የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
“ጦርነትና የጦርነት ወሬ” ባለበት እርዳታ ማበርከት
ግንቦት 27, 2022
በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት “ጦርነትና የጦርነት ወሬ” እንደምንሰማ እንጠብቃለን። (ማቴዎስ 24:6) ያም ቢሆን፣ ወንድሞች በእነዚህ ክስተቶች የተነሳ ችግር ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ ያገኛሉ። በ2022 የበላይ አካሉ ሪፖርት ቁጥር 3 ላይ በዩክሬን በሚካሄደው ጦርነት የተጎዱትን ክርስቲያኖች ለመርዳት በምሥራቅ አውሮፓ እየተካሄደ ስላለው የእርዳታ ሥራ የሚያበረታታ መረጃ ሰምተን ነበር። በአቅራቢያው ጦርነት ቢኖርም ይህን እርዳታ ማድረስ የተቻለው እንዴት ነው? የእርዳታ እንቅስቃሴው በዩክሬን ያሉ ወንድሞቻችንን የጠቀማቸው እንዴት ነው?
ምን ዓይነት እርዳታ ያስፈልጋል? እርዳታውን ማድረስ የሚቻለውስ እንዴት ነው?
የካቲት 24, 2022 ማለትም በዩክሬን ጦርነቱ በጀመረበት ዕለት፣ የአስተባባሪዎች ኮሚቴው በዩክሬን ያሉ ወንድሞቻችንን ለመርዳት የሚውል በጀት አጸደቀ። የዩክሬን ቅርንጫፍ ቢሮ ወዲያውኑ የእርዳታ ቁሳቁሶችን መግዛትና ባቋቋማቸው 27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች አማካኝነት እርዳታውን ማከፋፈል ጀመረ።
ከዚህም በተጨማሪ በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ያሉ ወንድሞች ምን ዓይነት እርዳታ ማበርከት እንደሚቻል ወዲያውኑ ማሰብ ጀመሩ። የበላይ አካሉ የአስተባባሪዎች ኮሚቴና የሕትመት ኮሚቴ፣ ዓለም አቀፉ የግዢ ክፍል ከዩክሬንና ከፖላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮች ጋር በመሥራት እርዳታውን ለማቅረብ አስፈላጊውን ዕቅድ እንዲያወጣ ጠየቁ። በቅርንጫፍ ቢሮዎቹ ውስጥ ያሉት በዕቃ ግዢ፣ በዕቃ መላኪያና በሕግ ክፍል የሚያገለግሉ ወንድሞች፣ አንድ የዩክሬን ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል እንዲሁም የዓለም አቀፉ የዕቃ ግዢ ክፍል አባላት ሥራውን ለማደራጀት በየዕለቱ ይሰበሰቡ ነበር።
በዓለም አቀፉ የዕቃ ግዢ ክፍል ውስጥ የሚሠራው ጄይ ስዊኒ እንዲህ ብሏል፦ “በመጀመሪያ፣ የሚያስፈልጉትን ነገሮች መለየት ነበረብን። በዚያ ያሉ ወንድሞች የለመዷቸውን ምግቦችና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች መላክ ፈልገን ነበር። ሆኖም የሚያስፈልጉት ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ መለየት ብቻ በቂ አልነበረም። እነዚህን ቁሳቁሶች በጦርነቱ መሃል የወንድሞችን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥል መንገድ እንዲሁም በፍጥነት ወደ ዩክሬን ማድረስ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ነበረብን።”
እስከ መጋቢት 9, 2022 ድረስ፣ በዩክሬን ያሉ ወንድሞቻችን የሚያስፈልጓቸው ቁሳቁሶች የትኞቹ እንደሆኑ መለየት ተቻለ። የታሸገ ሥጋና ዓሣ፣ እህል፣ ሩዝ እንዲሁም ቦሎቄ የያዙ ካርቶኖችን እንደ ሳሙናና ሶፍት ካሉ መሠረታዊ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ጋር ለመላክ ወሰኑ። በወቅቱ ለአንድ ሰው ለአራት ሳምንት የሚበቃ የእርዳታ ቁሳቁስ ለመላክ 65 የአሜሪካ ዶላር ገደማ እንደሚያስፈልግ ተገምቶ ነበር። የአስተባባሪዎች ኮሚቴው በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን እርዳታ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ስለጠበቀ እርዳታውን ለማበርከት የሚውል ከፍተኛ መጠን ያለው በጀት አጸደቀ። ይሁንና የወንድሞቻችንን ሕይወት ሳያስፈልግ አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ እነዚህን ቁሳቁሶች ማድረስ የሚቻለው እንዴት ነው?
