛ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። እያንዳንዱን ተማሪ ለማስመዝገብና ለቪዛ በአማካይ 510 የአሜሪካ ዶላር ይፈጃል።
ተማሪዎቹ የሚያገኙት ሥልጠና ለሌሎችስ ምን ጥቅም ያስገኛል? ሄንድራ ጉናዋን በደቡብ ምሥራቅ እስያ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። በሚያገለግልበት ጉባኤ ውስጥ ከጊልያድ የተመረቁ ባልና ሚስት አሉ። እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል ጉባኤያችን ውስጥ አንድም የዘወትር አቅኚ አልነበረም። ተመራቂዎቹ ከመጡ በኋላ ግን ቅንዓታቸውና የነበራቸው የፈቃደኝነት ስሜት ወደ ሌሎችም ስለተጋባ የጉባኤው አስፋፊዎች የዘወትር አቅኚ ሆነው ማገልገል ጀመሩ። እንዲያውም በጉባኤያችን ያለች አንዲት እህት ከጊዜ በኋላ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተካፍላለች!”
ሰርጊዮ ፓንጃይታን በደቡብ ምሥራቅ እስያ በሚገኝ ቤቴል ውስጥ ከጊልያድ ምሩቃን ጋር አብሮ ይሠራል። እንዲህ ብሏል፦ “ያገኙት ሥልጠና ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለእኛም በረከት ሆኖልናል። ብዙ እውቀት አካብተዋል! ሆኖም በዚህ የተነሳ ራሳቸውን ከፍ ከፍ ከማድረግ ይልቅ የተማሩትን ነገር ለሌሎች ያካፍላሉ። ይህም እነሱ እኛን፣ እኛ ደግሞ ሌሎችን እያበረታታን እንድንቀጥል ያደርጋል።”
የዚህ ትምህርት ቤት ወጪዎች የሚሸፈኑት እንዴት ነው? ለዓለም አቀፉ ሥራ በሚደረገው መዋጮ አማካኝነት ነው፤ መዋጮ ማድረግ የሚቻልባቸውን ዘዴዎች donate.pr418.com ላይ ማግኘት ይቻላል። ይህን ዓለም አቀፋዊ ትምህርት ቤት ለመደገፍ በልግስና ለምታደርጉት መዋጮ እናመሰግናችኋለን።
a የትምህርት ቤቱን መርሃ ግብር የሚቀርጸው በበላይ አካሉ የትምህርት ኮሚቴ ሥር ያለው የቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች ክፍል ነው። በትምህርት ቤቱ የሚያስተምሩት በዚህ ክፍል ውስጥ የሚያገለግሉት ወንድሞችና ተጋባዥ አስተማሪዎች ናቸው፤ ከተጋባዥ አስተማሪዎች መካከል የበላይ አካል አባላት ይገኙበታል።