በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

sinceLF/E+ via Getty Images

ነቅታችሁ ጠብቁ!

ለንጹሐን ዜጎች ማን ይደርስላቸዋል?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ለንጹሐን ዜጎች ማን ይደርስላቸዋል?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንዳደረገው፦

  •   ከጥቅምት 7 እስከ ጥቅምት 23, 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ በጋዛ እና በእስራኤል መካከል በተከፈተው ጦርነት ከ6,400 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 15,200 የሚሆኑ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ንጹሐን ዜጎች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።

  •   እስከ መስከረም 24, 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ በሩሲያና በዩክሬን መካከል በተከፈተው ጦርነት በዩክሬን ያሉ 9,701 ንጹሐን ዜጎች ተገድለዋል፤ 17,748 የሚያህሉት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

 መጽሐፍ ቅዱስ የጦርነት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች ምን ተስፋ ይሰጣል?

ተስፋ አለ!

 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ [እንደሚያስወግድ]” በትንቢት ተናግሯል። (መዝሙር 46:9) አምላክ ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት በአንድ ሰማያዊ መንግሥት ወይም አገዛዝ ይተካቸዋል። (ዳንኤል 2:44) የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች እፎይታ ያስገኛል።

 የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ምን እንደሚያደርግ ተመልከት፦

  •   “እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ፣ እንዲሁም ችግረኛውንና ረዳት የሌለውን ሁሉ ይታደጋልና። ለችግረኛውና ለድሃው ያዝናል፤ የድሆችንም ሕይወት ያድናል። ከጭቆናና ከግፍ ይታደጋቸዋል።”—መዝሙር 72:12-14

 አምላክ ጦርነትና ዓመፅ ያስከተሉትን ሰቆቃና መከራ በመንግሥቱ አማካኝነት ይቀለብሳል።

  •   “እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:4

 በቅርቡ የአምላክ መንግሥት በምድራችን ጉዳዮች እጁን ጣልቃ ያስገባል። መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ዙሪያችንን ስለከበበው “ጦርነትና የጦርነት ወሬ” አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:6) እነዚህን ጨምሮ በዘመናችን እየተፈጸሙ ያሉ ሌሎች ክስተቶች በሰው ዘር አገዛዝ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ውስጥ እንደምንኖር ይጠቁማሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1