መጋቢት 13 ሁለት የፖላንድ ወንድሞች ከፖላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ተነስተው በልቪቭ፣ ዩክሬን አቅራቢያ ወደሚገኝ መጋዘን የእርዳታ ቁሳቁሶችን ለማድረስ የሙከራ ጉዞ አደረጉ። በፖላንድና በዩክሬን ቅርንጫፍ ቢሮ የሚሠሩ ወንድሞች፣ ሁለቱ ፈቃደኛ ሠራተኞች መንገድ ከመጀመራቸው በፊት አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ረዷቸው። ቅርንጫፍ ቢሮው ድንበር ተሻግሮ ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ የሚያስፈልጉትን ሕጋዊ ሰነዶች እንዲያሟሉ ረዳቸው፤ ወንድሞች የያዙት መኪና እርዳታ የያዘ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት በግልጽ እንዲለጠፍበት አደረገ፤ እንዲሁም በዩክሬን ካሉ ወንድሞች ጋር በመተባበር፣ ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ድንበሩን ከተሻገሩ በኋላ ሊከተሉት የሚችሉት ፈጣኑ መንገድ የትኛው እንደሆነ ለመለየት ጥረት አደረገ። ወንድሞች ያደረጉት ጥሩ ዝግጅት የይሖዋ በረከት ተጨምሮበት የእርዳታው ቁሳቁስ ልቪቭ በደረሰ በ24 ሰዓት ውስጥ ለአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች መሰራጨት ችሏል፤ ወንድሞቻችንም በሰላም ወደ ፖላንድ ተመልሰዋል።
የሙከራ ጉዞው የተሳካ ቢሆንም ወንድሞቻችን ያደረሱት ከአንድ ቶን ያነሰ የእርዳታ ቁሳቁስ ነበር። ገና 200 ቶን ገደማ የእርዳታ ቁሳቁስ ያስፈልጋል! ታዲያ ይህን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለውን የእርዳታ ቁሳቁስ በተቻለ ፍጥነት ማጓጓዝና ማሰራጨት የሚቻለው እንዴት ነው?
“ሕዝብህ በገዛ ፈቃዱ ራሱን ያቀርባል”
በዩክሬን በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ወንድሞቻችን የደረሰባቸውን ችግር ከjw.org ላይ ካነበቡ በኋላ በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞችና እህቶች እርዳታ ማበርከት ፈለጉ። ርቀው የሚኖሩ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ገንዘባቸው ጥሩ ዓላማ ላይ እንደሚውል በመተማመን ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ አደረጉ። በአጎራባች አገሮች የሚኖሩ ክርስቲያኖች ደግሞ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ንብረታቸውን በመስጠት እርዳታ ማበርከት ችለዋል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።
ፖላንድ ውስጥ ፈቃደኛ ሠራተኞች የእርዳታ ቁሳቁሶችን የያዙ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ካርቶኖችን አዘጋጁ፤ ልጆች ደግሞ ሥዕሎችን በመሣል ፖስት ካርዶችን ሠሩ። በፖላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ በዕቃ ግዢ ክፍል ውስጥ የሚያገለግለው ወንድም ባርቶሽ ኮሽቼልኒያክ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ሕዝብ በገዛ ፈቃዱ ራሱን እንደሚያቀርብ የሚገልጸውን በመዝሙር 110:3 ላይ ያለውን ሐሳብ በተደጋጋሚ አንብቤዋለሁ። ሆኖም በመቶዎች የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች ወዲያውኑ መጥተው ለሥራ ራሳቸውን ሲያቀርቡ ስመለከት የዚህን ጥቅስ እውነተኝነት በዓይኔ ማየት ችያለሁ።”
የሎጂስቲክስ ድርጅት ያለው አንድ የይሖዋ ምሥክር፣ የጭነት መኪኖቹ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ለማድረስ እንዲውሉ የፈቀደ ከመሆኑም ሌላ መኪኖቹን ለማንቀሳቀስ የሚውለውን ነዳጅ መዋጮ አድርጎ ሰጥቷል። እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ሁኔታ ለወንድሞቼና ለይሖዋ ያለኝን ፍቅር የማሳይበት አጋጣሚ ሰጥቶኛል። እርዳታ ለማበርከት ራሴን በማቅረቤ በጣም ደስተኛ ነኝ።” ከ7,700 ሊትር በላይ ነዳጅ በመዋጮነት እንደተሰጠ ይገመታል። በተጨማሪም ወንድሞች ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በፈቃደኝነት በመስጠት የእርዳታ ቁሳቁሶቹን ለማድረስ 48,000 ኪሎ ሜትር ገደማ በመኪና ተጉዘዋል!
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በፈቃደኝነትና በፍቅር ተነሳስተው ላከናወኑት ሥራ ምስጋና ይግባውና እስከ መጋቢት 28 ድረስ ማለትም የመጀመሪያው የሙከራ ጉዞ ከተካሄደ በኋላ ባሉት 15 ቀናት ውስጥ 100 ቶን የሚመዝኑ የምግብ፣ የንጽሕና መጠበቂያና የሕክምና ቁሳቁሶች ወደ ዩክሬን ማድረስ ተችሏል! ከዚህም ሌላ ወንድሞቻችንና ዕቃ አቅራቢዎች በልግስና ባደረጉት የቁሳቁስ መዋጮ የተነሳ እነዚህን የእርዳታ ቁሳቁሶች ለመግዛት ተመድቦ የነበረውን በጀት በእጅጉ መቆጠብ ተችሏል። እስካሁን ድረስ የይሖዋ ምሥክሮች ከ190 ቶን የሚበልጡ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ወደ ዩክሬን አድርሰዋል። የእርዳታ እንቅስቃሴው ወንድሞቻችንን የጠቀማቸው እንዴት ነው?
‘በውስጣቸው ፍቅራችሁም አለ!’
የእርዳታ ቁሳቁሶቹ ልቪቭ ከደረሱ በኋላ በመላው ዩክሬን የሚገኙ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ቁሳቁሶቹን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ክርስቲያኖች አሰራጭተዋል። የእርዳታ ቁሳቁሶቹ ወደተለያዩ ከተሞች ተልከዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ከተሞች የሚገኙት ከልቪቭ ከ1,300 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው ነው። ሥራውን በተቻለ መጠን በፍጥነት ለማከናወን ጥረት ቢደረግም ጊዜ መውሰዱ አልቀረም። a
የዩክሬን ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ማርከስ ሬይንሃርት እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ ጦርነት ወቅት በርካታ ወንድሞች የይሖዋን ፍቅር እንዲሁም አደጋ ከመድረሱ በፊትም ቢሆን የድርጅቱን መመሪያ በጥብቅ መከተል ያለውን ጥቅም ተመልክተዋል። ለምሳሌ ሁላችንም ለተወሰኑ ሳምንታት የሚበቃ ምግብና ውኃ በቤታችን ውስጥ እንድናስቀምጥ እንበረታታለን። በኪየቭ የሚያገለግል አንቶን የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ ይህን መመሪያ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ ‘የይሖዋ ድርጅት ለአስቸጋሪ ሁኔታዎች አዘጋጅቶናል፤ ለዚህም አመስጋኞች ነን። ምግብና ውኃ እንዲሁም ሬዲዮ ማስቀመጣችን ቃል በቃል ሕይወታችንን አትርፎልናል።’ ወንድሞች ይህን መመሪያ ተግባራዊ በማድረጋቸው በጣም አመስጋኞች ነን፤ ምክንያቱም ቅርንጫፍ ቢሮው አስፈላጊውን እርዳታ ለማስተባበር ጊዜ ማግኘት ችሏል።”
ወንድሞቻችን እርዳታው ሲደርሳቸው ምን ተሰማቸው? በካርኪቭ የሚኖሩት ሚኮላና ዚናይዳ እንዲህ በማለት ስሜታቸውን ገልጸዋል፦ “ባሳያችሁን አሳቢነት ልባችን በጥልቅ ተነክቷል። ለላካችሁልን ምግብና መድኃኒት በጣም እናመሰግናለን። የይሖዋን እጅ በግልጽ ማየት ችለናል።” በዚያው አካባቢ የምትኖረው ቫለንቲናም እንዲህ ብላለች፦ “ጦርነቱ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ አስቤዛ ለመግዛት ረጃጅም ሰልፎች ነበሩ። አንዳንድ ጊዜም የሚያስፈልገንን ነገር መግዛት አንችልም። ሆኖም ይሖዋ ችግራችንን አይቶልናል። የእርዳታ ቁሳቁሶችን ቤታችን ድረስ የሚያደርሱልን ወንድሞች ሾመልን። ደግሞም የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ አግኝተናል። እንዲህ ባለው አስቸጋሪ ወቅት ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ በሚመስልበት ጊዜ የይሖዋንና የድርጅቱን እንክብካቤ ልዩ በሆነ መንገድ ማጣጣም እንችላለን። . . . ይሖዋ የሚያስፈልገንን እርዳታና ድጋፍ ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ ሲሰጠን ማየት በጣም ያስደስታል።”
ከማሪዩፖል ሸሽተው የወጡት ዬቭሄን እና ኢሪና እንዲህ ብለዋል፦ “ለቤተሰባችን ለሰጣችሁን ድጋፍና ላደረጋችሁልን እንክብካቤ በጣም አመስጋኞች ነን። ብታምኑም ባታምኑም፣ ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ ነው የደረሳችሁልን። መጀመሪያ ላይ በካርቶኖቹ ውስጥ የእርዳታ ቁሳቁሶች ብቻ ያሉ መስሎን ነበር። ካርቶኖቹን ስንከፍታቸው ግን በውስጣቸው ፍቅራችሁም እንዳለ ተመለከትን!”
“ጦርነትና የጦርነት ወሬ” ባለበት ይህን ፍቅራዊ እርዳታ ማበርከት የተቻለው በይሖዋ መንፈስና አመራር እንደሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል። ለዓለም አቀፉ ሥራ ያደረጋችሁት መዋጮም ትልቅ ሚና ተጫውቷል፤ ብዙዎቻችሁ መዋጮ ያደረጋችሁት በdonate.pr418.com አማካኝነት ነው። ለምታሳዩት ልግስና ከልብ እናመሰግናለን!
በፍጥነትና በጥንቃቄ እርዳታ ማድረስ
የካቲት 24, 2022፦ የአስተባባሪዎች ኮሚቴ በዩክሬን ያሉትን ወንድሞች ለመርዳት የሚውል በጀት አጸደቀ፤ በመሆኑም ቅርንጫፍ ቢሮው የእርዳታ ሥራውን ጀመረ
ከየካቲት 24–መጋቢት 8, 2022፦ የዩክሬን ቅርንጫፍ ቢሮ አንዳንድ ቁሳቁሶችን በመግዛት በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች አማካኝነት ማከፋፈል ጀመረ። በተጨማሪም ቅርንጫፍ ቢሮው ከፖላንድ ቁሳቁሶችን በማስገባት ለማከፋፈል ዝግጅት ማድረግ ጀመረ
መጋቢት 9, 2022፦ የአስተባባሪዎች ኮሚቴው ወደ ዩክሬን የእርዳታ ቁሳቁሶች እንዲገቡ ፈቀደ
ከመጋቢት 10–12, 2022፦ ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን ከፖላንድ ወደ ልቪቭ፣ ዩክሬን ለመውሰድ የሙከራ ጉዞ እንዲደረግ ዝግጅት ተደረገ
መጋቢት 13, 2022፦ ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን ከፖላንድ ወደ ልቪቭ፣ ዩክሬን ለመውሰድ የተካሄደው የሙከራ ጉዞ ተሳካ
ከመጋቢት 14–16, 2022፦ የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች በፖዝናን፣ ፖላንድ አቅራቢያ በሚገኝ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ውስጥ ምግብና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በካርቶን ለማዘጋጀት ተደራጁ
መጋቢት 17, 2022፦ የሙከራ ጉዞው ከተሳካ ከአራት ቀናት በኋላ ወንድሞች 13 ቶን የሚመዝኑ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ወደ ዩክሬን መውሰድ ጀመሩ
ከመጋቢት 21–27, 2022፦ የቀሩት የእርዳታ ቁሳቁሶችም በተመሳሳይ መንገድ በፖላንድ ከተዘጋጁ በኋላ ወደ ዩክሬን ተወስደው በ24 ሰዓት ውስጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግባቸው ቦታዎች ተሰራጩ
መጋቢት 28, 2022፦ ወደ ዩክሬን እርዳታ እንዲገባ በተፈቀደ በ20 ቀን ውስጥ 100 ቶን የሚመዝኑ የምግብ፣ የንጽሕናና የሕክምና ቁሳቁሶች ወደ ዩክሬን ተልከዋል
እስካሁን ድረስ የይሖዋ ምሥክሮች ከ190 ቶን በላይ የሚመዝኑ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ወደ ዩክሬን ልከዋል።
a እርዳታው የተላከበትን መንገድ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “በዩክሬን ያሉ ወንድሞች በድፍረት እርዳታ ያደርሳሉ እንዲሁም በጦርነት ቀጠና ያሉትን ይታደጋሉ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት